እነ ጄነራል ሰዓረ መኮንንን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው ተከሳሽ በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነ

በሃሚድ አወል

የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም  የነበሩትን ጄነራል ሰዓረ መኮንንን እና ሜጀር ጄነራል ገዛዒ አበራን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው ተከሳሽ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 21 በተከሳሽ አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ውሳኔውን ያስተላለፈው፤ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የቀረበውን የሞት ቅጣት ውድቅ በማድረግ ነው። 

ዐቃቤ ህግ ሰኔ 11 በዋለው ችሎት  ከቅጣት አወሳሰን መመሪያው ወጥቶ በተከሳሽ ላይ የሞት ቅጣት እንዲወስንበት ጥያቄ አቅርቦ ነበር። “የቅጣት አወሳሰን የዜጎችን ደህንነት እና ሰላም ማስጠበቅ ዓላማ እና ታራሚውን የማስተማር ግብ አለው” ያለው ፍርድ ቤቱ፤ ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን የሞት ቅጣት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተከሳሹ ላይ የእድሜ ልክ እስራት ውሳኔ ያስተላለፈው፤ “ድርጊቱ ተሳክቶ ቢሆን በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰተውን ከግምት ውስጥ በማስገባት እና ተከሳሹ የገደላቸው የአገሪቱን ሉዓላዊነት ጠባቂ የሆነውን የመከላከያ ጠቅላይ አዛዥ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት” መሆኑን በዛሬው ችሎት ላይ ገልጿል። የፌደራል ማረሚያ ቤት ቅጣቱን እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ የሰጠው ፍርድ ቤቱ፤ ግራ ቀኙ የይግባኝ መብት እንዳላቸው አስታውቋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የተከሳሽ ጠበቆች በውሳኔው ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል። 

ተከሳሽ አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፤ ጄነራል ሰዓረን እና ሜጀር ጀነራል ገዛኢን “ተኩሶ በመግደል” ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው ግንቦት 27፤ 2013 ነበር። ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ በጀኔራል ሰዓረ መኖሪያ ቤት የተከሰተው የወንጀል ድርጊት፤ የኢትዮጵያ መንግስት “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” ባለው እና ሰኔ 15 በባህር ዳር ከተማ በአማራ ክልል አመራሮች ላይ የተፈጸመው ግድያ አንድ አካል እንደሆነ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ባለፈው ግንቦት ወር አስታውቆ ነበር።   

ቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

በባህርዳር በተፈጸመው ጥቃት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ምግባሩ ከበደ እና የርዕሰ መስተዳድሩ የአደረጃጀት አማካሪ የነበሩት አቶ እዘዝ ዋሴ መገደላቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ባለፈው ወር ባወጣው መረጃ፤ “አስር አለቃ መሳፍንት በቀድሞው የአማራ ክልል የሰላም እና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ በነበሩት ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ በተመራው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል የማፍረስ ተግባር” ተሳታፊ እንደነበር አስታውቋል።  

ተከሳሹ ጄነራል ሰዓረን እና ሜጀር ጄነራል ገዛዒን በሽጉጥ ተኩሶ ከገደለ በኋላ ለማምለጥ ሲሞክር በቁጥጥር ስር የዋለው ሰኔ 15፤ 2011 ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ገደማ ነበር። የአስር አለቃን መሳፍንት ጥጋቡን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ወር መጨረሻ ተከሳሹን ጥፋተኛ ያለው፤ “ዐቃቤ ህግ እንደ ክሱ ያስረዳ እና ተከሳሽ ያላስተባበለ መሆኑን” ካረጋገጠ በኋላ መሆኑን በወቅቱ መግለጹ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)