የእነ ስብሃት ነጋ የቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት እና ማንነታቸው ሳይጠቀስ እንዲካሄድ ተወሰነ

በቅድስት ሙላቱ

የፌደራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በእነ ስብሃት ነጋ መዝገብ የምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት እና የምስክሮች ስምና አድራሻቸው ሳይጠቀስ እንዲካሄድ ዛሬ አርብ ውሳኔ አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው ዐቃቤ ህግ “ለምስክሮች ጥበቃ አድርጊያለሁ” ማለቱን ተከትሎ በተከሳሽ ጠበቆች የቀረበውን መቃወሚያ ከመረመረ በኋላ ነው። 

በዐቃቤ ህግ በኩል የተነሳው የምስክሮች ጥበቃ ህገ-መንግስታዊ መሆኑን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፤ ከቀረቡለት ሶስት የምስክር አሰማም ሂደቶች ሁለቱን  መቀበሉን በውሳኔው አመልክቷል። ተቀባይነት ካገኙት የምስክር አሰማም ሂደቶች የመጀመሪያው ማንኛውም ሚዲያ እና ታዳሚ ሳይገባ በዝግ ችሎት የቅድመ ምርመራ ምስክሮች የሚሰሙበት ነው። 

የምስክሮች ስም እና አድራሻ ለተጠርጣሪዎች ሳይጠቀስ የምስክሮች ቃል የሚሰማበት ሁለተኛው አካሄድም እንዲሁ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አግኝቷል። ፍርድ ቤቱ ውድቅ ያደረገው የምስክር አሰማም ሂደት፤ ምስክሮች በአካል ሳይታዩ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ በሚል በዐቃቤ ህግ የቀረበውን ነው። 

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ፤ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ባገኙት ሁለት ሂደቶች የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ለግንቦት 9፤ 2013 ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን ውሎውን አጠናቅቋል። በዛሬው ችሎት አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ በርከት ያሉ ተጠርጣሪዎች በአካል ቀርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)