የችሎት ውሎ፦ ጃዋር መሐመድ “በከፍተኛ ሁኔታ መታመማቸውን” ለፍርድ ቤት ገለጹ

በተስፋለም ወልደየስ

በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የቅድመ ምርመራ ጉዳያቸው እየታየ ካሉ 14 ተጠርጣሪዎች መካከል 5ቱ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 11፤ 2012 ከሰዓት ላስቻለው ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አስታወቀ። ከሌሎች ሰባት ተጠርጣዎች ጋር ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ጃዋር መሐመድ በከፍተኛ ሁኔታ መታመማቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸው በግል ሀኪማቸው ህክምና ማግኘት ይችሉ ዘንድ ጥያቄ አቅርበዋል።  

ችሎቱ ለዛሬ የተቀጠረው የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት እና ፍርድ ቤቱ የሰጣቸውን ትዕዛዞች መፈጸም አለመፈጸማቸውን ለማረጋገጥ ነበር። የዕለቱን ችሎት ያስቻሉት ዳኛ ቅድሚያ ሰጥተው የተመለከቱት የትዕዛዞቹን ጉዳይ ነው። ዳኛው ከፌደራል ፖሊስ የሚመለከተው አካል መቅረቡን ካረጋገጡ በኋላ ፖሊስ ትዕዛዞቹን በተመለከተ በዛሬው ዕለት ለፍርድ ቤት ያስገባውን ደብዳቤ ጥቅል ይዘት አሰምተዋል።

“በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ባሉ አራት ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ” በሚል የቀረበው ደብዳቤ የተጠርጣሪዎቹን ማንነት ባይገልጽም በዚያ ያሉ ተጠርጣሪዎች ተገቢውን እንክብካቤ እያገኙ እንደሆነ ጠቅሷል። ተጠርጣሪዎቹ ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ በማይሆን መልኩ መያዛቸውን፣ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ቤተሰቦቻቸውን እንደሚያገኙም ደብዳቤው ገልጿል። 

በወንጀል ምርመራ ቢሮ የቦታ ጥበት በመኖሩ ምክንያት ቀሪዎቹ 10 ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲቆዩ መደረጉን ደብዳቤው ጠቁሟል። እነዚህ ተጠርጣሪዎች በየክፍላቸው ዘርዝር ተደርገው እንዲቀመጡ በማድረግ ለኮሮና እንዳይጋለጡ ተደርጓልም ብሏል። ተጠርጣሪዎቹ በጥንቃቄ ቤተሰቦቻቸውን እንዲገናኙ መደረጉንም አስታውቋል። 

በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በመጠርጠሩ ምክንያት ባለፈው አርብ ነሐሴ 8፤ 2012 በዋለው ችሎት ያልቀረቡ አምስት ተጠርጣሪዎች በድጋሚ እንዲመረመሩ መደረጉንም የፌደራል ፖሊስ ደብዳቤ አመልክቷል። የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተጠርጣሪዎቹን የምርመራ ውጤት ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ በደብዳቤ ማሳወቁንም አብራርቷል። 

ኢንስቲትዩቱ የተጠርጣሪዎቹን የምርመራ ውጤት በአባሪነት የያዘ ሁለት ገጽ ደብዳቤ ዛሬ ለፍርድ ቤቱ ማስገባቱን ጉዳዩን የሚመለከቱት ዳኛ ለችሎቱ ታዳሚያን አሳውቀዋል። በምርመራ ውጤቱም መሰረት ዳዊት ንብረት፣ ሰቦቃ ቃቆ፣ ኬኛ ደሜቻ፣ ጌቱ ተረፈ እና በሽር ሁሴን በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ኢንስቲትዩቱ ለፍድር ቤቱ አረጋግጧል። 

በኮሮና ምክንያት ባለፈው ችሎት ካልቀረቡት ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ ታምራት ሁሴን የተባሉ ተጠርጣሪ ዛሬ በችሎት አለመገኘታቸውን የጠቀሱት ዳኛው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ጠይቀዋል። እንደሌሎቹ ሁሉ ታምራትም በኮሮና ቫይረስ መያዙ በመጠርጠሩ ፍርድ ቤት አለመገኘቱን ፖሊስ ለፍርድ ቤት ምላሽ ሰጥቷል። 

ፍርድ ቤቱ ባለፈው የችሎት ውሎ የቀረቡ ተጠርጣሪዎች ላይም የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዲደረግ እና ውጤቱ እንዲገለጽ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ያስታወሱት ዳኛው የእነርሱስ ጉዳይ ከምን ደረሰ? ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል። ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ ከአንደኛ እስከ አራተኛ የተዘረዘሩ ተጠርጣሪዎች ለኮሮና በማያጋልጣቸው ቦታ፣ በቂ እንክብካቤ እያገኙ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል። ቀሪዎቹ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎችም ቢሆኑ አንድ ቦታ ላይ አለመሆናቸውን ጠቅሷል። 

የፖሊስን ምላሽ ያደመጡት ዳኛው ይህም ቢሆን ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝ “አልተፈጸመም” ብለዋል። “እነዚህ ተጠርጣሪዎች እንደ ማንኛውም ሰው በእንክብካቤ የመያዝ መብት አላቸው። ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ባልሆነ ሁኔታ የመያዝ መብት እንዳላቸው ፍርድ ቤቱ ያምናል። የፍርድ ቤቱ አቋምም ይሄው ነው” ሲሉ ለችሎቱ ተናግረዋል።  

“አንድ ሰው በለበሰው ለረጅም ጊዜ ሊቆይ እንደማይገባ” የጠቀሱት ዳኛው ይህ ከሆነ “ለሌሎች በሽታዎች ሊጋለጥ እንደሚችል ግልጽ ነው” ብለዋል። ተጠርጣሪዎቹ ከቤተሰብ የሚመጣላቸውን ምግብም ሆነ ልብስ ሊከለከሉ እንደማይገባም አስገንዝበዋል። “ለጥንቃቄ ብላችሁ ልብስም፤ ምግብም እንዳይገባ ብትከለክሉም ቦታው ለቫይረሱ ተጋላጭ እያደረጋቸው ነው። በቫይረሱም እየተጠቁ ነው ያሉት” ሲሉ ዳኛው ተናግረዋል። 

ኮሮና ኖረም፣ አልኖረ ተጠርጣሪዎች ምግብ እና ልብስ የማግኘት፣ ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጠበቆቻቸው እና የእምነት አባቶቻቸው ጋር የመገናኘት ህገ መንግስታዊ መብታቸው ሊጣበብ አይገባም በማለትም ዳኛው አሳስበዋል። “መብታቸው ቫይረሱን ምክንያት ተደርጎ ሊገደብ አይገባም” ብለዋል። 

በዚህ አቋሙ ላይም ተመርኩዞ ፍርድ ቤቱ ለተጠርጣሪዎቹ ልብስ ሊገባላቸው እንደሚገባ፣ ምግብም ከቤተሰብ ሲመጣ ተገቢው ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲገባላቸው፣ ከጠበቃ እና ከእምነት አባቶቻቸው ጋር እንዲገናኙ “በአጽንኦት እና በጥብቅ” ትዕዛዝ ማስተላለፉን ዳኛው አስታውቀዋል። “ይሄን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተላልፋችሁ የማትፈጽሙ ከሆነ ፍርድ ቤቱ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል” ሲሉ ዳኛው አስጠንቅቀዋል።

ከዚህ የዳኛው ንግግር በኋላ አራት ተጠርጣሪዎች በየተራ አሉን የሚሏቸውን አቤቱታዎች ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል። ከተጠርጣሪዎቹ ቅድሚያውን የወሰዱት አቶ ሀምዛ ቦረና ናቸው። እርሳቸውን ጨምሮ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኙ አራት ተጠርጣሪዎች፤ ለኮቪድ 19 በተጋለጠ ቦታ እንዳልተያዙ ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት የፖሊስ ኮማንደር “ትክክል” መሆናቸውን አቶ ሀምዛ ተናግረዋል። እንዲያም ቢሆን ግን የኮሮና ቫይረስ “ምልክቶች እየታዩብን ነው። ደረቅ ሳል እያሳለን” በማለት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ስላሳለፉት ጊዜ አስረድተዋል። 

“ምርመራ ሊደረግን ይገባል ብለን ብናመለክትም አልተመረመርንም” ያሉት አቶ ሀምዛ ችሎት ሲመጡ ከሌላ ቦታ ከሚመጡት ጋር ንኪኪ ስለሚኖራቸው በበሽታው የመያዝ ስጋት እንዳለባቸው አመልክተዋል። ከኮሮናም ሌላ በሌሎች በሽታዎች የተያዙ ተጠርጣሪዎች እንዳሉ የገለጹት አቶ ሀምዛ ለበሽታዎቻቸው በቂ ህክምና እንደማያገኙ ለፍርድ ቤት አቤት ብለዋል። 

የደም ግፊት እና ስኳር በሽታ እንዳለባቸው የጠቀሱት ተጠርጣሪው ለህክምና ቢወሰዱም በዚያ በቂ ህክምና አለማግኘታችውንና የተሰጣቸውም መድኃኒትም እንዳላሻላቸው አብራርተዋል። ጓደኛቸው አቶ ጃዋር መሐመድም ታማሚ መሆኑን ተናግረው ፍርድ ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል። 

ከሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መምጣታቸውን የተናገሩ ሌላ ተጠርጣሪ ከእነርሱ ጋር አብረው ሲመገቡ እና ሲተኙ የነበሩ ስድስት ሰዎች በኮሮና ፖዘቲቭ ተብለው ከፍርድ ቤት መቅረታቸውን አስታውሰው ከዚያ በኋላ ግን ለእነርሱ ምርመራ አለመደረጉን ጠቁመዋል። ውሃ በጋራ የሚጠጡባቸው ዕቃዎችን እንኳ በአግባቡ ለማጽዳት ሁኔታው እንደማይመች ለችሎት አስረድተዋል። አሁን በእነርሱ ላይም የኮሮና ቫይረስ ምልክቶች እየታዩባቸው መሆኑንም ተናግረዋል። 

ፖሊስ በፍርድ ቤት የተሰጠውን ትዕዛዝ አክብሮ ከቤተሰብ ጋር በየጊዜው እንድንገናኝ እያደረገ አይደለም ያሉት እኚህ ተጠርጣሪ ምግብም ከቤተሰብ እንደማይገባላቸው ገልጸዋል። ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሩቁ እንዲተያዩ መፈቀዱን የተናገሩት ተጠርጣሪው “መነጋገር በማይቻልበት ሁኔታ ልብስ ወርውረውልን ነው የሄዱት” ሲሉም ‘ኮሮና ገብቷል’ በመባሉ በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚፈጠረውን ጭንቀት ለችሎት አስረድተዋል። 

እነርሱ ታስረው ባሉበት ቦታ ላሉ ተጠርጣሪዎች፤ በትላንትው ዕለት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲነጋገሩ ስልክ ተፈቅዶ እንደነበር የገለጹት ተጠርጣሪው ሆኖም “በወቅታዊ ጉዳዮች የተጠረጠራችሁ መደወል አትችሉም ተብለናል” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል። በስተመጨረሻም ከእነርሱ ተለይተው ስላሉ ተጠርጣሪዎች ሲናገሩም “30 ሰው በሚይዝ ቦታ 68 ሰው ታጭቆ ነው ያለው” ብለዋል። 

አቤቱታውን ያደመጡት ዳኛ  “እናንተ እስረኞች እንደመሆናችሁ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ትዕዛዝ የመፈጸም ግዴታ አለባቸው”በማለት የአዲስ አበባ ፖሊስም ቢሆን ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ ሊፈጽም እንደሚገባ አሳስበዋል። ቤተሰብ ሲመጣ፤ የጤና ጥበቃ ያወጣውን ህግጋት ተክትሎ እና ርቀታቸውን ጠብቆ ማገናኘት እንደሚቻልም ዳኛው ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ በቃል የሰጠውን ትዕዛዝ ስለመፈጸሙም እንደሚያረጋግጥ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ዳኛው የአቃቤ ህግ ምስክሮች የመስማት ሂደት እንዲቀጥል ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ ምን ያህል ምስክሮች ለዛሬ እንደቀረቡ ጠይቀዋል። አቃቤ ህግ ሶስት ምስክሮች እንዳቀረበ ገልጾ ሂደቱ ሊጀመር ሲል በሁለተኛ ተጠርጣሪነት በመዝገቡ ላይ የሰፈሩት አቶ በቀለ ገርባ “ሂደቱ ላይ አንዳንድ ሀሳብ መስጠት እፈልጋለሁ” በማለታቸው እንዲናገሩ ተፈቅዶላቸዋል። 

አቶ በቀለ “ቅድመ ምርመራ ሂደት ውስጥ እንድናልፍ መደረጉ ተገቢ አይደለም” ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። የህግ ባለሙያ ባይሆኑም ይህ የቅድመ ምርመራ ህግ ከወጣ 50 እና 60 ማስቆጠሩን እና በፍርድ ቤቶች እምብዛም ስራ ላይ ያልዋለ መሆኑን ጠቅሰዋል። “ስራ ላይ ካለመዋሉ የተነሳ ለእኔ እንደተተወ የሚቆጠር ህግ ነው” ያሉት ተጠርጣሪው በዚህ ህግ የሚደረገው ሂደት አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል። መደበኛ ክስ ተመስርቶ፤ ክስ የመስማት ሂደት ቢጀምር ተገቢ መሆኑም ጠቁመዋል። 

ሁለተኛ ምስክሮችን የሚሰማበት ሂደትን በተመለከተም ያላቸውን አስተያየት ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል። “ምስክሮቸ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው የሚመሰክሩበትን ሂደት መቃወም እፈልጋለሁ” ያሉት አቶ በቀለ “መንግስት የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ከመጋረጃ ጀርባ ሊያስመሰክርብን የተዘጋጀ እንደሆነ አድርጌ ነው የምወስደው” ሲሉ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል። 

“እኛ የፓርቲ አባላት ነን። የመንግስት ተቃናቃኝ ነን። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከመንግስት ጋር የተካረረ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። ይሄ አካሄድ እኛን ለማጥፋት ነው የሚል እምነት ነው ያለን። እኛ ንጹሀን ሰዎችን ከፖለቲካ ገለል ለማድረግ እንጂ ፍትህ ለመስጠት ነው ብዬ አላምንም” ሲሉ በፍትህ ሂደቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለችሎት አሰምተዋል።  

አቶ በቀለ ዛሬ ምስክርነት ይሰማ ቢባል እንኳ “ይህንን የማያስችሉ ምክንያቶች አሉ” ብለዋል። “ከእኛ ጋር የተጠረጠሩ ሰዎች ታምመው ችግር ላይ ባሉበት ሁኔታ ምስክርነት ለመስማት አንችልም” ሲሉ ለችሎቱ በመጀመሪያ ደረጃ ያስቀመጡትን ምክንያት አስረድተዋል። ከእነርሱ ጋር ታስረው ካሉት ውስጥ የጃዋር መሐመድን የጤንነት ሁኔታም በተጨማሪነት አንስተዋል። “ትላንትም፤ ዛሬ ቀኑ ሙሉም ህመም ውስጥ ነው ያለው። የግድ መሄድ አለበት ስለተባለ ነው የመጣው እንጂ ህመም ላይ ነው ያለው” ሲሉ ስለ ጃዋር ሁኔታ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። 

ዛሬ ምስክር መሰማት አይችልም ያሉበት ሁለተኛ ምክንያት ከጠበቆቻቸው ጋር በነጻነት መነጋገር ባለመቻላቸው መሆኑን አቶ በቀለ ገልጸዋል። ጠበቆቻቸው ከእነርሱ ጋር ለመነጋገር ዛሬ ወደ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መጥተው እንደነበር የጠቆሙት ተጠርጣሪው፤ በተቀመጡበት ቦታ ድምጽ እና ምስል የሚወስድ ካሜራ በመኖሩ መመካከር እንዳልቻሉ አስረድተዋል። “በምስጢር መነጋገር እስክንችል እና ካሜራው እስኪነሳ ድረስ የዛሬው ቀጠሮ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ እጠይቃለሁ” ሲሉም ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል። 

ከአቶ በቀለ ተከትሎ የመናገር እድል ያገኙት ጃዋር መሐመድ “ትላንት ማታ አልተኛሁም። በከፍተኛ ሁኔታ ታምሜ ነው ያለሁት። እስካሁን ማስታገሻ መውሰድ አልቻልኩም” ሲሉ ለችሎት ተናግረዋል። “ፖሊሶች ለ30 ደቂቃም ቢሆን ፍርድ ቤት መቅረብ አለብህ ብለውኝ ነው የመጣሁት” ሲሉ ለፍርድ ቤት የተናገሩት አቶ ጃዋር ከአልጋ ተነስተው መምጣታቸውን ገልጸዋል። 

አቶ ጃዋር ያለባቸውን ህመም የተጠርጣሪዎቹ ማረፊያ ቤት በምክትል ዳይሬክተርነት ለሚመሩት ኮማንደር መግለጻቸውን ለፍርድ ቤቱ ጠቅሰዋል። “ከፍተኛ ዘመቻ እየተደረገባቸው” መሆኑን ለፍርድ ቤቱ የገለጹት ተጠርጣሪው ይህም ለህይወቸው “ከፍተኛ አደጋ” መጋረጡን አንስተዋል። “በማላውቀው ሀኪም ለመታየት እኔም ሆነ ቤተሰቤ ስጋት አለን” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት በግል ሀኪማቸው ህክምና ማግኘት ይችሉ ዘንድ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ  እንዲሰጥላቸው ጥያቄ አቅርበዋል። በጣም እያመማቸው በመሆኑ፤ ሲሻላቸው እንዲመጡ ችሎቱ ለዛሬ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል።  

በመጨረሻም በውጭ ሀገር ያሉትን ባለቤታቸውን እና ልጃቸውን ለማነጋገር እንዲፈቅድላቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል። ይህንኑ ጥያቄቸውን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አዳነች አቤቤ ሊጎበኟቸው በመጡ ጊዜ ማቅረባቸውን እና ሁኔታዎች እንደሚመቻቹላቸው ምላሽ እንደተሰጣቸው አስታውሰዋል። ቤተሰቦቻቸውን በምን መልኩ ሊያነጋግሯቸው እንዳሰቡ ከዳኛው ለቀረበላቸው ጥያቄም “በቪዲዮ ኮንፍረንስ ማግኘት እችላለሁ” ሲሉ መልሰዋል። ወጪውን ራሳቸው መሸፈን እንደሚችሉ ለፍርድ ቤቱ አስታውቀዋል።

ዳኛው የቀረቡትን የተጠርጣሪዎች አቤቱታ ካደመጡ በኋላ ለጠበቆች የመናገር እድል ከመስጠታቸው በፊት አቶ በቀለ በቀረቡ የተወሰኑ ቅሬታዎችን በተመለከተ የፍርድ ቤቱን አቋም ግልጽ አድርገዋል። “ቅድመ ምርመራ ሂደትን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ያለፈበት ነው” ያሉት ዳኛው ቀሪ ሊሆን የሚችለው በይግባኝ ሲሻር እንደሆነ ጠቁመዋል።   ፍርድ ቤቱ “ወደ ኋላ መመለስ አይችልም” ሲሉም ለአቶ በቀለ አቤቱታ ምላሽ ሰጥተዋል። 

ዛሬ ችሎት ፊት ከቀረቡት የእነ ጃዋር መሐመድ 11 ጠበቆች ውስጥ ሁለቱ በአቶ በቀለ አማካኝነት ከቀረበው አቤቱታ ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው መከራከሪያ አሰምተዋል። በዚህ መካከል አቶ ጃዋር “በጣም ነው እያመመኝ ያለው” በማለት አየር ለመውሰድ፤ ችሎቱን አቋርጠው ለመውጣት ጥያቄ በማቅረባቸው ተፈቅዶላቸው ከችሎት ውጪ እንዲቆዩ ተደርገዋል።

ጠበቆቹ ባለፈው አርብ ደንበኞቻቸው ወደታሰሩበት ሲሄዱ “ፍርድ ቤት ሄደዋል” ተብለው እንዲመለሱ መደረጉን ጠቅሰው ዛሬ ጠዋት ተመልሰው ሲሄዱም ካሜራ በተገጠመለት ክፍል እንዲገናኙ በመደረጉ እንደልብ መነጋገር አለመቻላቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። ድርጊቱ በህገ መንግስቱ የተደነገገው የደንበኞቻቸው የግላዊነት (privacy) መብት በሚጥስ እና ጠበቃ የመወከል መብታቸውን በሚጎዳ መልኩ የተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል። 

ከጠበቆቹ አንዱ “ለደንበኞቻችን ተገቢውን ውክልና (effective respresenetaion) የምንሰጥበት ሁኔታ ላይ አይደለም እና ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ እንጠይቃለን” ሲሉ ለችሎቱ አመልክተዋል። የጠበቆችን ጥያቄ ያዳመጡት ዳኛው አቃቤ ህግ በቀረቡ ጉዳዮች ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ዕድል ሰጥተዋል።

“ተጠርጣሪዎች እና ጠበቆች ካሜራ በተገጠመለት ክፍል እንዲገናኙ ተደርገዋል” ለሚለው አቤቱታ አቃቤ ህግ በሰጠው ምላሽ “በእኛ በኩል የምናውቀው ነገር የለም። እናጣራለን” ብሏል። ቀዳሚ ምርመራን በተመለከተ የቀረበው አቤቱታ ግን ምስክር እንዲሰማ ከተወሰነ መቆየቱን በመጥቀስ፤ በተጠርጣሪዎች አሁን እየቀረበ ያለው መከራከሪያ “ሂደቱን ራሱን በተለያዩ ምክንያቶች የማሰናከል አካሄድ ነው” ሲል አቃቤ ህግ ተቃውሟል። 

አቃቤ ህግ “ፍርድ ቤቱ ቀዳሚ ምርመራ ለማድረግ ከወሰነ ቆይቷል። ሂደቱን በተለያየ መንገድ ወደ ኋላ የመመለስ ምልክቶች እያየን ነው” ሲል ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ሂደቱን እንዲጓተት እያደረጉ ለመሆኑ አቃቤ ህግ ከዚህ ቀደም የነበሩ የችሎት ሂደቶችን በመዘርዘር ተከራክሯል። 

በጠበቆች በኩል የቀረበው “የመዘጋጃ ጊዜ አላገኘንም” የሚለው አቤቱታም ችሎቶቹ በተደጋጋሚ ቀጠሮዎች ሲራዘሙ ሊዘጋጁ ይችሉ እንደነበር በመጠቆም ተቀባይነት እንደሌለው አመልክቷል። “የተፋጠነ ፍትህ ማግኘት” የሚለው መርህ ለተጠረጠረ ሰው ብቻ ሳይሆን ለወንጀሉ ሰለባዎች የሚውል እንደሆነ የጠቀሰው አቃቤ ህግ የተፋጠነ ፍትህ እንዳይገኝ ሂደቱን በተለያዩ ምክንያቶች ማጓተት በተጠርጣሪዎች በኩል እንደሚታይ ተናግሯል። የምስክሮች መሰላቸት፣ የማስረጃ መባከን እንዲፈጠር የሚደረጉ ሙከራዎች እንደሆኑም አስገንዝቧል።   

የአቶ ጃዋርን መታመም በተመለከተ ዛሬ ጠዋት በፖሊስ አማካኝነት እንደተገለጸለት የጠቀሰው አቃቤ ህግ ሆኖም “እስር ቤቱ ባለው ህክምና ለማሳከም ሲሞክር ተጠርጣሪው ፍቃደኛ አልነበሩም” ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። “ሀኪም ለማየት ፍቃደኛ ስላልሆኑ በቁጥጥር ስር የሚያቆያቸው አካል እንዴት ነው ጤንነታቸው የሚያረጋግጠው?” ሲል አቃቤ ህግ ጠይቋል።   

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች እና ጠበቆቻቸው ያቀረቡትን “ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጥልን” ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የአቃቤ ህግ ምስክሮች እንዲሰሙ አዟል። ሆኖም ሂደቱ እየተከናወነ ባለበት ወቅት አቶ ጃዋር እያመማቸው በመሆኑ እና በተደጋጋሚ ውጭ ለመውጣት እያስፈቀዱ በመሆኑ የምስክር ሂደቱን መቀጠል እንዳልተቻለ ፍርድ ቤቱ ገልጾ፤ ለሐሙስ ነሐሴ 14፤ 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። 

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች እና ጠበቆቻቸው ያቀረቡትን “ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጥልን” ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የአቃቤ ህግ ምስክሮች እንዲሰሙ አዟል። ሆኖም ሂደቱ እየተከናወነ ባለበት ወቅት አቶ ጃዋር እያመማቸው በመሆኑ እና በተደጋጋሚ ውጭ ለመውጣት እያስፈቀዱ በመሆኑ ምስክር የመስማት ሂደቱን መቀጠል እንዳልተቻለ ፍርድ ቤቱ ገልጾ፤ ለሐሙስ ነሐሴ 14፤ 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። የአቃቤ ህግ ምስክሮችም በተለዋጭ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ብሏል። 

ፍርድ ቤቱ በቀረቡ አቤቱታዎች ላይም ትዕዛዝ ሰጥቷል። በዚህ መሰረት ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት የኮሮና ምርመራ እንዲደረግላቸው ታዞላቸው የነበሩ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ምርመራ እንዲደርግላቸው፣ 11ኛ ተጠርጣሪ ሀምዛ ቦረና ከኮሮና ውጭ አሉብኝ ያሉትን እና በፍርድ ቤት ለዘረዘሯቸው በሽታዎች ህክምና እንዲያገኙ እንዲደረግ አዟል። 

አንደኛ ተጠርጣሪ ጀዋር መሐመድ ባለው የህክምና አሰጣጥ መሰረት ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል። አቶ ጀዋር ወጪያቸውን ሸፍነው ከቤተሰቦቻቸው ጋር በቪዲዮ ኮንፍረንስ እንዲገናኙ እንዲደረግም ትዕዛዝ ሰጥቷል። ተጠርጣሪዎች ምስጢራዊነቱ በተጠበቀ እና ካሜራ በሌለበት ቦታ ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙም አዟል። በቀጣይ ቀጠሮ ከኮሮና በሽታ ያገገሙ ተጠርጣሪዎች ካሉ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ በማሳሰብ ፍርድ ቤቱ የዕለቱን ችሎት አጠናቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)