የመራጮች ምዝገባ ለሶስተኛ ጊዜ ተራዘመ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባን ለሶስተኛ ጊዜ አራዘመ። የመራጮች ምዘገባ ዛሬ ይጠናቀቅባቸው በነበሩ በሰባት ክልሎች እና በሁለት የከተማ መስተዳድሮች ቀነ ገደቡ ለተጨማሪ አንድ ሳምንት መራዘሙን ቦርዱ ዛሬ አስታውቋል። 

ምርጫ ቦርድ በመጀመሪያ ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የመራጮች ምዝገባን ለማከናወን አቅዶ የነበረው ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 21፤ 2013 ነበር። ቦርዱ የምርጫ ክልል ጽህፈት ቤቶችን ለመክፈት በክልል መንግስታት በኩል የታየው ዳተኝነት፣ የዕጩዎች ምዝገባ መራዘም እና የምርጫ ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ የገጠሙትን ተግዳሮቶች በምክንያትነት በመጥቀስ የመራጮች ምዝገባን ወደ መጋቢት አጋማሽ ማዛወሩ ይታወሳል። 

መጋቢት 16 ተጀምሮ ሚያዝያ 15 ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው የመራጮች ምዝገባ በታሰበው መልኩ ባለመከናወኑ፤ ከሶማሌ እና አፋር ክልል ውጪ ባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሁለት ሳምንት እንዲራዘም ተደርጎ ነበር። የመራጮች ምዝገባ በግማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ዘግይቶ መጀመሩ፤ ምዝገባው በጊዜው በተጀመረባቸው ቦታዎችም ቢሆን በመረጃዎች እጦት እና በሌሎች ምክንያቶች የምዝገባ ሂደቱን ለማከናወን የተወሰነ ጊዜ መውሰዱ እንዲሁም በአንድ የምርጫ ጣቢያ መመዝገብ የሚችሉት 1,500 ሰዎች ብቻ መሆናቸው የፈጠረው እክል ለምዝገባው መራዘም በምክንያትነት የቀረቡ ችግሮች ነበሩ።

በእነዚህ ምክንያቶች የመራጮች ምዝገባ በተስተጓጎለባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች፤ ምዝገባው እስከ ሚያዝያ 29፤ 2013 መራዘሙን ቦርዱ በወቅቱ አስታውቋል። የመራጮች ምዝገባ “እጅግ ዘግይቶ ተጀምሮባቸዋል” ለተባለባቸው የሶማሌ እና አፋር ክልሎች ተጨማሪ አንድ ሳምንት የሰጠው ቦርዱ የመመዝገቢያ ቀነ ገደቡን እስከ ግንቦት 6 ድረስ ማራዘሙ አይዘነጋም። 

ቦርዱ በዛሬው መግለጫው፤ በተሻሻለው የመራጮች የምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ ወቅት በተደራራቢ የበዓላት ቀናት ምክንያት የምርጫ ጣቢያዎች ዝግ እንደነበሩ ጠቅሶ በዚህም ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ሊከናወን አልተቻለም ብሏል። የመራጮች ምዝገባ በተራዘመበት ወቅት 1,500 መራጮች የመዘገቡ ጣቢያዎችን ለይቶ ንዑስ ጣቢያዎችን የማደራጀት ሂደት ጊዜ መውሰዱንም በመግለጫው አንስቷል። በዚህም ምክንያት በምርጫ ጣቢያዎች ላይ ከፍተኛ የመራጮች መጨናነቅ እንደተፈጠረ መረዳቱንም ገልጿል። 

በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ መምረጥ የሚችሉ፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ዜጎች የመራጮች ካርድ አለመውሰዳቸውን ከግምት ውስጥ ማስገባቱን የጠቆመው ቦርዱ፤ ይህን ተከትሎ ውሳኔ ለማሳለፍ ስብሰባ ማድረጉን አትቷል። በውሳኔው መሰረትም የመራጮች ምዝገባ ዛሬ ሚያዝያ 29 ይጠናቀቅባቸው በነበሩ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በሃረሪ ክልሎች፤ ምዝገባው ለተጨማሪ አንድ ሳምንት መራዘሙን አስታውቋል። 

እስከ ግንቦት 6፤ 2013 የተራዘመው የመራጮች ምዝገባ፤ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች ተግባራዊ እንደሚደረግም ቦርዱ አመልክቷል። በዚህም መሰረት የምርጫ ጣቢያዎች ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ለቀጣይ ሰባት ቀናት  የመራጮች ምዝገባን እንዲያከናውኑ ቦርዱ አሳስቧል። በአሁኑ ወቅት 41,798 የምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን እየመዘገቡ እንደሚገኙም ቦርዱ አክሏል። 

ቀድሞ ከተገመተው አንጻር “የተቀዛቀዘ ነው” የተባለለት የመራጮች ምዝገባ ሂደት መሻሻል ማሳየቱን የጠቆመው ምርጫ ቦርድ፤ ያለፉት ሶስት ቀናትን ሳይጨመር በተሰበሰበው ጊዜያዊ መረጃ መሰረት 28,731,935 መራጮች መመዝገባቸውን ይፋ አድርጓል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)