🔴 የምርጫ 2018 የቀጥታ ዘገባ

ዛሬ ሰኞ ግንቦት 24፤ 2018 የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ዕለት ነው። የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች ከተለያዩ ስፍራዎች የሚልኳቸው መረጃዎች፣ ፎቶዎች እንዲሁም በዝግጅት ክፍላችን የተጠናቀሩ ዘገባዎችን በቀጥታ እናቀርባለን።


7:10 በዛሬው ዕለት በተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ፤ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ 40 ሚሊዮን መራጮች ድምጽ መስጠታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ተናገሩ። የምርጫ ቆጠራ ውጤቱ ዛሬ በማይጠናቀቅባቸው ቦታዎች፤ በነገው ዕለት እንደሚከናወንም ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

ሜላትወርቅ ይህን የገለጹት ዛሬ ሰኞ ግንቦት 24፤ 2018 ሲካሄድ የዋለውን ምርጫ መጠቃለል በተመለከተ ለሊት ሰባት ሰዓት ገደማ በሰጡት መግለጫ ነው። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ በዚሁ መግለጫቸው በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ስላልተካሄደባቸው እና ስለተቋረጠባቸው አካባቢዎች በቅድሚያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዋና ሰብሳቢዋ ዛሬ እኩለ ቀን ገደማ በሰጡት መግለጫ በ143 የምርጫ ጣቢያዎች፤ በጸጥታ ችግር ምክንያት የድምጽ መስጠት ሂደቱ አለመካሄዱን ገልጸው ነበር። ሜላትወርቅ በዚሁ መግለጫቸው ለማሳያነት ከጠቀሷቸው መካከል በአማራ ክልል በሚገኘው የኩታ በር ምርጫ ክልል 15 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ድምጽ መስጠት መቻሉን አስታውቀዋል። 

በዚሁ ምርጫ ክልል በሚገኙ አራት የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ግን ምርጫ ሳይከናወን መቅረቱን ተናግረዋል። በመኮሳቺ እና ቀርሳ ምርጫ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ ባለመሻሻሉ በተመሳሳይ ሁኔታ የድምጽ መስጠት ሂደቱ አለመካሄዱን አብራርተዋል።

ዝርዝር ዘገባውን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://ethiopiainsider.com/2026/18192/
  


6:50 በአዲስ አበባ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ምርጫ ክልል 17፣ ወረዳ 13፣ ላስታ ስላሴ ዕድር ምርጫ ጣቢያ የድምፅ ቆጠራ እስከ ለሊት 6 ሰዓት ከ50 ደቂቃ አልተጀመረም። ከምሽቱ 4 ሰዓት በኋላ የመራጮች ቁጥር በጣም አነስተኛ ቢሆንም፤ የምርጫ ጣቢያው እስከ እኩለ ለሊት ሰዓት ድረስ ክፍት ሆኖ ቆይቷል።

በዚህ ምርጫ ጣቢያ 1,300 መራጮች ተመዝግበዋል። በዲጂታል በታብሌት የተመዘገቡ 14 መራጮች መዝገብ ላይ ባለመገኘታቸው፤ በድጋሚ በስክሪፕቶ እየተመዘገቡ እንዲመርጡ መደረጉን የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ለዘጋቢያችን ገልጾለታል።

እነዚህን መራጮች ጨምሮ እስከ ምሽት አምስት ሰዓት ድረስ  በአጠቃላይ ድምጽ የሰጡ መራጮች ብዛት  924 መሆናቸው የጣቢያው የመዝገብ ሹም መረጃ ያመለክታል። በምርጫ ጣቢያው አንድ ድምጽ ያልተሰጠበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የድምፅ መስጫ ወረቀት መጥፋቱን ምርጫ አስፈጻሚው ለዘጋቢያችን ነግረውታል።

በዚህ ምርጫ ጣቢያ ሶስት የክልል ምክር ቤት እና አንድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሮጆ ጥቅም ላይ ውሏል። በምርጫ ጣቢያው ሂደቱን ለመታዘብ የተገኘው ብልፅግና ፓርቲ ታዛቢ ብቻ መሆኑን ዘጋቢያችን ተመልክቷል።

በጣቢያው ከ4 ሰዓት ከ50 ደቂቃ በኋላ መራጮች ባለመምጣታቸው፤ ምርጫ አስፈጻሚዎች እራት ሲበሉ እና ቡና ሲጠጡ አምሽተዋል። የጸጥታ ኃይሎች ምርጫ ጣቢያው ባዶ በመሆኑ እና መራጮቾ ባለመኖራቸው ወደ ጣቢያው በተደጋጋሚ ጊዜ እየገቡ ሲወጡ ዘጋቢያችን ታዝቧል።


6:30 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምጽ መስጠት ሂደቱን ያራዘመው እስከ ለሊቱ ስድስት ሰዓት ቢሆንም፤ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ሰሚት ፍየል ቤት አካባቢ መራጮች አሁንም ሰልፍ ላይ ናቸው። በምርጫ ክልል 17 ወደሚገኘው ሁንዳፍ ጀርባ ምርጫ ጣቢያ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ ያቀኑ መራጮች እኩለ ለሊት ካለፈ ግማሽ ሰዓት ተቆጥሮም፤ ድምጻቸውን ለመስጠት ወረፋ እየጠበቁ ነው።

እነዚህ መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያው ቀን ላይ ቢመጡም፤ ሰልፉ ረጅም በመሆኑ ለመመለስ ተገድደው ነበር። የመራጭ ብዛት ይቀንሳል ብለው ባሰቡበት ምርጫ ቦርድ ባራዘመው ጊዜ ላይም ግን በወረፋ ሰዓታት እንዲጠብቁ ሆነዋል።


4:07 የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ በአዲስ አበባ ከተማ፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 6፣ በሚገኘው የግንፍሌ አናጺ እድር ቤት ምርጫ ጣቢያ ያለውን ሁኔታ ለመመልከት ከምሽቱ 4 ሰዓት ገደማ ተገኝታ ነበር። ዘጋቢዋ ለደቂቃዎች በስራው በነበራት ቆይታ፤ ከምርጫ አስፈጻሚ እና ታዛቢዎች ውጭ በምርጫ ጣቢያው ውስጥ መራጭ አልተመለከተችም።

ይህንኑ በፎቶ አስደግፎ ለመዘገብ በሞከረችበት ወቅት፤ የብልጽግና ፓርቲ ሁለት ታዛቢዎች ፎቶግራፍ እንዳታነሳ ከልክለዋታል። ታዛቢዎቹ “መራጭ በሌለበት ሁኔታ፣ ባዶ ቤት መቅረጽ እና ፎቶ ማንሳት የፈለጋችሁት ለምንድን ነው?” ሲሉ ተቃውሞ የተቀላቀለበት ጥያቄ አቅርበዋል።

ዘጋቢያችን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጣትን የዘገባ ፍቃድ (ባጅ) በማሳየት እና የምትሰራበትን መገናኛ ብዙሃን በመጥቀስ ለማስረዳት ብትሞክርም፤ ታዛቢዎቹ ግን የተቋሙን ስም ሰምተው እንደማያውቁ በመጥቀስ በክልከላቸው ጸንተዋል።

በምርጫ ጣቢያው የነበሩት የኢዜማ የምርጫ ታዛቢ ግን ራሳቸው ፎቶ መነሳት እንደሚፈልጉ በመግለጽ የምርጫ አስፈጻሚውን ማብራሪያ ጠይቀዋል። የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚ “በህጉ መሰረት ፎቶግራፍ ማንሳት እንደሚቻል” ማስገንዘቢያ ለመስጠት ቢሞክሩም፤ የገዢው ፓርቲ ታዛቢዎች ግን በዚህም ሳይስማሙ ቀርተዋል።

ደቂቃዎች ከፈጀ ክርክር በኋላ ግን አንደኛው የብልጽግና ፓርቲ ታዛቢ ፍቃደኛ መሆኑን በመግለጽ ሀሳባቸውን ቀይረዋል። ቀሪው የገዢው ፓርቲ ታዛቢ በእምቢታቸው በመጽናታቸው፤ ዘጋቢያችን  በእድር ቤቱ ግቢ ውስጥ የሚገኘውን የመራጮች መቆያ ቦታ ብቻ በፎቶ ለማንሳት ተገድዳለች።


2:50 የግል ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ አብርሃም ጥላሁን በአዲስ አበባ ከተማ፣ በቦሌ እና ከፊል ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ሆነው ቀርበዋል። በቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 05፣ በምርጫ ክልል 24 በሚገኘው 40/60 ምርጫ ጣቢያ ላይ ያለውን የድምጽ አሰጣጥ ሁኔታ ለመመልከት በመጡበት ወቅት ከ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል።

አቶ አብርሃም በዲጂታል የተመዘገቡ መራጮች ላይ መጉላላቶች መከሰቱን በማንሳት፤ ይህ አሰራር “መሻሻል” እንደሚገባው አሳስበዋል። “ሰው ጠዋት 12 ሰዓት ወጥቶ 8፣ 9፣ 10 ሰዓት ድረስ እየጠበቁ የነበሩበት፣ የተጉላሉበት አለ” ያሉት የግል ተወዳዳሪው፤ በምሽት የተገኙበትን የምርጫ ጣቢያ ለዚህ በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

በዚህ ምርጫ ጣቢያ አንድ ሺህ መራጮች የተመዘገቡ ቢሆንም፤ እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ገደማ ድረስ ግን ድምጽ የሰጡት 500ዎቹ ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል። ይህን ቁጥር ለዘጋቢዎቻችን ያረጋገጡት የጣቢያው የምርጫ አስፈጻሚዎች፤ በሰልፍ ላይ ያሉትን በርካታ መራጮች በቀረው ጊዜ ለማስተናገድ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል።


2:30 በአዲስ አበባ ከተማ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 2 በሚገኘው በትለምልም እድር ቤት ምርጫ ጣቢያ የተመዘገቡ መራጮች ብዛት 1,500 ነው። በዚሁ ምርጫ ጣቢያ እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ ድምጽ የሰጡ ሰዎች ቁጥር 1,200 መድረሱን የጣቢያው ምርጫ አስፈጻሚ ለዘጋቢያችን ነግረዋታል።

ወደ ምርጫ ጣቢያው የሚመጡ መራጮች ቁጥር በመቀነሱ እና የቀሩትም 300 ገደማ በመሆናቸው፤ የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚ የድምጽ ቆጠራ ሂደቱን ለመጀመር ለምርጫ ክልል አስተባባሪ ጥያቄ ሲያቀርቡ ዘጋቢያችን ተመልክታለች። ሆኖም የቦርዱ የስራ ኃላፊዎች ለመምረጥ የተመዘገቡት የመራጮች ቁጥር እስኪሞላ ድረስ መቆየት እንዳለባቸው ለምርጫ አስፈጻሚው ምላሽ ሰጥተዋቸዋል።

ይህን ተከትሎም ምርጫ ቦርድ የድምጽ መስጫ ሰዓቱን እስከራዘመበት ለሊት ስድስት ሰዓት ድረስ፤ የምርጫ ጣቢያው ክፍት ሆኖ ለመቆየት ተገድዷል።


2:10 የድምጽ መስጠት ሂደቱ እስከ ለሊት ስድስት ሰዓት እንዲቀጥል መወሰኑን ተከትሎ፤ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኝ ምርጫ ጣቢያ የተገኙ ዘጋቢዎቻችን በርካታ መራጮች ወረፋ ሲጠብቁ ተመልክተዋል። ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላም ድምጽ ሰጪ በብዛት የሚታይበት ይህ የምርጫ ጣቢያ፤ በምርጫ ክልል 28 የሚገኝ ነው።

በወንድይራድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተቋቋመው በዚህ ምርጫ ጣቢያ የተመዘገቡ መራጮች ብዛት 1,500 ነው። በምርጫ ጣቢያው ተራቸውን በሚጠብቁ መራጮች መካከል ቅድሚያ ድምጽ ለመስጠት በሚል “አለመግባባት” ተፈጥሮ እንደነበር ዘጋቢዎቻችን ታዝበዋል።

በጣቢያው ቅጽር ግቢ እና በአቅራቢያው ከአዲስ አበባ ፖሊሶች በተጨማሪ የአካባቢው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ ተስተውለዋል።


1:02 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 24፤ 2018  ሲያከናወን የዋለውን የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ፤ ድምጽ የመስጠት ሂደት ባልተጠናቀቀባቸው ጣቢያዎች ላይ እስከ እኩለ ለሊት ድረስ ማራዘሙን አስታውቋል። ቦርዱ ምሽቱን ባወጣው መግለጫ፤ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው በሥምሪት ላይ ያለው የመስሪያ ቤቱ የክትትል ቡድን ያቀረበለትን ሪፖርት ከተመለከተ በኋላ መሆኑን ገልጿል።

በህግ የተቀመጠው የምርጫ ማጠናቀቂያ ሰዓት መድረሱን ተከትሎ ቦርዱ ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ፤ በምርጫ ጣቢያዎች በሰልፍ ላይ የሚገኙ መራጮች ድምጽ ሰጥተው እስኪያጠናቀቁ ድረስ የምርጫ ሂደቱ እንደሚቀጥል አስታውቆ ነበር። በ2011 ዓ.ም የወጣው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና እና የስነ ምግባር አዋጅ፤ ምርጫ ጣቢያዎች ህጉን ተከትለው ቢዘጉ እንኳ “በምርጫ ጣቢያ ድምጽ ለመስጠት በመጠባበቅ ላይ ያሉ መራጮች ድምጽ መስጠት እንዳለባቸው” ይደነግጋል።

ምርጫ ቦርድ “ለምርጫው ነጻ እና ፍትሃዊነት ይበልጥ ያሰፍናል ብሎ ካመነ” የድምጽ መስጫ ሰዓቱን መራዘም እንደሚችልም በዚሁ አዋጅ ስልጣን ሰጥቶታል። ቦርዱ በዚህ መሰረት ምርጫውን እስከ ለሊት ስድስት ሰዓት ማራዘሙን ከማስታወቁ ጎን ለጎን፤ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ ቆጠራ ሂደት እንዲከናወን ማሳሰቢያ ሰጥቷል።


12፡ 07 በአዲስ አበባ ከተማ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 03፣ የምርጫ ክልል 11 የሚገኘው የእየሩሳሌም ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምርጫ ጣቢያ ምሽት 12 ሰዓት ካለፈ በኋላ መራጮች ድምጽ ሲሰጡ ዘጋቢዎቻችን ተመልክተዋል።

በምርጫ ጣቢያ የሚገኙ አስፈጻሚ “በድንኳን ውስጥ ተሰልፈው የሚገኙ መራጮች ድምጽ ሰጥተው እስኪጨርሱ ድረስ አስመርጡ” የሚል መልዕክት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።


11፡ 59 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምሽት 12 ሰዓት ይጠናቀቅ የነበረውን የድምጽ መስጪያ ጊዜ አራዘመ። የተራዘመው ጊዜ የሚቆየው እስከ 12 ሰዓት ድረስ ሰልፍ ላይ የነበረው መራጭ ድምጽ ሰጥቶ እስኪያጠናቀቅ መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።

በ2011 ዓ.ም የጸደቀው የምርጫ፣ የየፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና እና የስነ ምግባር አዋጅ፤ ምርጫ ቦርድ “በልዩ ሁኔታ” የድምጽ መስጫ ሰዓትን ሊያራዝም እንደሚችል ደንግጓል። ይኸው አዋጅ በህግ የተደነገገው የድምጽ መስጫ ሰዓት ሲያበቃ “የምርጫ ጣቢያዎች እንዲዘጉ” ያዝዛል።

ሆኖም የምርጫ ጣቢያው ቢዘጋም፤ “በምርጫ ጣቢያ ድምጽ ለመስጠት በመጠባበቅ ላይ ያሉ መራጮች ድምጽ መስጠት እንዳለባቸው” በዚሁ አዋጅ ላይ ሰፍሯል። ምርጫ ቦርድ “ለምርጫው ነጻ እና ፍትሃዊነት ይበልጥ ያሰፍናል ብሎ ካመነ” የድምጽ መስጫ ሰዓቱን መራዘም እንደሚችልም በዚሁ አዋጅ ላይ ተቀምጧል።


የአዲስ አበባ ሴቶች ማኅበር፣ በምርጫ ክልል 1 እና 9፣ አፄ ፋሲል የምርጫ ጣቢያ ተቀማጭ ታዛቢ የሆኑት አለሚቱ ኦልማ፣ በዕለቱ የምርጫ ሂደት በምርጫ ጣቢያው ውስጥ ያስተዋሉት ምንም ችግር እንደሌለ ለ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ነግረውታል።


የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን መሪ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ በአዲስ አበባ ከተማ፣ አራዳ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 04፣ ምርጫ ክልል 1 እና 9 በሚገኘው የአጼ ፋሲል ትምህርት ቤት ምርጫ ጣቢያ ዛሬ 10 ሰዓት ከ20 ላይ የምርጫ ሂደቱን ተመልክተዋል። ኡሁሩ ከትዝብታቸው በኋላ ውሏቸውን አስመልክተው ከመገናኛ ብዙሃን ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል።

“ተዘዋውረን የታዘብናቸው የምርጫ ጣቢያዎች ሠላማዊ ናቸው” ያሉት ኡሁሩ፤ የመራጮች ትዕግስት እና ለመምረጥ ያላቸው ፍላጎት “የሚበረታታ ነው” ሲሉ አድንቀዋል። “ምርጫ የሁሉም ነገር መጀመሪያ እና መጨረሻ ሳይሆን ሂደት ነው” ሲሉም አስገንዝበዋል።


10፡ 30 በድሬዳዋ የድሮ ቀበሌ ሸማቾች ግቢ ምርጫ ጣቢያ፣ ነገ ተስፋ ት/ቤት ምርጫ ጣቢያ፣ እና ነገ ተስፋ ፎረም ምርጫ ጣቢያ በአንድ ግቢ እንደተቋቋመ የ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። ዘጋቢያችን 10፡30 ገደማ እንደተመለከተው፣ በዲጂታል የምዝገባ ስርዓት የተመዘገቡ መራጮችን የማረጋገጥ ሼል ረዘም ያለ ጊዜ በመውሰዱ መጨናነቅ እንደተፈጠረ አስተውሏል።

በተጨማሪም በግቢው ውስጥ የቀበሌ አመራሮች መራጭ ሰዎችን ይዘው በመምጣት እንዲመርጡ ጫና ሲያደርጉ ተስተውለዋል። የምርጫ አስፈፃሚዎቹ ከ3 ጊዜ በላይ ከምርጫ ጣቢያ ቢያስወጧቸውም በተደጋጋሚ ችግር በመፍጠራቸው በፖሊስ ተባርረው ሲወጡ ዘጋቢያችን ተመልክቷል።


9፡ 30 በአዲስ አበባ ከተማ፣ አራዳ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 04፣ ምርጫ ክልል 1 እና 9 የሚገኘውን የባሻ ወልዴ ምርጫ ጣቢያ አስር ሰዓት ተኩል ገደማ የተመለከቱት ዘጋቢዎቻችን፤ አሁንም በርካታ መራጮች ተሰልፈው ወረፋ ሲጠባበቁ ተመልክተዋል።

በዚሁ ምርጫ ክልል የሚገኘው የአጼ ፋሲል ትምህርት ቤት ምርጫ ጣቢያ ከደቂቃዎች በኋላ የጎበኙት ዘጋቢዎቻችን፤ በቁጥር አነስ ያሉ መራጮች መሰለፋቸውን ታዝበዋል። ዛሬ እኩለ ቀን ገደማ በተሰጠው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጫ ላይ በርካታ መራጮች በሰልፍ ላይ በመሆናቸው የጽምጽ መስጪያው ጊዜ ይራዘም እንደሆነ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦ ነበር።

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ “በህጉ የተቀመጠው 12 ሰዓት ጀምሮ 12 ሰዓት ያልቃል” የሚል እንደሆነ አስታውሰዋል። “ነገር ግን ህጉ እንደሚፈቅደው ድምጽ ለመስጠት የተሰለፉ መራጮች ካሉ እነሱን መራጮች በሙሉ እንዲመርጡ የማድረግ ኃላፊነት ስላለብን፤ የተሰለፉ መራጮች መርጠው የሚያጠናቅቁበት ይሆናል” ሲሉም አብራርተዋል።


9፡ 20 የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ፤ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 4 የብልፅግና ፓርቲ አባል በምርጫ ጣቢያ ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያከናውን መገኘቱን አሳውቋል። 

ኅብረቱ ይህንን ያሳወቀው ዛሬ ሰኞ ግንቦት 24፤ 2018 እየተካሄደ ያለውን የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የግማሽ ቀን የትዝብት ሪፖርቱን ይፋ ባደረገበት መግለጫው ነው። ጋዜጣዊ መግለጫውን ያነበቡት የኅብረቱ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሳህለሥላሴ አበበ፣ ኅብረቱ 2,255 ተቀማጭ ታዛቢዎች እንዲሁም 801 ተንቀሳቃሽ እና 3,149 አጠቃላይ ታዛቢዎች ማሰማራቱን ገልጸዋል። 

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ምርጫ በሚካሄድባቸው ሁሉም አካባቢዎች በአጠቃላይ ያሰማራው የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች ብዛት 2,258 መሆኑም ተጠቁሟል።


የኢዜማ የባሕር ዳር የምርጫ ክልል የፓርላማ ዕጩ የሆኑት ኃይለማርያም ብርሃኑ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ነጻና እና ገለልተኛ ሆነው ዜጎች ሲመርጡ የታዩ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎች “የነገሩን የሚያስደስት ነገር አይደለም” ብለዋል።

ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን ወደ ምርጫ ጣቢያ አላስገባም የማለት ሁኔታም እንደነበር ገልጸዋል። ሆኖም፣ “ዞሮ ዞሮ የአንድ አገር የዴሞክራሲ መለማመጃ ምርጫ ነው” ብለዋል።


8፡ 58 ዛሬ ከሰዓት በኋላ የድሬዳዋ ምርጫ ጣቢያዎችን እየተዘዋወረ የተመለከተው የ”ምርጫ 2018- ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፣ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑን አስተውሏል።

ለአብነትም በድሬዳዋ ምርጫ ክልል 1፣ ጌታቸው ዳቦ ቤት ምርጫ ጣቢያ፣ 907 ሠው ምርጫ ካርድ መውሰዱ የተገለጸ ሲሆን፣ 380 ሰው እስከ 8:58 ድረስ መምረጡን የምርጫ አስፈፃሚዎች አረጋግጠዋል፤ ሆኖም ገና 527 መራጮች በቀረው ሰዓት እንዲመርጡ ይጠበቃሉ።


በምርጫ ጣቢያዎች ስለሚስተዋሉ ረጅም ሰልፎች ምርጫ ቦርድ ምን አለ? 

“ካጋጠሙን ችግሮች አንዱ በተለይም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መራጮች ሰልፍ ላይ መሆን ነው። በተለይም የዲጅታል ምዝገባ ባደረግንባቸው ምርጫ ጣቢያዎች አዲስ አበባን ጨምሮ ረጅም ሰልፍ እያየን እንገኛለን። ይህ የሆነበት ምክንያት እንደምታቀውቁት በዲጂታል የሚመዘገቡ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው በሞባይል አፕ ወይም በዌብ ቤዝድ ራሳቸውን መዝግበዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በምርጫ ጣቢያ ቦርዱ ባዘጋጀው ታብሌት ተመዝግበዋል።

ስለዚህ ለአንድ ምርጫ ጣቢያ የሚመዘገብ ሰው፤ በታብሌት ሊመዘገብ ይችላል ወይም በራሱ ታብሌት ሊመዘገብ ይችላል። የእነዚህን ሰዎች ቅድመ ተከተላቸውን የሚወስነው ራሱ ሲስተሙ ነው። ነገር ግን ፕሪንት ስናደርግ ይህንን የመራጮች መዝገብ በአማርኛ አልፋቤት እየተከተልን ከሀ እስከ ፐ ነው የተዘጋጀው፡፡ እንደማንዋሉ ምዝገባ እያንዳንዱ መዝገብ አስቀድሞ የተሰጠው ገጽ ቁጥር የለም።

አንድ ተመዝጋቢ ሲመጣ በካርዱ ‘በገጽ 17 ተመዝግበዋል’ ቢለውም በዲጅታሉ ላይ የተመዘገቡት ግን ለተመዝጋቢዎች ገጽ ቁጥር አይሰጥም፡፡ ችግሩን አይተን፣ በሰልፍ ላይ ያሉትን ሰዎች የተመዝጋቢዎችን ዳታ ይዘን፣ በካርድ ጀርባ ላይ እየጻፉ የሚሰጡ የሚያስተናግዱ እና ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ እያመቻቸን ነው።

የሲስተሙ አፈጻጸም ስለሆነ በመራጮች ካርድ አስቀድሞ የገጽ ቁጥር ባለመሰጠቱ ያጋጠመ ችግር ነው። በዚህ አጋጣሚ ረጅም ሰዓት ሰልፍ ላይ የቆዩትን መራጮች ይቅርታ ማለት እፈልጋለሁ” – ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ 


7፡ 29 በአዲስ አበባ ከተማ፣ ምርጫ ክልል 21/22 የኢዜማ ዕጩ የሆኑት አቶ አንዷለም በውቀቱ፣ የፓርቲያቸው ተዘዋዋሪ ታዛቢ ሆነው በተሰማሩበት የ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ጋር ተገናኝተው አጭር ቆይታ አድርገዋል።

አቶ አንዷለም ምርጫው እስካሁን ባለው ሁኔታ ሰላማዊ መሆኑን ገልጸው፤ ከፍተኛ ወረፋ በምርጫ ጣቢያዎች መታየቱን ገልጸዋል። የሰልፉን ርዝመት ምክንያት የማጣራት ሥራ እየሠሩ መሆኑንም ጨምረው አስረድተዋል። 


7፡ 20 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ዛሬ እኩለ ቀን ገደማ በሰጡት መግለጫ በምን ያህል የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ ታዛቢዎች እንደተገኙ ቁጥራዊ መረጃ ሰጥተዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ በ39,723 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ ታዛቢዎች ተገኝተዋል።

በተመሳሳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል እጩዎች ወኪሎች በ1,978 የምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ሂደቱን እየተከታተሉ መሆኑን አስታውቀዋል። የምርጫ ሂደቱ “ነጻ እና ገለልተኛ መሆኑን ለማረጋገጥ” የታዛቢዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ዋና ሰብሳቢዋ በዚሁ መግለጫቸው ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።


7፡ 10 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 143 የምርጫ ጣቢያዎች በጸጥታ ችግር አለመከፈታቸውን አስታወቀ። በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል “በተወሰኑ ቦታዎች” የድምጽ መስጠት ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ የተቋረጠባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉም ቦርዱ ገልጿል።  

ቦርዱ ይህን ያስታወቀው ዛሬ ሰኞ ግንቦት 24፤ 2018 ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ያለውን ሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ በሰጠው መግለጫ ነው። መግለጫውን በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል የሰጡት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ናቸው። 

ሜላትወርቅ በዚሁ መግለጫቸው፤ በዛሬውን የድምጽ መስጠት ሂደት ለማካሄድ 50,188 ምርጫ ጣቢያዎች በሰዓቱ ተከፍተዋል። ከ12 ሰዓት ከ30 እስከ ጠዋት አንድ ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የተከፈቱ የምርጫ ጣቢያዎች ብዛት 695 መሆናቸውን ዋና ሰብሳቢዋ አመልክተዋል።

ድምጽ መስጠት ከተጀመረ በኋላ ባጋጠመ “የጸጥታ ችግር”፤ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች የምርጫ ሂደቱ መቋረጡንም ሜላትወርቅ ተናግረዋል። ምርጫ ከተቋረጠባቸው ውስጥ  ቢሎኖፓ፣ መኮሳቺ፣ ቀርሳ እና ኩታበር የተባሉ የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚገኙበትም አክለዋል።


3፡ 20 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ መሪ አቶ እዮብ መሳፍንት፤ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 9፣ ምርጫ ክልል 18፣ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ምርጫ ጣቢያ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ተገኝተው ጽምጻቸውን ሰጥተዋል።

አቶ እዮብ ከመረጡ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ ሂደቱ ችግሮች ቢያጋጥሙንም እየፈታን እዚህ ደርሰናል” ብለዋል። “ኢዜማውያን እየመረጡ ነው። እስካሁን ባለው ሂደት ያን ያህል የጎላ ችግር አልገጠመንም” ሲሉም አክለዋል።

የኢዜማው መሪ ፓርቲያቸው በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫው በ12 ሰዓት መጀመሩን ማረጋገጡንም አስታውቀዋል። “ካርድ ማባከን ተገቢ ስላልሆነ፣ ሁሉም የተመዘገበ ዜጋ መምረጥ አለበት” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።


2:18 በአዲስ አበባ ከተማ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 13፣ ምርጫ ክልል 17፣ ላስታ ስላሴ ምርጫ ጣቢያ ጠዋት 2 ሰዓት ገደማ የደረሱት የ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች፤ በርካታ መራጮች ተሰልፈው ተመልክተዋል ።

በዚህ ጣቢያ ለመምረጥ ተራቸውን ከሚጠባበቁ መራጮች መካከል የፌደራል ፖሊስ አባላት ይገኙበታል። አንዲት የ90 ዓመት አዛውንት ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ድምጻቸውን ሰጥተዋል። አዛውንቷ በምርጫ ሲሳተፉ ለአምስተኛ ጊዜያቸው እንደሆነ ለዘጋቢዎቻችን ተናግረዋል። ድምጻቸውን የሚሰጡት “ለሀገር ሰላም” ሲሉ እንደሆነም ገልጸዋል።

እርሳቸው ድምጽ በሰጡበት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ፊት ለፊት በሚገኘው ምርጫ ጣቢያ፤ ከአንዲት የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ ውጪ ሌሎች ታዛቢዎች አልነበሩም። ይህን በተመለከተ ለምርጫ አስፈጻሚዎች ጥያቄ ያቀረቡት ዘጋቢዎቻችን፤ “ጠዋት ነበሩ። አሁን ሄደዋል” የሚል ምላሽ አግኝተዋል።


2:05 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ እና የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው የህዳሴ ምርጫ ጣቢያ ዛሬ ጠዋት ተገኝተው ድምጽ ሰጥተዋል።


1፡ 13  በአዲስ አበባ ከተማ፣ አቃቂ ምርጫ ክልል፣ ወረዳ 6 ፅህፈት ቤት፣ ሸማች ግቢ ምርጫ ጣቢያ ድምጽ የመስጠት ሂደቱ ከጠዋቱ 12 ሰዓት መጀመሩን የምርጫ አስፈጻሚዎች ገልጸዋል።

በዚህ የምርጫ ጣቢያ ድምጽ ከሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ልጇን ያዘለች መራጭ ትገኝበታለች። ይህቺው መራጭ የድምጽ መስጫ ወረቀቱን ሳትሸፍነው ለምርጫ አስፈጻሚ ስትሰጥ ዘጋቢያችን ተመልክቷል። የምርጫ አስፈጻሚው በበኩሉ የድምጽ መስጪያ ወረቀቱን አስተካክሎ በማጠፍ፣ የድምጽ መስጪያ ኮሮጆ ውስጥ እንድታስገባ ሲያደርጋት ዘጋቢያችን ታዝቧል።


1፡ 11  የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ ጠዋት 1፡00 ሰዓት ገደማ፣ በምርጫ ክልል 01 ቀበሌ ምርጫ ጣቢያ ጌይ መድረሳ ታችኛው ቁ 2፣ መርጠዋል።


12፡ 56 በአዲስ አበባ ከተማ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 12፣ ቢላል መስጊድ ሼድ አጠገብ የሚገኘው የምርጫ ጣቢያ፤ የድምጽ መስጠት ሂደቱ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እየተከናወነ ነው።

በዚህ የምርጫ ጣቢያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዕጩነት ከቀረቡት ውስጥ የብልጽግና ፓርቲን የወከሉት የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ እና በትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ስር የሚወዳደሩት ምስጢረ ስላሴ ታምራት የኢህአፓ ዋና ጸሀፊ ምስጢረ ስላሴ ታምራት ይገኙበታል።

በምርጫ ጣቢያው ድምጻቸውን ለመስጠት ከተገኙ መራጮች መካከል አንዲት ግለሰብ የምርጫ ካርድ ቢኖራትም ስሟ የዲጂታል ምዝገባ መራጮች ዝርዝር መዝገብ ላይ ሲፈለግ አለመገኘቱን የ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክታለች። በጣቢያው የተመደቡ የመዝገብ ሹም፤ ለግለሰቧ በስልክ የተላከላትን የመራጭ መለያ ቁጥር አይተው እንድትመርጥ አድርገዋታል።

ይህ ችግር የተከሰተው በዚህ ምርጫ ጣቢያ ለሶስት ቀናት “ሲስተም በመጥፋቱ” ምክንያት እንደሆነ የጣቢያው ምርጫ አስፈጻሚ ለ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት 40 ገደማ የተመዘገቡ እና የምርጫ ካርድ የወሰዱ የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ከሲስተሙ ላይ “ስማቸው እንደጠፋ” የምርጫ አስፈጻሚዋ ለዘጋቢያችን ተናግረዋል።


12፡ 43 በአዲስ አበባ ከተማ፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 6፣ ቤቶች ኮርፖሬሽን ምርጫ ጣቢያ ድምጽ መስጠት የተጀመረው ጠዋት 12 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ላይ ነበር።

የድምጽ መስጠቱ ለምን እንደዘገየ የ”ምርጫ 2018- ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ላቀረበው ጥያቄ፤ የጣቢያው የምርጫ አስፈጻሚ “ቅድመ ዝግጅቱ በሰዓቱ ስላላለቀ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህ የምርጫ ጣቢያ 1,498 መራጮች ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በጣቢያው የብልጽግና ፓርቲ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር፣ የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ታዛቢዎች ተገኝተዋል።


12፡ 20 የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን መሪ የሆኑት የቀድሞው የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ፤ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ በምርጫ ክልል 18 ፣ በፒተር ፓን ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከጠዋቱ 12 ሰዓት በፊት ተገኝተው የምርጫውን ሂደት ታዝበዋል።

አሁሩ ሂደቱን ከተከታተሉ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት፤ ምርጫው በሰዓቱ መጀመሩን እና በምርጫ ጣቢያው የተደረገው ዝግጅት ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ፒኮክ መናፈሻ ወደሚገኘው የምርጫ ጣቢያ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከ20 ገደማ ተገኝተው፤ በዚያ ያለውን ሂደትም ተመልክተዋል። አሁሩ በዚህኛው የምርጫ ጣቢያ የተወሰነ መዘግየት እንዳለ ገልፀው ሂደቱ ግን “ጥሩ ነው” ብለዋል።


12፡ 19 በአማራ ክልል፣ በባህር ዳር ከተማ፣ ህዳሴ የምርጫ ጣቢያ ከጠዋቱ 12 ሰዓት የድምጽ መስጠት ሂደት ተጀምሯል። የምርጫ ጣቢያው ሲከፈት የጽምስ መስጪያ ኮሮጆዎቹ ባዶ መሆናቸውን በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች ተመልክተዋል።


12፡ 09 በሐረር ከተማ ፣ ቀበሌ 10፣ ደን ልማት ምርጫ ጣቢያ ከንጋቱ 11:28 ጀምሮ በምርጫ ጣቢያው መራጮች ተገኝተዋል። የምርጫ ጣቢያው ሲከፈት የፓሊስ አባላት በቦታው ነበሩ።

የምርጫ አስፈጻሚ የጽምጽ መስጫ ሳጥኑ ባዶ መሆኑን በቦታው ለተመደቡ ሁለት ታዛቢዎች አሳይቷል። በእነዚሁ ታዛቢዎች ፊት የምርጫ መዝገቡ እና የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ከእሽግ ተፈቷል። በዚህ ምርጫ ጣቢያ ድምጽ መስጠት የተጀመረው ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከ08 ደቂቃ ላይ ነው።


11፡ 50 በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአቃቂ የምርጫ ክልል፣ ቶታል ኮንዶሚኒየም እና ጊዮርጊስ ዕድር ቤት የምርጫ ጣቢያዎች፤ ፤ እንዲሁም በላፍቶ ኮንዶሚኒየም የምርጫ ጣቢያ የድምጽ መስጠት ሂደት ከመጀመሩ አስቀድሞ ያለው ሁኔታን ለመመልከት ከታች የተያያዙትን ፎቶዎች ይመልከቱ።


11፡ 40 በአዲስ አበባ ከተማ፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ፒተር ፓን ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚገኘው ምርጫ ጣቢያ ንጋት ላይ የነበረው ሂደት ከታች በፎቶ የሚታየውን ይመስላል።