የፌዴራል መንግስት ለክልሎች 520.6 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጎማ መደበ

የፌደራል መንግስት ለ2019 ባዘጋጀው በጀት፤ ለ12 ክልሎች እና ለሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተመደበው የገንዘብ ድጎማ መጠን ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ትሪሊዮን ብር ተሻገረ። በዚህ የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ ባለፈው ዓመት ከድጎማ ዝርዝር ውጭ ተደርጎ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተመልሶ የተካተተ ቢሆንም፤ የተመደበለት የገንዘብ መጠን ግን ሩብ ቢሊዮን ብር እንኳ የማይሞላ ሆኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2019 በጀት ዓመት የተመደበለት የገንዘብ ድጋፍ መጠን 74.53 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለፓርላማ አባላት ከተሰራጨው የበጀት ሰነድ ላይ ተመልክታለች። የከተማ አስተዳደሩ በ2017 ከፌደራል መንግስት የተመደበለት ድጎማ 5.45 ቢሊዮን ብር ነበር። 

በ2016 በጀት ዓመት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተመድቦ የነበረው የገንዘብ መጠንም እንዲሁ አምስት ቢሊዮን ብርን የተሻገረ ነው። በዚህ ዓመት ለከተማ አስተዳደሩ የተበጀተው ድጎማ 5.25 ቢሊዮን ብር እንደነበር የወቅቱ የበጀት ሰነድ ያሳያል።

ለመጪው በጀት ዓመት ከተያዘው የክልሎች ድጋፍ ውስጥ ከፍተኛው መጠን የተመደበው ለኦሮሚያ ክልል ሲሆን አማራ እና ሶማሌ ክልሎች በሚያገኙት የድጎማ መጠን በሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የኦሮሚያ ክልል ለ2019 በጀት ዓመት የተመደበለት ድጋፍ 179.35 ቢሊዮን ብር ነው።

የኦሮሚያ ክልል የፌደራል መንግስት ለክልሎች ከሚሰጠው ድጎማ ከፍተኛውን ድርሻ ሲያገኝ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። እየተገባደደ ባለው የ2018 በጀት ዓመት 108.4 ቢሊዮን ብር፣ በ2017 ደግሞ 74.8 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ያገኘው ክልሉ፤ የድጎማውን የመጀመሪያ ረድፍ ለዓመታት ይዞ ቆይቷል። 

በተመሳሳይ መልኩ የአማራ ክልልም፤ ከፌደራል በሚገኝ ድጋፍ ሁለተኛውን ከፍተኛ መጠን ሲያገኝ ቆይቷል። የአማራ ክልል ለመጪው ዓመት የተበጀተለት ድጋፍ 112.4 ቢሊዮን ብር ነው። ክልሉ ለመጪው በጀት ዓመት የተመደበለት ድጎማ 67.9 ቢሊዮን ብር ነበር። ይህ የድጋፍ መጠን በ2017 ከነበረው በ21 ቢሊዮን ብር የላቀ ነው።

በፌደራል በጀት የድጎማ ክፍፍል ለሶስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ የቆየው የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ነበር። ለአራት የተከፈለውን ይህን ክልል በመተካት፤ ከ2017 በጀት ዓመት ጀምሮ ሶስተኛ ደረጃን የያዘው የሶማሌ ክልል ነው።

የሶማሌ ክልል በ2019 በጀት ዓመት የተመደበለት የድጋፍ ገንዘብ 52 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ነው። ይህ የድጎማ መጠን ለክልሉ በዘንድሮው በጀት ዓመት ከተመደበው ድጎማ በ20 ቢሊዮን ብር የላቀ ነው። በ2018 በጀት ዓመት ለሶማሌ ክልል የተበጀተው 31.4 ቢሊዮን ብር ድጋፍ፤ በ2017 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ9 ቢሊዮን ብር የጨመረ ነበር።

ለክልሎች በሚከፋፈለው የገንዘብ ድጋፍ ሶማሌ ክልልን ተከትለው በአራተኛ እና በስድስተኛ ደረጃ የተቀመጡት የደቡብ ኢትዮጵያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ናቸው። በህዝበ ውሳኔ የተመሰረቱት ሁለቱ ክልሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በበጀት ዝርዝር ውስጥ የገቡት በ2017 ዓ.ም ነበር።

በዚሁ በጀት ዓመት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 15.2 ቢሊዮን የድጋፍ ገንዘብ የተመደበለት ሲሆን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 12.8 ቢሊዮን ብር ተበጅቶለታል። ከሁለት ዓመት በኋላ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተመደበው ድጎማ ከሁለት እጥፍ በላይ ጨምሮ 36.5 ቢሊዮን ብር ሲደርስ፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ድጋፍም በተመሳሳይ 30.9 ቢሊዮን ብር ገብቷል። 

በክልሎች የድጋፍ ክፍፍል አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የትግራይ ክልል፤ ለመጪው 2019 በጀት ዓመት የተመደበለት የድጋፍ ገንዘብ 31.3 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ የድጎማ መጠን ለክልሉ ዘንድሮ ከተመደበው ድጎማ በ12.4 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ ነው። 

የትግራይ ክልልን ጨምሮ ለክልሎች በመጪው በጀት ዓመት ከተመደበው 520.6 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ፤ 98 በመቶው የሚሸፈነው ከመንግስት ግምጃ ቤት መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ሰነድ ያመለክታል። ቀሪው 8.9 ቢሊዮን ብር ከፕሮጀክት ዕርዳታ እንደሚሸፈን ለፓርላማ አባላት በተሰራጨው ሰነድ ላይ ሰፍሯል።

ከዚህ የድጎማ መጠን በተጨማሪ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማስፈጸም የሚውል 14 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጋፍ ለአስራ ሁለቱ ክልሎች እና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መደልደሉን በሰነዱ ላይ ተቀምጧል። ይህ የበጀት ድጋፍ “የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ ለሚያግዙ የአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ እና በክልሎች ለሚካሄዱ ለአነስተኛ እና መካከለኛ መስኖ ልማት ካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል” እንደሆነም ተጠቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)