ሱዳን የህዳሴው ግድብ ሙሌት ስምምነት ላይ ሳይደረስ እንዳይጀመር የጸጥታውን ምክር ቤት ጠየቀች

በሐይማኖት አሸናፊ

ሱዳን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ባስገባችው ደብዳቤ በህዳሴው ግድብ ላይ አጠቃላይ ስምምነት ሳይደረስ በፊት የግድቡ ሙሌት እንዳይጀመር ጠየቀች። ሁሉም ወገኖች በቅን ልቦና ወደ ድርድር እና ስምምነት እንዲመለሱ ሱዳን እያደረገች ያለውን ጥረት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲያግዝም ጥሪ አቅርባለች።

ሀገሪቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አስማ መሃመድ አብደላ የተፈረመውን ደብዳቤ ለጸጥታው ምክር ቤት ያስገባችው ትላንት ማክሰኞ ግንቦት 25፤ 2012 ነው። ግብጽ ሚያዚያ 23፤ 2012 እና ኢትዮጵያ ደግሞ ግንቦት 6፤ 2012 ለጸጥታው ምክር ቤት  ያስገቧቸውን ደብዳቤዎች ተከትሎ ሱዳንም በጉዳዩ ላይ ካላት ጥቅም ተነስታ አስተያየት ለመሰጠት መወሰኗን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ባለ 15 ገፅ ደብዳቤ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ግብጽ አጠቃላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ብዙ ርቀት መጓዛቸውን አስታውሷል። ሚኒስትሯ “የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ካለ በቀሩት ጥቂት ጉዳዮች ላይ መስማማት ይቻላል” ሲሉም ያላቸውን ተስፋ በደብዳቤያቸው ጠቁመዋል። 

የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አጠቃቀም አስመልክቶ በተባበሩት መንግስታት አማካኝነት በ1989 ዓ. ም. የወጣውን ስምምነት በደብዳቤዋ የጠቀሰችው ሱዳን የስምምነቱ መርህ “በህዳሴው ግድብ ላይም ሊተገበር ይገባል” ብላለች። ምክንያታዊ እና ተመጣጠኝ የውሃ አጠቃቀም፣ የከፋ ጉዳት ያለማድረስ ኃላፊነት፣ መረጃ የመለዋወጥ እና የማሳወቅ ኃላፊነት እንዲሁም ግጭቶችን በሰላም መፍታት የሚሉት የኮንቬንሽኑን መርሆዎችንም በደብዳቤዋ ላይ አካትታለች።

የሱዳን ደብዳቤ የአባይ ወንዝ በተለይ ለሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ያለውን ጠቀሜታ እና ትርጉም በዝርዝር አስቀምጧል። የሱዳን 40 ሚሊዮን ዜጎች ህይወት የተመሰረተው በአባይ ወንዝ ላይ እንደሆነ የሚያስረዳው ደብዳቤው ከሀገሪቷ የመስኖ ልማት 70 በመቶ የሚሆነው የሚሸፈነው በዚሁ ወንዝ መሆኑን አመልክቷል። 

“የአባይ ወንዝ ቀጠናችንን የባረከ ወንዝ ነው። ከ250 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የሶስቱ አገራት ህዝቦች ህይወት የተመሰረበት ወንዝ ነው። ወንዙ ከቀጠናው ህዝቦች ታሪክ፣ ባህል፣ ኢኮኖሚ እና ህሊና የማይነጠል አካል ነው” ሲሉ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በደብዳቤያቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ግዙፉ የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ በትልቅነቱ ከአፍሪካ አንደኛ፤ ከአለም ደግሞ 15ኛ እንደሚሆን ሱዳን በደብዳቤዋ ላይ ጠቅሳለች። የእዚህን ግድብ አዎንታዊ እና አሉታዊ ጎኖች በደብዳቤዋ የዘረዘረችው ሱዳን መደረግ ይኖርበታል ያለችውን ጠቁማለች። 

የህዳሴው ግድብ መገንባት፤ ሱዳን በየአመቱ የዝናብ ወቅት በመጣ ቁጥር የሚያጋጥማትን የጎርፍ መጥለቅለቅ ለማስቀረት የሚያስችል መሆኑ በዋነኛ ጠቀሜታን ተነስቷል። ግድቡ ለተሻለ የመስኖ ልማት አስተዳደር እና ሱዳን ያላትን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ለመጨመር እንደሚያግዝም ተገልጿል። 

በሌላ በኩል ግድቡ የአባይ ወንዝን የፍሰት መስመር የሚቀይር መሆኑ እና የህዳሴው ግድብ ዲዛይን፣ ግንባታ፣ ሙሌት እና የዕለት ተዕለት ተግባር ባግባቡ ካልተመራ በሱዳን ህዝብ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያመጣ በደብዳቤው ተብራርቷል። ጉዳቱ ከህዳሴ ግድቡ ጋር በቀጥታ የሚዋሰኑ የሱዳን ህዝቦችን ህይወት እና ደህንነት ለአደጋ ከማጋለጥ አንስቶ የሱዳን ግድቦችን የዕለት ተዕለት ተግባር እስከመጉዳት የሚደርስ ጫና ሊኖረው እንደሚችል ይዘርዝራል። 

የህዳሴ ግድብ ፎቶዎች፦ ዶ/ር ስለሺ በቀለ

ሱዳን ግድቡ የአገሯን “ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊ፣ የግብርና እንዲሁም የአካባቢ ሁኔታ የሚጎዳበት እድል አለ” በማለት በደብዳቤዋ ብትገልጽም በግድቡ በጎ ጎኖች ላይ በማተኮር እንዲሁም አሉታዊ ጎኖቹን መቀነስ እንደሚቻል ያላትን እምነት ከመጠቅስ አልተቆጠበችም። ለዚህም ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት መድረስ እንደሚያስፈልግ አስገንዝባለች። ስምምነቱ “የግድቡን ሙሌት እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ያጠቃለለ መሆን አለበት” ብላለች። 

ይህ ካልሆነ ግን “የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ አደጋ አለው” ስትል አቋሟን ገልጻለች። ኢትዮጵያውያን የአባይን ወንዝ የመጠቀም እና ኑሮአቸውን የማሻሻል መብት አላቸው ብላ እውቅና እንደምትሰጥ የገለፀችው ጎረቤት አገር ሱዳን ይህ ግን የታችኛው ተፋሰስ አገራትን እንዳይጎዳ ምክክር እና ትብብር ያስፈልጋልም ስትል አክላለች።

ሱዳን ከ2003 ጀምሮ በግድቡ ላይ ሲካሄዱ የነበሩ ድርድሮችን እና ስምምነቶችን በመጥቀስ ሶስቱ አገራት በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን ልዩነት እያጠበቡ መምጣታቸውን አስረድታለች። መጋቢት 14፤ 2007 በካርቱም የተፈረመው የስምምነት መርሆዎች፤ በሶስቱ አገራት መካከል በተደረጉ ውይይቶች ከተገኙ መልካም ፍሬዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቅሳለች። “ለአመታት የዘለቀው የድርድር ሂደት በአሜሪካ እና በአለም ባንክ ታዛቢነት ቀጥሎ ነበር” ያለችው ሱዳን በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል በሚሰጡ መግለጫዎች አማካኝነት የተገባው የቃላት ጦርነት ግን ውይይቱ እንዲቆም ማድረጉን ሱዳን ለጸጥታው ምክር ቤት ገልጻለች።

ኢትዮጵያ እና ግብጽ በግድቡ ዙሪያ ለውይይት እንዲቀመጡ ሱዳን በቀዳሚነት ጥረት እያደረገች መሆኗን የገለጹት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ግንቦት 11፤ 2012 የሶስቱ አገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች በቪዲዮ ስብሰባ መቀመጣቸውንም ለአብነት አንስተዋል። ሱዳን በደብዳቤዋ “ድርድሮች በቅን ልቦና ሊደረጉ ይገባል” የሚለውን አቋሟን ደጋግማ አንጸባርቃለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)