የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ “የለውጡ አስተዳደር ስልጣን ላይ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ” በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በሌሎች ወገኖች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ልዩ ቡድን በአስቸኳይ እንዲቋቋም ጠየቀ። ቡድኑ የምርመራውን ውጤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለክልል ምክር ቤቶች እና ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግም ፓርቲው አሳስቧል።
ኢዜማ ጥያቄውን ያቀረበው “የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር በምንም ምክንያት እና በማንኛውም ጊዜ ለድርድር የማይቀርብ ነው” በሚል ርዕስ ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 25፤ 2012 ባወጣው መግለጫ ነው። የፓርቲው መግለጫ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም አምንስቲ ኢንተርናሽናል፤ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዘ በተመለከተ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው ሪፖርት ላይ የተንተራሰ ነው።
አምንስቲ በሪፖርቱ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ፈጽመዋቸዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በስፋት ዘርዝሯል። ሪፖርቱ የተወሰኑ ቦታዎችን ብቻ መሸፈኑ እና ውስን ክስተቶች ላይ ያጠነጠነ መሆኑ “በሀገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሙሉ በሙሉ ለመረዳትም ሆነ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ” በቂ እንደማያደርገው ኢዜማ በመግለጫው ጠቁሟል። ሆኖም ሪፖርቱ የጠቀሳቸው ዝርዝር መረጃዎች “ተጨማሪ ምርመራ ተደርጎ፤ የተጠቀሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው ከተረጋገጠ፤ የእርምት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ከበቂ በላይ አመላካች ናቸው” ብሏል።
“ተጨማሪ ምርመራ ተደርጎ፤ የተጠቀሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው ከተረጋገጠ፤ የእርምት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ከበቂ በላይ አመላካች ናቸው”
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
በዚህ እሳቤ ላይ በመመስረትም ፓርቲው “በአስቸኳይ” መደረግ ይኖርበታል ያለውን እርምጃ ጠቁሟል። የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሊተገብረው ይገባል የተባለው ይህ እርምጃ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ቡድን ማቋቋም ነው። መርማሪ ቡድኑ በአምንስቲ ሪፖርት ውስጥ የተካተቱን ጨምሮ “የለውጡ አስተዳደር ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ” የተፈጸሙ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያጣራ ኢዜማ ጠይቋል።
መርማሪ ቡድኑ የፌደራል እና የክልል መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በዜጎች ላይ ከፈጸሟቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ባሻገር “የፖለቲካ ዓላማ ያነገቡ ታጣቂዎች እና በየአካባቢው የተደራጁ ኢ-መደበኛ ቡድኖች” የፈጸሟቸውን ተመሳሳይ ድርጊቶች ማጣራት እንደሚገባው ፓርቲው በመግለጫው አሳስቧል። ቡድኑ ምርመራውን በየቦታዎቹ በመገኘት፣ ከተጎጂዎች እና ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ በጊዜው በአካባቢው ግዳጅ ላይ ከነበሩ የፀጥታ አስከባሪዎች፣ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ ወገኖችን በማካተት እንዲያካሄድ ፓርቲው ሀሳብ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት “የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር በምንም ምክንያት እና በማንኛውም ጊዜ ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን መረዳት እንደሚገባው” ኢዜማ በመግለጫው አመልክቷል። “ዜጎች ላይ ጥፋት የሚያደርሱ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ መገንባት ለምንፈልገው ሥርዓት ያለውን ከፍተኛ ዋጋ በመረዳት [መንግስት] ለዜጎች ደህንነት እና ሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያረጋግጥ እናሳስባለን” ሲልም አክሏል።
መንግስት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለሚያደርገው ልዩ ምርመራ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ እና በምርመራው ውጤት ላይ በመመስረትም አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ ቁርጠኝነቱን በድጋሚ ያረጋግጥ ዘንድም ፓርቲው ጠይቋል። (በተስፋለም ወልደየስ -ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)