በአፋር ክልል ከደረሰው “ጥቃት” በኋላ የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት 18 ሺህ ገደማ መድረሱን ባለስልጣናት ተናገሩ  

በአፋር ክልል፣ መጋሌ ወረዳ ላይ ከደረሰው “ጥቃት” በኋላ ከቶንሳ ቀበሌ እና ከአጎራባች አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት 18 ሺህ ገደማ መድረሱን እና 11 ሺህ ያህሉ እስካሁን ድረስ ድጋፍ እንዳላገኙ የአካባቢው ባለስልጣናት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የክልሉን ወሰን ተሻግረው ወደ አካባቢው መግባታቸው የተነገረላቸው “የትግራይ ኃይሎች” አሁንም ስፍራውን ለቅቀው አለመውጣታቸውንም ገልጸዋል። 

የአፋር ክልል መንግስት ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ባወጣው መግለጫ “የህወሓት ቡድን” ሲል የጠራው አካል፤ በመጋሌ ወረዳ በሚገኘው ቶንሳ ቀበሌ ላይ ጥቃት ፈጽሞ ስድስት መንደሮችን “በጉልበት ተቆጣጥሯል” ሲል ወንጅሎ ነበር። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከአንድ ቀን በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ የትግራይ ክልል ኃይሎች “ወደ አፋር ክልል ዘልቀው ጥቃት ፈጽመዋል” መባሉን “መሰረተ ቢስ” ሲል ማስተባበሉ አይዘነጋም።  

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይበል እንጂ “የትግራይ ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸዋል” በተባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት፤ ታጣቂዎቹ ጥቃት መፈጸማቸውን እና አሁንም ስፍራውን ለቅቀው አለመውጣታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አንድ የቶንሳ ቀበሌ ኃላፊ “የትግራይ ኃይሎች” ሲሉ የጠሯቸው ታጣቂዎች ከሁለት ሳምንት በፊት የያዟቸው ከሚልኪ፣ ዋረዓ፣ ሚላ፣ ከረፈቱ፣ ካኦሶበራ እና ከረሙአጋ የተባሉ አካባቢዎች አሁንም በእነርሱ ቁጥጥር ስር መሆኑን ገልጸዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ዋረዓ ከሚባለው አካባቢ ተፈናቅለው አሁን አሮሪ በሚባል የቀበሌው አካባቢ ከሌሎች ተፈናቃዮች በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ በሚገኝ ዛፍ ጥላ ስር ተጠለለው የሚገኙ ሌላ ነዋሪ፤ በአካባቢው የሚገኙ የአፋር ክልል ሚሊሺያዎች እና ልዩ ኃይሎች ጋር እየደወሉ ሁኔታውን እንደሚከታታሉ ተናግረዋል። ከጸጥታ ኃይሎቹ ባገኙት መረጃ መሰረትም፤ በአካባቢው አሁንም የትግራይ ኃይሎች እንዳሉ ማረጋገጣቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። 

በተመሳሳይ ቦታ ላይ ከስምንት ልጆቻቸው ጋር ተፈናቅለው የሚገኙ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ፤ ከትላንት በስቲያ እሁድ ወደ መኖሪያቸው አቅራቢያ ተጉዘው አሁንም ስፍራው “በትግራይ ኃይሎች” ቁጥጥር ስር እንደሆነ እንደተመለከቱ የዓይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። “እነሱ እዚያ እያሉ መመለስ አንችልም” ሲሉም የቀያቸውን አካባቢ ትተው ተፈናቃዮች ወደተሰባሰቡበት ስፍራ የተመለሱበት ሁኔታ አስረድተዋል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በስልክ ያነጋገረቻቸው የቶንሳ ቀበሌ ኃላፊ፤ “የትግራይ ኃይሎች” አልፎ አልፎ “ከባድ መሳሪያ እንደሚተኩሱ” ገልጸዋል። የመጋሌ ወረዳ የእንስሳት፣ እርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱ መሐመድ በበኩላቸው፤ “የትግራይ ኃይሎች” አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በኋላ የቶንሳ ቀበሌ “ለሁለት ተከፍሎ ነው ያለው” ይላሉ።

ግማሹን የአፋር ክልል ሲያስተዳድረው፤ ግማሹን ደግሞ “የትግራይ ኃይሎች” አሁንም እንደያዙት አቶ አብዱ ተናግረዋል። የቶንሳ ቀበሌ ባለበት መጋሌ ወረዳ የተፈናቃዮችን ጉዳይ የሚከታተለውን ቢሮ የሚመሩት አቶ አብዱ፤ ከሁለት ሳምንት በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጡት ቃለ ምልልስ ከሶስት ቀበሌዎች በድምሩ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጸው ነበር። 

የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከሁለት ሳምንት በፊት ከተገለጸው ጭማሪ እንዳሳየ የጠቆሙት አቶ አብዱ፤ በአሁኑ ወቅት 18 ሺህ ገደማ መድረሱን አመልክተዋል። ከቶንሳ እና ፋሮ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች “አሮራ” በተባለ በቶንሳ ቀበሌ ላይ የሚገኝ ቦታ፣ ከአዱ ቀበሌ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ደግሞ ኤላከሎ በሚባል በቀበሌው በሚገኝ ቦታ ዛፍ ስር እና ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲያርፉ መደረጉን ኃላፊው አክለዋል።

አቶ አብዱ የተፈናቃዮቹ ቁጥር ሊጨምር የቻለው፤ “የትግራይ ኃይሎች” “በተቆጣጠሩት” አካባቢ “ተቆርጠው የቀሩ” ነዋሪዎች “እየሾለኩ” በመምጣታቸው መሆኑን አስረድተዋል። ተፈናቃዮቹ በአፋር አርብቶ አደር ልማት ማህበር በኩል 300 ኩንታል ዱቄት እና 70 ኩንታል በቆሎ ከክልሉ የአደጋ ስጋት እና መከላከል ኮሚሽን ድጋፍ እንደተደረገላቸው ኃላፊው አስረድተዋል። 

“በመጀመሪያው እርዳታ ለአንድ ሳምንት የሚያህል ነው ድጋፍ የተሰጣቸው። በቂ የሆነ ድጋፍ አይደለም” ያሉት አቶ አብዱ፤ “11 ሺህ አካባቢ ለሚሆኑ ተፈናቃዮች ገና ድጋፍ እየፈለግን ነው” ሲሉ አሁንም ለአካባቢው ነዋሪዎች ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ከሁለት ሳምንት በፊት ከሰባት ልጆቻቸው ጋር ከቤታችው እንደወጡ እንዳልተመለሱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹ ተፈናቃይ ይህንኑ አረጋግጠዋል።

በአፋር አርብቶ አደር ልማት ማህበር በኩል የቀረበው ዱቄት “ለሁሉም እንዳልተዳረሰ” የተናገሩት ተፈናቃዩ “እናቶች እና ልጆች በረሀብ፣ በጸሀይ እና በብርድ እየተሰቃዩ ነው” ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል። እንደ እርሳቸው ሁሉ ከልጆቻቸው ጋር የተፈናቀሉ ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ፤ 12 ኪሎ ዱቄት ቢደርሳቸውም እየቀረበ ያለው እርዳታ “በቂ አይደለም” ባይ ናቸው። እኚሁ ነዋሪ እርዳታ ያልደረሳቸው ሰዎች እንዳሉም አልሸሸጉም። 

ከ10 በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወደ አካባቢው መጥተው “ለሶስት እና አራት ቀናት” ጉብኝት ማድረጋቸውን የጠቀሱት የመጋሌ ወረዳ የእንስሳት፣ እርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ የተፈናቃዮችን ሁኔታ በአካል ከተመለከቱት ከእነዚህ ድርጅቶች “ብዙ ነገር እንጠብቃለን” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)