የአዲግራት ከተማ ነዋሪ የሆነው የ27 ዓመቱ ወጣት ጎይቶም ገብረስላሴ*፤ ከመቐለ እና ከመኖሪያ ከተማው የሚገዛቸውን ቡና እና በርበሬ ወደ ዛላንበሳ ከተማ እየወሰደ በመሸጥ የሚተዳደር ነው። ጎይቶም በትግራይ ክልል እና በኤርትራ ድንበር ወደምትገኘው ዛላንበሳ በሳምንት ሁለት ጊዜ እየተመላለሰ የንግድ ስራውን ሲያከናወን፤ ከዚህ ቀደም የከፋ ችግር አልገጠመውም።
በዚሁ ከተማ በሚገኝ ሻይ ቤት ውስጥ ከስድስት ጓደኞቹ ጋር ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ግንቦት 12፤ 2018 ረፋድ ተቀምጦ እየተጫወተ ባለበት ያጋጠመው ክስተት ግን ያልጠበቀው ነበር። በዚሁ ዕለት እርሱ “ቲዲኤፎች” ብሎ የሚጠራቸው የትግራይ ሰራዊት አባላት ድንገት ወደ ሻይ ቤቱ ተከታትለው ይገባሉ።
ዱላ እና መሳሪያ የያዙት እነዚህ የሰራዊት አባላት፤ ወደ ሻይ ቤት ከገቡ በኋላ ወጣቶቹን ወደ ውጭ እንዲወጡ ትዕዛዝ እንደሰጧቸው ጎይቶም ይናገራል። ትዕዛዙን አልቀበል ያሉት ወጣቶች ከሰራዊቱ አባላት የገጠማቸው ምላሽ “ድብደባ” እንደነበርም ጎይቶም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።

እርሱን ጨምሮ በዚህ መልኩ ከየቦታው የተያዙ ሰዎች እስከ ዘጠኝ ሰዓት በአንድ ቦታ እንዲቆዩ ከተደረጉ በኋላ በቅጥቅጥ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች በመጫን ሃይቅ መስሃል ወደ ተባለ ቦታ መወሰዳቸውን ጎይቶም ያስረዳል። በአውቶብሶቹ ተሳፍረው የነበሩት አብዛኞቹ ወጣቶች እንደሆኑ እና ቁጥራቸው በግምት 70 እንደሆኑም አክሏል።
በትግራይ ሰራዊት አባላት ታጅበው የተወሰዱት እነዚህ ወጣቶች፤ መዳረሻቸው የሆነው ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ ነበር። ወታደራዊ ማሰልጠኛው ሁለት ሰፊ አዳራሾች ያሉት እንደሆነ የሚናገረው ጎይቶም፤ በእነዚህ ውስጥ ከተለያዩ ቦታዎች የተያዙ በግምት 700 የሚሆኑ በግዳጅ የተመለመሉ ሰዎች እንደነበሩባቸው መመልከቱን ይገልጻል።
በማሰልጠኛ ጣቢያው ለአራት ቀናት የቆየው ጎይቶም፤ ሁሉም በአፈሳ የተያዙ ሰዎች ከአዳራሾቹ 10 ደቂቃ ገደማ የሚያስጉዝ ቦታ ላይ ተወስደው በየዕለቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሰሩ ይገደዱ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። ስልጠናውን ለወጣቶቹ የሚሰጡት አዛዦች “ጠላት ሊወረን ነው። ጠላት ሊመጣብን ነው። እየተሰባሰበ ነው። ሌላ ዳግማይ ጄኖሳይድ ሊፈጽሙብን ነው” ይሏቸው እንደነበርም ያስታውሳል።

በዚህ መልክ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ ከተደረጉ ሰዎች መካከል ዕድሜያቸው በግምት እስከ 50 የሚደርሱ እንዳሉበትም ጎይቶም ታዝቧል። ከየቦታው የታፈሱት ሰዎች በየዕለቱ እንዲመገቡ የሚሰጣቸው ሁለት ዳቦ እና ሻይ እንደነበር የሚገልጸው ጎይቶም፤ ጸጉራቸውን በግዳጅ እንዲላጩ መደረጋቸውንም አመልክቷል።
ጎይቶቶም በዚህ ማሰልጠኛ የነበረው ቆይታ በአጭር የተቋጨው፤ በወንድሞቹ አማካኝነት ለአንድ የጣቢያው ጠባቂ ገንዘብ ከተከፈለ በኋላ እንደነበር ያስረዳል። ወንድሞቹ ከዛላንበሳ ከተማ መያዙን ከሰሙ በኋላ ያለበትን ቦታ አፈላልገው እንደደረሱበት ጎይቶም ይናገራል። እርሱን ከወታደራዊ ማሰልጠኛ ለማስለቀቅም፤ ለአንደኛው የጣቢያው ጠባቂ 26 ሺህ ብር መክፈላቸውን እንደነገሩትም ያትታል።
በዚሁ ጠባቂ አማካኝነት ከማሰልጠኛው እንዲያመልጥ የተመቻቸለት ጎይቶም፤ ባለፈው እሁድ ምሽት ሁለት ሰዓት ገደማ ከጣቢያው ከወጣ በኋላ በጨለማ ለሰዓታት መጓዙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። በመንገዱ ላይ ከጅቦች በስተቀር ሌላ እክል ያላጋጠመው ወጣቱ፤ ከአራት ሰዓታት በኋላ የእግር ጉዞ በኋላ አጉላዕ ከተማ ደርሷል።

ከመቐለ ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ከዚህ ከተማ ወደ መኖሪያው አዲግራት የተመለሰው ጎይቶም፤ ዳግም አፈሳን በመፍራት የዛላንበሳ ንግዱን ሙሉ በሙሉ ማቆሙን ይገልጻል። ጥሎት በመጣው ወታደራዊ ማሰልጠኛ የቀሩት ጓደኞቹ፤ ባለፉት ቀናት መሳሪያ መተኮስ እንዲለማመዱ እየተደረጉ መሆኑንም መስማቱንም አክሏል።
እንደ ጎይቶም ሁሉ በትግራይ ክልል ያለው የግዳጅ አፈሳ ድንገት ያጋጠመው የ26 ዓመት ወጣት፤ ከያዙት ሰዎች ባመለጠበት ወቅት ሌላ ወጣት በተኩስ ሲገደል መመልከቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። ይህ ወጣት ከአቢ ዓዲ ወጣ ብሎ በምትገኝ አባጊባ በተባለች ስፍራ በወርቅ ፍለጋ ስራ ላይ የተሰማራ ነው።
ባለፈው ሰኞ ግንቦት 17፤ 2018 እንደተለመደው በዚሁ ስራው ላይ ነበር። በዚሁ ዕለት ከሰዓት 10 ሰዓት ገደማ ወደ ስፍራው የመጡ የትግራይ ክልል ሰራዊት አባላት እርሱን ጨምሮ በአካባቢው የነበሩት ወደ 400 ገደማ የሚሆኑ ወጣቶችን አስገድደው በአይሱዙ ተሽከርካሪዎች ጭነው መውሰዳቸውን ይገልጻል።

“እዚያ ያለው ወጣት በዚህ ስራ ስድስት እና ሰባት ቤተሰብ ነው የሚያስተዳድረው። ወርቅ በሚወጣበት ጉድጓድ ላይ የነበረውን ወጣት በሙሉ ነው አፍሰው የወሰዱት። የመጡት ከሁለት አርሚ ነው” ሲል በግዳጅ ስለወሰዷቸው ታጣቂዎች ማንነት ያስረዳል። ተሽከርካሪዎቹ ሌሎች ተጨማሪ የታፈሱ ወጣቶችን እና ምግብ ለመጫን ወርቃምባ በተባለ ቦታ ላይ ሲቆም፤ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን ከመኪናው በመዝለል ማምለጡን ይናገራል።
በዚህ ጊዜ አብሯቸው ለማምለጥ የሞከረ ሌላ ወጣት፤ እነርሱን ካጀቧቸው የትግራይ ሰራዊት አባላት በተተኮሰበት ጥይት ሲገደልም ተመልክቷል። በዚህ ሁኔታ ያመለጠው ወርቅ ቆፋሪ ለስምንት ሰዓት ገደማ በእግር ከተጓዘ በኋላ ትላንት ሐሙስ ጠዋት አበርገሌ ከተማ መግባት መቻሉን ገልጿል።
ከእርሱ ጋር ታፍሰው የነበሩ እና የማምለጥ ያልቻሉ ጓደኞቹ፤ በዕዳጋ ሐሙስ እና በዕዳጋ ዓርቢ አካባቢ አዲስ በተከፈቱ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ውስጥ እንደሚገኙ መረዳቱንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። ከአፈሳ ያመለጡ ወጣቶች ያሉባቸው አካባቢዎች ላይ ወላጆች እና ቤተሰቦች “በምትክነት እየታሰሩ” መሆናቸውን መስማቱንም አክሏል።

የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላው እና አፈሳው፤ በአዲግራት፣ አድዋ፣ አክሱም እና ሽረ ከተሞች እንዲሁም በአካባቢው በሚገኙ የገጠር ከተማዎች አሁንም በመካሄድ ላይ መሆኑን የዓይን እማኞች፣ የትግራይ ክልል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እየገለጹ ይገኛሉ። ከሽረ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ላይ በምትገኘው እንዳባጉና ነዋሪ የሆነ የ36 አመት ጎልማሳ የካሜራ ባለሙያ ይህንኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል።
የካሜራ ባለሙያው እርሱ በሚኖርበት ከተማ ባለፈው ሳምንት አፈሳ ተካሄዶ እንደነበር ይገልጻል። አፈሳውን የሚያካሄዱት የትግራይ ክልል ሰራዊት አባላት እንደሆኑ የጠቆመው የእንዳባጉና ነዋሪው፤ ይህንኑ የለየው በለበሱት አፈርማ የደንብ ልብሳቸው አማካኝነት መሆኑን ያስረዳል።
አፈሳው የሚደረገው “በጥናት” እንደሆነ የሚናገረው ነዋሪው፤ ለወታደራዊ ምልመላ የሚፈለገው “ከዚህ በፊት የሰራዊቱ አባል መሆን አለመሆኑ” ላይ አስቀድሞ ማጣራት እንደሚደረግ ያብራራል። ይህንን መሰረት በማድረግ “በሌሊት ቤት ለቤት በመዞር”፤ ተፈላጊዎቹን ሰዎች ከያዙ በኋላ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚወስዷቸውም ይገልጻል።

“በጎረቤት ላይ ተደርጓል። [ከዚያ በኋላ] እነሱን ማግኘት አልቻልንም። ወዴት እንደወሰዷቸው መረጃ የለንም” ሲል የእንዳባጉናው ነዋሪ የዓይን እማኝነቱን ሰጥቷል። ባለፈው እሁድ ይህን የለሊት አፈሳ የተመለከተው ጎልማሳ፤ ከአክስቱ ልጅ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ከተማቸውን ለቅቀው ወደ ሽረ ለመጓዝ መወሰናቸውን ተናግሯል።
ሁለቱ የእንዳባጉና ነዋሪዎች የተወሰነ ኪሎ ሜትር በእግር ከተጓዙ በኋላ በሞተር ሳይክል የሚጭናቸው ሰው አግኝተው ለሊት 10 ሰዓት ገደማ ሽረ ከተማ ግብተዋል። “የአክስቴ ልጅ አለ። ከእሱ ጋር ሆነን ወደ ሽረ ወጣን። ሽረ ከእሱ ጋ ሆነን ሆቴል ተደብቀን ነው ያለነው። ቤት ብንሆን ምን እንደሚመጣብን አናውቅም” ሲል የ36 አመቱ ጎልማሳ አሁን ያሉበትን ሁኔታው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድቷል።
የግዳጅ አፈሳውን የሸሸው ይህ ጎልማሳ የሽረ ከተማ ቆይታውም አልስተማመነውም። በእንዳባጉና ከተማ የምትገኘውን ባለቤቱን ወደ ኋላ ትቶ ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን ለመሄድ ትኬት ቆርጦ ቀኑን እየተጠባበቀ ነው።

በትግራይ ክልል ወጣቶች በግዳጅ ምልመላ እየተደረገባቸው መሆኑን የሚያሳዩ “ብዛት ያላቸው ጥቆማዎች” እንደደረሱት ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ የተሰኘው ሀገር በቀሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አስታውቋል። የድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መብርሂ ብርሃነ፤ በክልሉ “የግዳጅ ምልመላዎች” እንዳሉ እና “ተይዘው የተለቀቁ ሰዎች እንዳሉ” የሚያመለክቱ ጥቆማዎች መምጣት የጀመሩት ካለፈው ሁለት ሳምንት ወዲህ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
እነዚህ ጥቆማዎች ከሚያደርሷቸው ውስጥ የተመልማዮቹ ቤተሰቦች እንደሚገኙበት የጠቀሱት አቶ መብርሂ፤ ምልመላዎቹ በተለይ በገጠር ቀበሌዎች ላይ የሚደረጉ መሆናቸውን መረዳታቸውን ይገልጻሉ። በ16 ዓመት ታዳጊዎች ላይ ጭምር የግዳጅ ምልመላ እንደተደረገባቸው ጥቆማ እንደደረሳቸው የሚናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ይህ አይነቱ ድርጊቱ “ወንጀል መሆኑን” ያስገነዝባሉ።
ድርጅታቸው ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ ድርጊቱ መፈጸሙን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ከተለያዩ አካባቢዎች እያሰባሰበ እንደሚገኝ አመልክቷል። አቶ መብርሂ እነዚህን መረጃውን በማጠናቀር፤ ድርጅታቸው የምርመራ ውጤቱን የያዘ ሪፖርት በቅርቡ ይፋ ያደርጋል ብለዋል።

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው ብሄራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ ፓርቲ (ባይቶና) ፕሬዝዳንት አቶ ክብሮም በርሀ፤ በክልሉ የሚደረገው የወጣቶች አፈሳ “በግልጽ” እና “ሁሉም ሊያየው” በሚችል መልኩ እየተከናወነ የሚገኝ ነው ባይ ናቸው። ቀደም ብለው በነበሩት ጊዜያት በክልሉ ተመሳሳይ የወጣቶች አፈሳ ቢኖርም፤ በዚህ ደረጃ የደረሰ እንዳልነበርም የፓርቲው ፕሬዝዳንት ይገልጻሉ።
በትግራይ ዳግም የክልሉ ወጣቶች መታፈስ የጀመሩት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ወደ ስልጣን ከተመለሱ በኋላ መሆኑንም አቶ ክብሮም ያስረዳሉ። ህጋዊ ዕውቅናው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ ባለፈው ዓመት የተሰረዘውን ህወሓት በሊቀመንበርነት የሚመሩት ዶ/ር ደብረጽዮን፤ የትግራይ ክልልን የመምራት ኃላፊነት በድጋሚ የተረከቡት ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ነበር።
በጥቅምት 2013 ዓ.ም በትግራይ ከተቀሰቀሰው ጦርነት በፊት የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድሩ የነበረው ዶ/ር ደብረጽዮን፤ ወደ ስልጣናቸው እንዲመለሱ ሹመት የሰጣቸው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ነው። ከጦርነቱ በፊት በተካሄደ አወዛጋቢ ምርጫ የተመረጠው ይህ ምክር ቤት፤ ስድስት ዓመት ካስቆጠረው የስራ ዘመኑ በኋላ ወደ ስራ እንዲመለስ የተደረገው በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።
ይኸው ምክር ቤት ያጸደቀው የዶ/ር ደብረጽዮን ሹመት፤ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ተቋቁሞ ትግራይን ሲመራ የቆየው ጊዜያዊ አስተዳደር ህልውና እንዲያከትም ምክንያት ሆኗል። በፌደራል መንግስት ይሁንታ የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መፍረስ፤ “የትግራይ ክልልን ዳግም ወደ ጦርነት ይመልሳል” የሚል ስጋት አሳድሮ ቆይቷል።
የባይቶና ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ክብሮም፤ አሁን በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው የወጣቶች አፈሳ፤ ህወሓት “ለሌላ የጦርነት ዝግጅት እና እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የሚያሳይ ነው” ይላሉ። የሚታፈሱት ወጣቶች ከዚህ ቀደም “የትግራይ መከላከያ ኃይል (TDF)” አባላት መሆናቸው እንዲሁም የተክለ ሰውነት ሁኔታቸው ለወታደራዊ ስልጠና የተመቸ መሆን አለመሆኑ የሚገመገም መሆኑንም ያስረዳሉ።
በየቤቱ በሚካሄደው የቤት ለቤት የወጣቶች አፈሳ ወቅት፤ ልጆች በሌሉባቸው ቦታዎች የቤተሰብ አባላቶቻቸው እስር እንደሚገጥማቸውም አቶ ክብሮም ይገልጻሉ። የግዳጅ አፈሳው “የተባባሰባቸው” እና “በከፍተኛ ሁኔታ ያለባቸው” አድዋ እና አክሱም ከተሞች እንዲሁም የገጠር አካባቢዎች እንደሆኑ የባይቶና ፓርቲ ተናግረዋል።
“መለኪያ አላቸው። የእኛ የሚሉት አካባቢ አለ። እሱን መሰረት አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት። ሌላው አካባቢ ‘ተቃውሞ ሊበረታ ይችላል’ ብለው ያስባሉ። ግን ደግሞ እዚያም አካባቢ የበረታ ተቃውሞ እየገጠማቸው ነው ያለው”
“መለኪያ አላቸው። የእኛ የሚሉት አካባቢ አለ። እሱን መሰረት አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት። ሌላው አካባቢ ‘ተቃውሞ ሊበረታ ይችላል’ ብለው ያስባሉ። ግን ደግሞ እዚያም አካባቢ የበረታ ተቃውሞ እየገጠማቸው ነው ያለው” ሲሉ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካብቢዎች ያለውን ሁኔታ አቶ ክብሮም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላውን የሚቃወም እንቅስቃሴ መኖሩ፤ አፈሳውን ቀላል እንዳላደረገውም የባይቶና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ያክላሉ። የግዳጅ አፈሳውን ለማከናወን በሚመጡ የሰራዊት አባላት እና በወጣቶች መካከል “የተኩስ ልውውጥ” እንደሚካሄድ የተናገሩት አቶ ክብሮም፤ በዚህም ሳቢያ በሁለቱም ወገን የሞቱ ሰዎች እንዳሉ መረጃው እንዳላቸው ገልጸዋል።
በቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ (ስምረት) ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ ይህንኑ የሚያጠናክር መረጃ አጋርቷል። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው “ኋላ ቀር” ሲል የጠራው ቡድን፤ “ለጦርነት አንሰለፍም” ብለው የተቃወሙ ወጣቶችን በተለያዩ የትግራይ ወረዳዎች “በጅምላ እያሰረ”፣ “እያሰቃየ” እና “የጥይት እራት እያደረጋቸው ነው” ሲል ወንጅሏል።

ስምረት ፓርቲ ከመላው ትግራይ የታፈሱ ወጣቶች “ወደማይታወቁ ማዕከላት እየተወሰዱ ጥብቅ ወታደራዊ ጥበቃ” እየተደረገባቸው መሆኑን ማረጋገጡንም በመግለጫው ጠቅሷል። ድርጊቱን በመቃወም ድምጻቸውን ያሰሙ እናቶችን ሳይቀር “በሰደፍ ከመምታት” እስከ “ማሰር” የደረሰ እርምጃ ሲወሰድባቸው መታየቱንም ፓርቲው አመልክቷል።
በእዚህ የወጣቶች አፈሳ ላይ የተሳተፉ አካላት እና ግብረ-አበሮቻቸው ወደፊት የሚመጣውን “ከባድ ተጠያቂነት” ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ፓርቲው “አሳፋሪ” ሲል ከጠራው ድርጊት “በአስቸኳይ” እንዲታቀቡም በጥብቅ አሳስቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[ * በዚህ ዘገባ መጀመሪያ ላይ የጠቀስነው ወጣት ስም ለደህንነቱ ሲባል የተቀየረ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን። የሌሎቹንም የዓይን እማኞች ስም በተመሳሳይ ምክንያት ከመግለጽ ታቅበናል።]





























