ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚውል የ40 ሚሊዮን ገደማ የመማሪያ መጽሐፍት እጥረት እንዳለ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ 

ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ የመማሪያ መጽሐፍት ህትመትን በውጭ ሀገር ለማከናወን ከ16 ቢሊዮን ብር (105 ሚሊዮን ዶላር) በላይ ወጪ መደረጉን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከቅደመ አንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች የሚውል 24.7 ሚሊዮን የመማሪያ መጽሐፍት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያሳተመ ቢሆንም፤ እስከ 40 ሚሊዮን የሚደርስ የመጽሐፍት ፍላጎት አሁንም አለመሟላቱን ገልጿል።

መስሪያ ቤቱ ትላንት አርብ ህዳር 5፤ 2018 ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የሩብ ዓመት የስራ ሪፖርት፤ በህትመት ላይ የሚገኙት መጽሐፍት የእንግሊዝኛ፣ ሂሳብ እና የአካባቢ ሳይንስ የትምህርት አይነቶችን የያዙ እንደሆነ አመልክቷል። ህትመታቸው “በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ይጠናቀቃል” ለተባሉት ለእነዚህ መጽሐፍት ማሳተሚያ፤ ሚኒስቴሩ ሶስት ቢሊዮን ብር (19.8 ሚሊዮን ዶላር) ወጪ ማድረጉም በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል። 

ሪፖርቱን ለፓርላማው የሰው ሀብት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ እሸቱ ገላዬ፤ መስሪያ ቤታቸው ባለፉት ዓመታት የሁለተኛ ደረጃ መማሪያ መጽሐፍትን በማሳተም እና ወደ ክልሎች ለማውረድ እና ለተማሪዎች “አንድ ለአንድ ለማድረስ” መቻሉን አስታውሰዋል።

ከቅደመ አንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የመማሪያ መጻሐፍት የማሳተም “የክልሎች ስራ” መሆኑን የገለጹት አቶ እሸቱ፤  የትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ዓመት ይህንኑ ስራ ደርቦ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። ሚኒስቴሩ ከሚያደርገው “እገዛ” ባለፈ፤ ክልሎች በራሳቸው አቅም መጽሐፍ የሚያሳትሙበትን ሁኔታ “እየተነጋገርን ነው” ሲሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለዋል።

ሪፖርቱን ተከትሎ በፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ የተዘጋጀውን ጥያቄ በንባብ ያቀረቡት አቶ ታደሰ ጌጡ፤ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት “ለትምህርት ጥራት ወሳኝ” መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚህ ደረጃ ላሉ ትምህርት ቤቶች “የመማሪያ መጽሐፍት አንድ ለአንድ ማዳረስ ለምን አልተቻለም?” ሲሉ የጠየቁት የቋሚ ኮሚቴ አባሉ፤ “ክልሎች የማስተማሪያ መጽሀፍትን አሳትመው ለተማሪዎቻቸው ከማድረስ አኳያ አፈጻጸሙ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?” ሲሉ ተጨማሪ ጥያቄ አስከትለዋል።

የሚመሩት መስሪያ ቤት ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጻህፍት የማቅረብ ኃላፊነት እንደሌለበት በመጥቀስ ምላሻቸውን የጀመሩት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ለዚህ ተብሎ ለሚኒስቴሩ “የተመደበ በጀት እንደሌለ” ተናግረዋል። ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ትኩረት በመስጠት ብቻ የትምህርት ጥራት እንደማይሻሻል የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ተመሳሳይ ስራዎች “ከታችም ማድረግ አለብን” ብለዋል።

ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጽሐፍት የማቅረብ ኃላፊነት የክልሎች መሆኑን በድጋሚ በአጽንኦት ያነሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ለክልሎች የሚላከው በጀት “ይህንንም የሚያጠቃልል” እንደሆነ አስረድተዋል። “ክልሎች በበጀታቸው ላይ ከሚያገኙት ነገር አንዱ ይሄ ነው። ይሄንን ማድረግ አለባቸው” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ “ያንን እስኪያረጉ ግን ዝም ብለን እንጠብቅ አላልንም” ሲሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው እያደረገ ያለውን ጥረት ለፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል።  

“ገንዘብ ለምነን፤ እስኪ ቢያንስ በዋና ዋና ትምህርቶች በሳይንስ፣ በሂሳብ እና በእንግሊዝኛ አንድ መጽሀፍ ለአንድ ተማሪ እንዲደርስ ብለን፤ በትምህርት ሚኒስቴር 24.7 ሚሊዮን የመማሪያ መጽሐፍት እያሳተምን ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሆኖም ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በጠቅላላ የሚያስፈልገው መጽሐፍ 74.8 ሚሊዮን ገደማ መሆኑን በመጥቀስ በፍላጎት እና በአቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት አመልክተዋል።

ሚኒስቴሩ እና ክልሎች የሚሳትሟቸው መጽሐፍት ድምር ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ የሚፈለገው መጠን ላይ ለመድረስ “ሌላ 30፣ 40 ሚሊዮን መጽሐፍ ያስፈልጋል” ሲሉ አስረድተዋል። ለእያንዳንዱ ተማሪ አንዳንድ መጽሐፍ ለማድረስ፤ “ለሚቀጥለውም ዓመት ከቻልን ጥረት እናደርጋለን” ሲሉም ተደምጠዋል።፡

“እሱን የምናገኝበትን መንገድ እንደምታውቁት (donor) ለጋሾች አካባቢ የሚገኝ ገንዘብ እየቀነሰ እንጂ እየጨመረ እንደማይሄድ ታውቃላችሁ። በዚያ ላይ ብዙ መተማመን የለንም” ሲሉም የትምህርት ሚኒስትሩ ዘንድሮ መጽሐፍትን ሙሉ ለሙሉ ማዳረስ እንደማይቻል ጥቆማ ሰጥተዋል። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ችግሩን ለመቅረፍ ተስፋ ያደረጉት “በትልቁ” “በኢንዱስትሪ ደረጃ” ማተም የሚችሉ ኩባንያዎች  በሀገር ውስጥ ስራ መጀመርን ነው። 

“የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ቶፓን ግራቪቲ አሁንም እየተነጋገሩ [ነው።] ‘ጆይንት ቬንቸር’ አቋቁመው ከመጡልን፤ ቢያንስ የውጭ ምንዛሬ ስለማያስፈልግ በሀገር ውስጥ ገንዘብ የበለጠ አሳትሞ ማድረስ ይቻላል” ሲሉ መጽሐፍትን በሀገር ውስጥ ለማሳተም ያለው እቅድ አሁንም በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጃፓን የህትመት ኩባንያ የሆነው “ቶፓን ግራቪቲ” በኢትዮጵያ ቦሌ ለሚ ፓርክ ለሚገነባው ፋብሪካ በሚያዝያ 2016 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጠበት ወቅት፤ በአጭር ዓመታት የተማሪዎች የመጽሐፍት እጥረትን እንደሚቀርፍ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ኩባንያው ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍትን እንደሚያትም በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

የትምህርት ሚኒስቴር በ2016 የትምህርት ዘመን ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ፤ ይኸው ኩባንያ “ዝቅተኛ ዋጋ በማቅረቡ” ተመርጦ በ45 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የመማሪያ መጽሐፍትን እንዲያትም መደረጉ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። ሚኒስቴሩ ቤቱ በአሁኑ ወቅት የመማሪያ መጸሐፍትን እያሳተመ ያለው በቻይና ሀገር በሚገኝ ድርጅት እንደሆነ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከመስሪያ ቤቱ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለመማሪያ መጸሐፍት ህትመት ወጪ የተደረገው የገንዘብ መጠን ከ16 ቢሊዮን ብር (105 ሚሊዮን ዶላር) በላይ እንደሆነ ሚኒስቴሩ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት አስታውቋል። በእነዚህ ጊዜያት የታተሙ እና በህትመት ላይ ያሉ መጽሐፍት ብዛት 68.2 ሚሊዮን እንደሆነ በሪፖርቱ ላይስ ሰፍሯል። 

የትምህርት ሚኒስቴር የመጸሐፍት እጥረት ችግርን ለማቃለል፤ ተማሪዎች መጽሐፍትን በዲጂታል መንገድ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ቋት ማዘጋጀቱን ፕሮፌሰር ብርሃኑ በትላንቱ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል። “ከቴሌ ጋር በተስማማነው መሰረት ያለን የመጽሀፍ ፖርታል አለ። ማንም ሰው ስልኩ ላይ ማግኘት የሚችላቸው እነዚያ መጽሐፍት፤ እዚያ ፖርታል ላይ አሉ። ተማሪዎች እንዲያገኙት ግን አትመን ለማሰራጨት መሞከር አለብን። ክልሎች በዚህ ዙሪያ ቅድሚያ ሰጥተው ያደርጋሉ ብለን እናስባለን” ሲሉ ሚኒስትሩ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)