የ“አዲስ ስታንዳርድ” ምዝገባ መሰረዝን በመቃወም፤ ፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥ አቤቱታ ቀረበ 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በ“አዲስ ስታንዳርድ” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ላይ የወሰደው ምዝገባ የመሰረዝ እርምጃ፤ በፍርድ ቤት ታግዶ እንዲቆይ አቤቱታ ቀረበ። አቤቱታውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረበው ክስ ያካተተው የመገናኛ ብዙሃኑ አሳታሚ ጃኬን ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው። 

ድርጅቱ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ፣ የአስተዳደር ጉዳዮች ችሎት ክስ የመሰረተው ከሶስት ሳምንት በፊት ሚያዝያ 29፤ 2018 ነው። ክሱ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በየካቲት ወር አጋማሽ በ“አዲስ ስታንዳርድ” ላይ የወሰደውን “አስተዳደራዊ እርምጃ በመቃወም” የቀረበ መሆኑን አሳታሚ ድርጅቱ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

በፍርድ ቤት ክስ እንዲመሰረት ምክንያት የሆነው አስተዳደራዊ እርምጃ፤ የ“አዲስ ስታንዳርድ” የምዝገባ ምስክር ወረቀት መሰረዝን የተመለከተ ነው። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የበየነ መረብ መገኛ ብዙሃኑ ምዝገባ መሰረዙን ያስታወቀው ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ባወጣው መግለጫ ነው። 

ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ይህን እርምጃ የወሰደው፤ “አዲስ ስታንዳርድ” “የሚዲያ ስነ-ምግባርን፣ የኢትዮጵያን ህጎች እና የሀገርንና የህዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ አሰራጭቷል” በሚል ምክንያት ነበር። ውሳኔውን በወቅቱ የተቃወመው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃኑ፤ የቀረቡበትን ውንጀላዎችም ውድቅ አድርጓል።

መገናኛ ብዙሃኑ በዚህ ብቻ ሳይወሰን እርምጃውን በመቃወም ለባለስልጣኑ የስራ አመራር ቦርድ “የአቤቱታ ደብዳቤ በማስገባት” ምላሹን ሲጠባበቅ ቆይቷል። የስራ አመራር ቦርዱ “የባለስልጣኑን ውሳኔዎች በይግባኝ የመመልከት” ስልጣን በ2013 ዓ.ም በወጣው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ተሰጥቶታል።

ቦርዱ “አመልካቾች እና ባለፈቃዶች የሚቀርቧቸውን አቤቱታዎች፣ ባለፈቃዶችን አስመልክቶ ከህዝብ የቀረቡ ቅሬታዎችን እና [የመገናኛ ብዙሃን] አዋጅ አፈጻጸም በሚመለከት በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን መርምሮ” እንደሚወስንም በዚሁ ህግ ተደነግጓል። የ“አዲስ ስታንዳርድ” አሳታሚ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ የተወሰደው እርምጃ “ተገቢውን የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ሳይከተል” የተላለፈ መሆኑን በመግለጽ ለቦርዱ ያቀረበው “የቅሬታ አቤቱታ” “ምንም ዓይነት ምላሽ” አለማግኘቱን  አመልክቷል።

“ድርጅቱ ውሳኔው እንዲነሳለት መጀመሪያ ለባለሥልጣኑ የሥራ አመራር ቦርድ የቅሬታ አቤቱታ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ከቦርዱም ተገቢውን አስተዳደራዊ ፍትህ ማግኘት ባለመቻሉ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ተገድዷል”

“ድርጅቱ ውሳኔው እንዲነሳለት መጀመሪያ ለባለሥልጣኑ የሥራ አመራር ቦርድ የቅሬታ አቤቱታ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ከቦርዱም ተገቢውን አስተዳደራዊ ፍትህ ማግኘት ባለመቻሉ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ተገድዷል” ሲል ጃኬን ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በዛሬው መግለጫው ላይ አስፍሯል።

በአሳታሚ ድርጅቱ በኩል ለፍርድ ቤት የቀረበው ክስ፤ የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ እርምጃ የሀገሪቱን ህጎችን እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን “የጣሰ መሆኑን” ያጣቀሰ ነው። እርምጃው የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትን፣ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን፣ የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ እና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን የጣሰ መሆኑን ድርጅቱ በዛሬ መግለጫው አብራርቷል።

“ይህ ሁሉ ሕጋዊ ማዕቀፍ እያለ ባለሥልጣኑ የወሰደው እርምጃ፤ ከሕግ አግባብ ውጭ የሆነ እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ነጻነትን ለመገደብ የታለመ መሆኑን በመግለጽ ክስ መስርተናል” ሲል አሳታሚ ድርጅቱ በመግለጫው አትቷል። ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በወሰደው እርምጃ ላይ “የእግድ ትዕዛዝ” (injunction) እንዲሰጥለት ድርጅቱ ለችሎቱ አቤት ማለቱንም አስታውቋል።

የእግድ ትዕዛዙን በተመለከተ አሳታሚ ድርጅቱ፤ የፍርድ ቤቱን ብይን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝም ገልጿል። የእግድ ትዕዛዙን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለሚቀጥለው ረቡዕ ሰኔ 3፤ 2018 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተረድታለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)