አሜሪካ የዲቪ ሎተሪ ፕሮግራምን አገደች 

የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት ሚኒስትር ክሪስቲ ኖም በተለምዶ “ዲቪ” በመባል በሚታወቀው የፍልሰተኞች የዳይቨርሲቲ ቪዛ ፕሮግራም ላይ እገዳ ጣሉ። ሚኒስትሯ የእገዳ ትዕዛዙን ያስተላለፉት፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።

በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የሌሎች ሀገራት ሰዎች ወደ አሜሪካ የመግባት እና በሀገሪቱ የመኖር ዕድል የሚያገኙበት ይህ ፕሮግራም እንዲታገድ የተወሰነው፤ ባለፈው ቅዳሜ እና ሰኞ በአሜሪካ ሁለት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ከተፈጸመው ግድያ ጋር በተገናኘ ነው ተብሏል።

የአሜሪካ ዲፓርትመንት ኦፍ ሆምላንድ ሴኪዩሪቲ ሚኒስትሯ ክሪስቲ ኖም ይህንኑ የሚያስተጋባ መልዕክት ዛሬ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። በብራውን ዩኒቨርስቲ ተኩስ የከፈተው ግለሰብ በዲቪ ፕሮግራም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መግባቱን በዚሁ መልዕክታቸው የገለጹት ሚኒስትሯ፤ “ይህ ክፉ ግለሰብ ወደ ሀገራችን እንዲገባ በፍጽሙ ሊፈቀድለት አይገባም ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። 

በብራውን ዩኒቨርስቲ ሁለት ሰዎችን በመግደል እና ሌሎች ዘጠኝ ሰዎችን በማቁሰል የተጠረጠረው ፖርቹጋላዊው ክላውዲዮ ኔቬስ ቫለንቴ በፈረንጆቹ 2000 ዓመት በተማሪ ቪዛ ወደ አሜሪካ የገባ ነው። ተጠርጣሪው በ2017 በዲቪ ሎተሪ አማካኝነት በሀገሪቱ ቋሚ ነዋሪ መሆን ችሏል። 

ለዲቪ ሎተሪ መታገድ ምክንያት የሆነው ይህ ግለሰብ፤ ሐሙስ አመሻሽ ላይ በራሱ ላይ በፈጸመው ተኩስ ከቆሰለ በኋላ ሞቶ መገኘቱን ፖሊስ ገልጿል። የሃገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት ሚኒስትሯ በዲቪ ፕሮግራም ምክንያት “አሜሪካውያን ከእንግዲህ በኋላ ጉዳት እንዳይደርስባቸው” ለማረጋገጥ እገዳውን ለአሜሪካ ዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት ማስተላለፋቸውን አስታውቀዋል።

ይህ እገዳ ከ55 ሺህ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች በየዓመቱ በአሜሪካ በቋሚነት ለመኖር ዕድል የሚያገኙበትን ፕሮግራም እንዲቆም የሚያደርግ ነው። በፈረንጆቹ 2025 ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለዲቪ ፕሮግራም አመልክተው እንደነበር የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መረጃ ያመለክታል።

ከእነዚህ አመልካቾች ውስጥ ከልጆቻቸው እና የትዳር አጋሮቻቸው ጋር ተደምረው ዕድለኞች የሆኑ ሰዎች ብዛት 131,060 መሆኑን የመስሪያ ቤቱ መረጃ ያሳያል። ከአፍሪካ የዘንድሮ የዲቪ ዕድለኞች ውስጥ በብዛታቸው መጠን ከአንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃ የያዙት አልጄሪያ፣ ግብጽ እና ሱዳን ናቸው። 

ኢትዮጵያ ዲቪ ባገኙ 3,674 አመልካቾች ብዛት በዚህ የደረጃ ዝርዝር ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ከኢትዮጵያ በፊት ያሉትን ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ የያዙ ሀገራት ኬንያ፣ ሞሮኮ እና ካሜሮን ናቸው። 

የዲቪ ፕሮግራም የእገዳ እርምጃን በመቃወም የህግ ባለሙያዎች በፍርድ ቤት ክስ ይመሰርታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የቪዛ ፕሮግራሙ የተጀመረው በፌዴራል ሕግ በመሆኑ እና የእገዳ እርምጃው ያለ ኮንግረሱ እውቅና የተወሰነ መሆኑ ለክሱ መነሻ እንደሚሆን በዘገባዎቹ ላይ ተመልክቷል።     

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ከዚህ እገዳ በፊትም ቢሆን ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች እና ፍልሰተኞችን ለመገደብ በርካታ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል “አሳሳቢ” ከተባሉ 19 ሀገራት ወደ አሜሪካ የገቡ ዜጎችን ግሪን ካርድ እንደገና መመርመር እና በሺህዎች የሚቆጠሩ የተማሪ ቪዛዎችን መሻር ይጠቀሳሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)