ከሶስት ሳምንት በፊት በአጣዬ ከተማ በደረሰ ጥቃት ከ400 በላይ ቤቶች መቃጠላቸውን እና ወደ 34 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውን አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በከተማይቱ እና አካባቢው ቤት ንብረታቸው የተቃጠሉባቸው ነዋሪዎች የምግብ እና ቁሳቁስ አፋጣኝ እርዳታ እንደሚሹም ገልጸዋል።
የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስዩም አሰፋ፤ ትላንት ረቡዕ ሚያዝያ 27 በአጣዬ ከተማ ለተገኘው የጋዜጠኞች ቡድን እንደገለጹት፤ በርካታ የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች እና ሌሎችም አካባቢዎች ተሰድደዋል። በጥቃቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ቀይ መስቀልን ጨምሮ ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ ቢያቀርቡም፤ ያለው መጠን ለሁሉም ተፈናቃዮች ለማዳረስ “በቂ አይደለም” ብለዋል።
“አሁን አንገብጋቢው በየቦታው የተሰደዱ ህብረተሰቦች ቤታቸው ተሰርቶ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ፤ የሚሟላቸው ዕቃ ካለ የቤት ቁሳቁስ እነኚያ እንዲሟሉ [ነው]። ከዚያ በመቀጠል ደግሞ እርዳታው ለሁሉም ህብረተሰብ እንዲደርስ የሚደረግበት ነገር ቢፈጠር የሚል ነገር አለኝ” ሲሉ የከተማይቱ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተናግረዋል።
ይህንን የአካባቢውን ባለስልጣን ጥሪ በጥቂቱም ቢሆን የመለሰ ሰብዓዊ ድጋፍ በትላንትናው ዕለት በአጣዬ ከተማ ተደርጓል። ድጋፉን የሰጠው አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አልያንስ) የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ለአደጋ መከላከል በሚል ካስቀመጠው ገንዘብ ላይ 1.2 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ 2,800 የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች ድጋፍ ማድረጉን የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል አርጋው ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)