ኢትዮጵያ በዘንድሮው በጀት ዓመት ሶስት ወራት ብቻ ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶቿ 2.48 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ። በዚሁ ሩብ ዓመት ሚኒስቴሩ የሚከታተላቸው እንደ ጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ከመሳሰሉ ምርቶች 149 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንም መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
ሚኒስቴር ይህን የገለጸው፤ የ2018 በጀት ዓመት የሶስት ወራት እቅድ አፈጻጸምን በተመለከተ ከመስሪያ ቤቱ እና ከተጠሪ ተቋማት አመራሮች ጋር በተደረገው ውይይት ላይ ነው። ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ካሳሁን ጎፌ በሰጡት መግለጫ፤ በወጪ ንግድ ረገድ በሩብ ዓመቱ ከተያዘው እቅድ “117 ፐርሰንት” መፈጸም መቻሉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ (export) በጠቅላላ ለማግኘት ያቀደችው ገቢ 9.4 ቢሊዮን ዶላር ነው። ሀገሪቱ ባለፈው በጀት ዓመት ከዚሁ ዘርፍ ያገኘችው ገቢ 8.3 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር መገለጹ ይታወሳል። ይህ የገቢ መጠን በሀገሪቱ ታሪክ “ለመጀመሪያ ጊዜ” የተመዘገበ መሆኑን ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከሳምንት በፊት ፓርላማውን በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ላይ አስታውቀው ነበር።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ገቢ ካለፈው ዓመት በ1.1 ቢሊዮን ዶላር የላቀ ነው። በዘርፉ ባለፉት ሶስት ወራት የተመዘገበው የገቢ መጠን፤ ይህንን እቅድ ማሳካት እንደሚቻል “ከወዲሁ አመላካች ሆኗል” ብለዋል አቶ ካሳሁን በትላንቱ መግለጫቸው።
በሩብ ዓመቱ የተገኘው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር “የ980 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ብልጫ ያለው” መሆኑን ሚኒስትሩ አክለዋል። ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከውጪ ንግድ ያስገባቸው ገቢ 1.5 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
“ይህ በሀገር ደረጃ እያደረግን ያለነው የማክሮ ኢኮኖሚክ ሪፎርም ውጤት ማሳየት መጀመሩን ብቻ ሳይሆን የአንድ ጊዜ ውጤት አለመሆኑን [የሚያመለክት] ነው። ተከታታይነት እና ቀጣይነት ያለው ነው” ያሉት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ፤ በ2017 በጀት ዓመት የተመዘገበው ውጤት “በሆነ ጊዜ ላይ የሚቆም” እና “ወፍ ዘራሽ” እንዳልሆነ የሚያሳይ እንደሆነ አብራርተዋል።

መስሪያ ቤታቸው ከሚከታተላቸው የምርት አይነቶች፤ በሩብ ዓመቱ ከእቅዱ 93 በመቶ ገቢ ማግኘቱንም አቶ ካሳሁን በትላንቱ ማብራሪያቸው ጠቁመዋል። የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ክትትል የሚያደርግባቸው ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች መካከል የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬዎች እንዲሁም የብርዕ እና አገዳ ሰብሎች ይገኙበታል።
የቁም እንስሳት፣ የጫት፣ የዕጣን እና ሙጫ የውጪ ንግዶችም እንደዚሁ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ክትትል ስር ያሉ ናቸው። በዘንድሮው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከእነዚህ ምርቶች የተገኘው ገቢ 149 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ከእነዚህ ምርቶች ለማግኘት የታቀደው 180 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፤ የነበረው አፈጻጸም ከእቅዱ 87 በመቶውን ብቻ ያሳካ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።
“በኤክስፖርት ወጪ ንግድ ላይ የምንሰራ ሰዎች፤ ይሄ ጊዜ የወጪ ንግድ የሚቀዛቀዝበት ጊዜ ነው የምንለው። በዓላት የነበሩበት [ነው]። ክረምቱ በራሱ ለትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቅልጣፌ [አስቸጋሪ በመሆኑ] ብዙ ኤክስፖርት የሚነቃቃበት ጊዜ አልነበረም። ግን ውጤቱ በጣም ከፍተኛ እና ከእቅድ በላይ ማሳካት የተቻለበት ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ የዘንድሮ የሩብ ዓመት የወጪ ንግድ አፈጻጸምን አሞካሽተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)