የመራጮች ምዝገባ ተራዘመ

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሶማሌ እና አፋር ውጪ ባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ ለሁለት ሳምንት እንዲራዘም ውሳኔ አሳለፈ። የመራጮች ምዝገባ “እጅግ ዘግይቶ ተጀምሮባቸዋል” ባላቸው በሶማሌ እና አፋር ክልሎች ደግሞ ምዝገባው ለሶስት ሳምንታት እንደሚራዘምም ገልጿል። 

ቦርዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በሶስት ምክንያቶች መሆኑን ዛሬ አርብ ምሽቱን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ቦርዱ ለውሳኔው በመጀመሪያ ምክንያትነት ያስቀመጠው የመራጮች ምዝገባ በግማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ዘግይቶ መጀመሩን ነው። ምዝገባው በጊዜው በተጀመረባቸው ቦታዎችም ቢሆን፤ በመረጃዎች እጦት እና በሌሎች ምክንያቶች የምዝገባ ሂደቱን ለማከናወን የተወሰነ ጊዜ መውሰዱን ቦርዱ በሁለተኛ ምክንያትነት ጠቅሷል። 

በአንድ የምርጫ ጣቢያ መመዝገብ የሚችሉት 1,500 ሰዎች ብቻ መሆናቸው የፈጠረው እክልም ለመራጮች ምዝገባ መራዘም የተጠቀሰው ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል። የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቁ በቀሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ በአዲስ አበባ የተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ይህንን ኮታ መሙላታቸውን በማስታወቃቸው የመራጮች ምዝገባ መቋረጡን ቦርዱ አስታውሷል። ተጨማሪ ምርጫ ጣቢያዎች በመክፈት መራጮችን ለመመዝገብ በተደረገው ጥረት ላይ “ክፍተት” መፈጠሩንም ቦርዱ አክሏል። 

በእዚህ እና መሰል ምክንያቶች የመራጮች ምዝገባ በተስተጓጎለባቸው የአገሪቱ ክፍሎች፤ የመራጮች ምዝገባው እስከ ሚያዝያ 29፤ 2013 መራዘሙን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። ከሌሎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለየ ተጨማሪ አንድ ሳምንት የመራጮች የመመዝገቢያ ጊዜ በተሰጣቸው በአፋር እና ሶማሌ ክልል ደግሞ ምዝገባው የሚጠናቀቀው ግንቦት 6፤ 2013 እንደሚሆን ቦርዱ ገልጿል።ምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫው እንዳለው በአሁኑ ወቅት 41,659 ምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን እየመዘገቡ ይገኛሉ። እስከ ትላንት ሐሙስ ሚያዝያ 14 ባለው ጊዜም 18,427,239 መራጮች መመዝገባቸውን ቦርዱ ይፋ አድርጓል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ባለፈው ሳምንት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ባካሄዱት ውይይት ላይ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር “ በጣም አነስተኛ” መሆነውን ገልጸው ነበር። በዚሁ ገለጻቸው ወቅትም በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ የተመዘገበው መራጭ ቁጥር 200,903 እንደሆነ ጠቁመዋል። 

በትላንትናው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደ ስብሰባ ላይ ግን በከተማይቱ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተጠቀሰው የመራጮች ቁጥር በአንድ ሚሊዮን የላቀ ነበር። በአዲስ አበባ ይመዘገባል ተብሎ የሚጠበቀው ሰው 1,405,650 መሆኑ የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ፤ ከዚህ ውስጥ 1,234,802 ያህሉ መመዝገቡን ተናግረዋል። 

በአንድ ሳምንት ውስጥ የታየው ከፍተኛ የቁጥር ልዩነት በሌሎች ክልሎችም ተስተውሏል። በአማራ ክልል እስካለፈው ሳምንት የተመዘገበው መራጭ ብዛት አንድ ሚሊዮን እንኳን የማይሞላ እንደነበር ያስታወሱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ ቁጥሩ በዚህ ሳምንት ከአምስት ሚሊዮን በላይ መሻገሩን በስብሰባው ላይ ገልጸዋል። 

በኦሮሚያ ክልል ከአራቱ የወለጋ ዞኖች ውጭ ባሉ 17 ዞኖች ውስጥ ለመራጭነት ይመዘገባሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ 85 በመቶ ያህሉ መመዝገባቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናግረዋል። ለዘንድሮ ምርጫ በኦሮሚያ ይመዘገባሉ ተብለው ቅድሚያ ግምት የተሰጣቸው ሰዎች ብዛት 16 ሚሊዮን 500 ሺህ ሲሆን እስካሁን የተመዘገቡት 12,347,537 መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል። 

አቶ ሽመልስ በንግግራቸው ጠቀሰው አድርገው ያለፏቸውና በጸጥታ ችግር ምክንያት እስካሁንም ምዝገባ ያልተጀመረባቸውን የአራቱ የወለጋ ዞኖችን ጉዳይ የዛሬው የምርጫ ቦርድ መግለጫ ማብራሪያ ሰጥቶበታል። በምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፤ ሆሩጉድሩ እና ቄለም ወለጋ ባሉ በርካታ ወረዳዎች የመራጮች ምዝገባ የማስጀመር እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ቦርዱ ገልጿል። እንዲያም ሆኖ ግን በዞኖቹ ውስጥ ባሉ ሰባት ወረዳዎች አሁንም ምዝገባ የማይጀመር መሆኑን ጠቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)