በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወደ ግልገል በለስ ከተማ በመጓዝ ላይ በነበሩ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ ትላንት ማክሰኞ ጠዋት ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ 30 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች እና የአካባቢው የፓርላማ ተወካይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የትላንቱን ጥቃት በተመለከተ መረጃ እንደደረሰው የገለጸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ ክስተቱን ባለሙያ መድቦ በማጣራት ላይ እንደሆነ አስታውቋል።
ድርጊቱ የተፈጸመው በመተከል ዞን፣ ጉባ ወረዳ፣ አይሲድ ቀበሌ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ ላይ እንደሆነ ከትላንቱ ጥቃት የተረፉ ሶስት የዓይን እማኞች ገልጸዋል። የመተከል ዞን የፓርላማ ተመራጭ የሆኑት ዶ/ር መብራቱ የትላንቱ ጥቃት የደረሰው የአይሲድ ቀበሌ ከታለፈ በኋላ ወደ ዳንጉር ወረዳ መግቢያ ላይ በሚገኝ ቦታ ላይ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
ከአሶሳ ወደ ግልገል በለስ ከተማ ይጓዝ በነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ ተሳፍራ እንደነበር የገለጸች አንድ የአይን እማኝ፤ ታጣቂዎች ተኩስ የከፈቱበት ቦታ የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ያለበት አካባቢ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች። እርሷ እና ሌሎች ተሳፋሪዎች መጀመሪያ ላይ የሰሙት ተኩስ፤ በአካባቢው በብዛት የሚገኘው ቀርከሃ ሲቃጠል የሚያወጣው ድምጽ መስሏቸው እንደነበርም አስረድታለች።

“ተኩሱ ሲሰማ ቀርከሃ ነበር የመሰለን። ‘ቀርከሃ ነው፣ ንዳው’ ብለን ነው [ሹፌሩን] ያስነዳነው። ከዚያ በኋላ [ተኩሱ] በረድ አለ። ለካ መኪናውን ለማስቆም አቅደው ነው በረድ አድርገውት የነበረው” ስትል የዓይን እማኟ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ገልጻለች። “[አውቶብሱ የያዘውን] የሰው ብዛት ባላውቅም፤ ሙልት ብለን ነው የሄድነው። ተጠቅጥቀን ማለት ነው። መንገድ ላይ ቁሙ ብለው አስወረዱን” ስትልም በታጣቂዎቹ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ አስታውሳለች።
ታጣቂዎቹ ንብረታቸውን መቀማታቸውን የምትገልጸው የአይን እማኟ፤ አንዱን ሹፌር በመደብደብ ላይ እያሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢው በመድረሳቸው ወደ ተኩስ ልውውጥ መግባታቸውን ተናግራለች። “ስልካችንን ምናምን ቀምተው ከዘረፉን በኋላ ተኙ አሉን። መከላከያ ሲመጣ ሩጡ አሉን። መከላከያዎች ምንም አትሆኑም እያሉ እየተዋጉ ነበር” ስትል የተከሰተውን ገልጻለች።
መነሻውን አሶሳ ከተማ አድርጎ፣ ማንኩሽ ከተማ አድሮ፣ ንጋት 11 ሰዓት ላይ ወደ ግልገል በለስ ከተማ በጉዞ ላይ በነበረ አውቶብስ ተሳፍሮ የነበረ ሌላ ተጓዥም፤ ተመሳሳይ ክስተት እንዳጋጠማቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድቷል። የደንብ ልብስ የለበሱ የታጠቁ ኃይሎች የነበሩበትን አውቶብስ በመክበብ ካስቆሟቸው በኋላ፤ ተሳፋሪዎች በሙሉ እንዲወርዱ አድርገው የፈጸሙትንም ዘርዝሯል።

“ ‘ማንም ሰው እንዳይንቀሳቀስ፣ ውረዱ እና ሰልፍ ያዙ’ አሉ። ሰው ጠቅላላ ወረደ እና ሰልፉን ያዘ። ሁለት ባስ ውስጥ ያለውን ሰው በአንድ በኩል አሰለፉ እና ወደ ጫካ ይዘው ገቡ። ጫካው ውስጥ ያለውን ሰው፤ ኪሳቸው ውስጥ ያለውን ጠቅላላ ሀብታቸውን፣ ስልካቸውን፣ ሰዓት፣ ሀብል፣ ሳይቀር [ወሰዱባቸው]” የሚለው የዓይን እማኙ፤ አብሮት ከነበረ ተሳፋሪ ጋር ለማምለጥ ከውሳኔ ላይ ከደረሰ በኋላ የተከተለው ተኩስ እንደነበር አስረድቷል።
“ከእኔ ጎን የነበረ ልጅ ‘ሄደንም መሞታችን ነው። ብንሮጥም መሞታችን ነው። በካራ ከምንታረድ ግን ሮጠን በጥይት እንመታ’ አለኝ። ጫካው ውስጥ ያለውን ሰው አንድ በአንድ መሬት ላይ አንበርክከው እያለ፤ እኛ ከመኪናው እንደዘለልን ሩጫ ጀመረን። [ይሄኔ] እኛ ላይ ተኩስ ከፈቱ። እነዚያን ያንበረከኩትን ትተው፤ እኛን ተከተሉ” ሲሉ የትላንት ጠዋት ሁኔታውን አብራርቷል።
ታጣቂዎቹ በአውቶብሶች ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎችን እንዲወርዱ በማድረግ ዘረፋ መፈጸማቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስተኛ የዓይን እማኝ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። እኚሁ ተጓዥ እርሳቸው የነበሩበት አውቶብስ ሹፌር በአቅራቢያው እየተፈጠረ ያለውን ነገር በመመልከቱ መሪውን ለማዞር ሙከራ በሚያደርግበት ጊዜ በታጣቂዎች ተኩስ እንደተከፈተበት ገልጸዋል።

ተኩሱን የከፈቱት ታጣቂዎች እንደ ብሬን እና ስናይፐር ያሉ መሳሪያዎችን ታጥቀው እንደነበርም የዓይን እማኙ አመልክተዋል። ሁለተኛው የዓይን እማኝ በበኩላቸው የወታደር ልብስ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይሎች ሲለብሱት የነበረውን የደንብ ልብስ መልበሳቸውን ተመልክቻለሁ ብለዋል።
የመጀመሪያው የዓይን እማኝም ታጣቂዎቹ ወታደራዊ የደንብ ልብስ መልበሳቸውን እና ረጃጅም ቡትስ ጫማዎች መጫማታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች። የመተከል ዞን የፓርላማ ተወካዩ ዶ/ር መብራቱ፤ ጥቃቱን የፈጸመው “የጉሙዝ ነጻ አውጪ ኃይል” የተባለ ቡድን ሳይሆን እንደማይቀር ጥርጣሬያቸውን አጋርተዋል።
በግለሰብ እጅ የማይገኙ የጦር መሳሪያ ታጥቀው ነበር የተባሉት እነዚህ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ፤ ቢያንስ 35 ሰዎች እንደተገደሉ እና ከ50 በላይ ሰዎች እንደቆሰሉ መረጃ እንደደረሳቸው የፓርላማ አባሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ሁለቱ የዓይን እማኞች በበኩላቸው በጥቃቱ ህይወታቸውን ያጡ 30 ሰዎች በአይሲድ ከተማ በሚገኘው ገብርኤል ቤተክርስቲያን በትላንትናው ዕለት መቀበራቸውን አመልክተዋል።

የዓይን እማኞቹ በጥቃቱ ከተገደሉት በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ቆስለው መመልከታቸውን አክለዋል። ሁለተኛው የዓይን እማኝ፤ ቁስለኞቹ በሁለት ተሽከርካሪዎች ተጭነው ወደ ማንኩሽ ጤና ጣቢያ ሲወሰዱ ማየቱንም አክሏል። በጉባ ወረዳ በሚገኘው ማንኩሽ ጤና ጣቢያ የሚሰሩ አንድ የጤና ባለሙያ ይህንኑ አረጋግጠዋል።
በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎች ወደ ህክምና ተቋሙ መምጣት የጀመሩት ትላንት ከሰዓት ስምንት ሰዓት አካባቢ እንደነበርም የጤና ባለሙያው ገልጸዋል። ከተጎጂዎቹ መካከል ሶስቱ ወደ ህክምና ተቋሙ ሳይደርሱ በመንገድ ላይ እና ሌሎች ሶስት ግለሰቦች ደግሞ በጤና ጣቢያው ህክምና እየተከታተሉ ሳለ ህይወታቸው ማለፉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
ለዘጠኝ ተጎጂዎች በጤና ጣቢያው አሁንም ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን የገለጹት እኚሁ የጤና ባለሙያ፤ ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ ለተሻለ ህክምና ወደ አሶሳ እና ፓዌ ሆስፒታሎች እንዲሄዱ ሪፈር የተጻፈላቸው እንደሆኑ ጠቁመዋል። ሆኖም በአካባቢው ባለው መንገድ መዘጋት ምክንያት ተጎጂዎቹን ወደተባሉት ሆስፒታሎች መውሰድ አለመቻሉንም አክለዋል።
የማንኩሽ ጤና ጣቢያ የሚገኝበት እና የትላንቱ ጥቃት የተፈጸመበት የመተከል ዞን፤ ባለፉት ዓመታት መሰል ክስተቶችን ሲያስተናግድ የቆየ ነው። በእነዚህ ዓመታት ከዞኑ ነዋሪዎች በተጨማሪ በአካባቢው ባለስልጣናት እና በስፍራው በተሰማሩ የጸጥታ ኃይሎች ላይ በሚሰነዘሩ ጥቃቶች በርካቶች ተገድለዋል።
የተወሰኑትን ግድያዎች መንግስታዊው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም የሆነው ኢሰመኮ በየጊዜው በሚያወጣቸው መግለጫዎች ላይ አካትቷቸዋል። የትላንቱን ጥቃት በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበለት የኮሚሽኑ የአሶሳ ጽህፈት ቤት፤ ስለ ጉዳዩ መረጃ እንደደረሰው እና ክስተቱን ባለሙያ መድቦ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
ጽህፈት ቤቱ በክትትሉ የደረሰበትን ሪፖርት አጠቃሎ ወደ ዋና መስሪያ ቤት እንደሚልክም አስታውቋል። በትላንትናው ዕለት ስለ ተፈጸመው ጥቃት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለመተከል ዞን እና ለጉባ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ጥያቄዎች ብናቀርብም፤ ባለስልጣናቱ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ጥረታችን ሳይሳካ ቀርቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































