በሽመልባ እና ህጻጽ መጠለያዎች ለነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞች “የከተማ ስደተኝነት” ዕውቅና መስጠት ተጀመረ

በሃሚድ አወል

በትግራይ ክልል በሚገኙት ሽመልባ እና ህጻጽ በተባሉ የስደተኛ ጣቢያዎች ተጠልለው ለነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞች “የከተማ ስደተኝነት” ዕውቅና መስጠት ተጀመረ። የከተማ ስደተኝነት ዕውቅናውን እየሰጠ ያለው የስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተለው የፌደራል መንግስት ተቋም ነው። 

የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንዳሉት መስሪያ ቤታቸው  ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ጋር በመሆን በሁለቱ የስደተኛ ጣቢያዎች የነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞችን ምዝገባ በማከናወን ላይ ይገኛል። ከትናንት በስቲያ ረቡዕ በተጀመረው በዚሁ ምዝገባ እስካሁን ከ500 በላይ ስደተኞች መመዝገባቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ከምዝገባው ጎን ለጎን ለስደተኞቹ “የከተማ ስደተኝነት ፍቃድ” አንድ ላይ እየተሰጣቸው እንደሚገኝም አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል። ይህ የተደረገውም “ከጉዳዩ አንገብጋቢነት እና አሳሳቢነት አንጻር” መሆኑንም አስረድተዋል። UNHCR በትናንትናው ዕለት በትዊተር ገጹ ባወጣው መረጃ መሰረት የተመዘገቡ ኤርትራውያን ስደተኞች ለሶስት ዓመታት የሚያገለግል የስደተኛ መታወቂያ ተሰጥቷቸዋል። 

“መታወቂያው ላይ [ስደተኞቹ] አዲስ አበባ ለመኖር እንደተፈቀደላቸው የሚያመላክት ነገር ይኖራል። እሱን የያዘ ማንኛውም ስደተኛ አዲስ አበባ ውስጥ እንደፈለገ መንቀሳቀስ ይችላል” ሲሉ አቶ ተስፋሁን ስለ መታወቂያው ጠቀሜታ አብራርተዋል።

ኤርትራውያኑ “የከተማ ስደተኛ” ሆነው ሲመዘገቡ የሚያገኟቸው ጥቅማ ጥቅሞች እንዳሉም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቃለ አቀባይ ኔቨን ክሬንኮቪች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት የተመዘገቡት ስደተኞች እንደየቤተሰባቸው መጠን የአንድ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ  ከተቋሙ ያገኛሉ፡፡

የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር፤ የኤርትራውያን ስደተኞች ምዝገባ እና እውቅና መስጠት ያስፈለገው “መደበኛ ባልሆነ (informal) መንገድ ወደ አዲስ አበባ የገቡ ስደተኞችን ጉዳይ ስርዓት ማስያዝ በማስፈለጉ” ነው ብለዋል። የኤርትራ ስደተኞች ጉዳይ በአግባቡ ለመያዝ እና ምዝገባውን ለመጀመርም መስሪያ ቤታቸው ቀደም ሲል “ተደጋጋሚ ውይይቶች” ሲያደርግ መቆየቱንም ጠቁመዋል። 

የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ሐምሌ 7፤ 2013 ባወጣው መግለጫ በማይ አይኒ እና አዲ ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞችን “በድጋፍ ላይ የተመሰረተ የከተማ ስደተኝነት እውቅና” እንደሚሰጥ መግለጹ ይታወሳል። በትግራይ ክልል ባለው ውጊያ ምክንያት የሽመልባ እና ህጻጽ የመጠለያ ጣቢያዎች “ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን” ተከትሎ፤ በካምፖቹ ተጠልለው ከነበሩ 20 ሺህ ስደተኞች ውስጥ ከ7ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ማይ አይኒ እና አዲ ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች መሸሻቸውን UNHCR ባለፈው መጋቢት ወር አስታውቆ ነበር።  

ውድመት ደረሰባቸው የተባሉትን ሁለቱን የመጠለያ ጣቢያዎችን ለቅቀው ከወጡ ስደተኞች ውስጥ፤ ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ሽሬ፣ መቀሌ፣ አፋር እና አዲስ አበባ መሄዳቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በዚሁ መግለጫው ጠቅሷል። የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቃል አቃባይ፤ ቀደም ሲል ከሁለቱ የመጠለያ ካምፖች የወጡ 5,500 ኤርትራውያን ስደተኞች በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። “በምዝገባ ሂደቱ ሁሉም ይሳተፋሉ ብለን እንጠብቃለን” ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ በሐምሌ 7 መግለጫው፤ በሽመልባ እና ህጻጽ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ለደረሰው ጥቃት “የህወሓት ኃይሎችን” ተጠያቂ አድርጓል። በዚሁ ጥቃት፤ በሽመልባ እና በህጻጽ የስደተኛ አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ እና ስደተኞች ወደተለያዩ አካባቢዎች እንዲበተኑ ምክንያት ሆኗል ሲል ኤጀንሲው ወንጅሏል። መስሪያ ቤቱ ሐምሌ 15፤ 2013 ባወጣው መግለጫ ደግሞ፤ የአማጺው ቡድን ኤርትራውያን ስደተኞችን ወደተዘጉት ሽመልባ እና ህጻጽ መጠለያ ጣቢያዎች ለማዘዋወር “ሙከራዎች በማድረግ ላይ ናቸው” የሚል ክስ ሰንዝሮ ነበር። 

ከኢትዮ-ኤርትራ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የሽመልባ ስደተኛ ጣቢያ፤ በ1996 ዓ.ም. የተመሰረተ ነበር። ኤርትራውያን ስደተኞችን ለማስተናገድ በትግራይ ክልል ከተመሰረተው ከዚህ የመጀመሪያ ስደተኛ ጣቢያ በመቀጠል፤ ኢትዮጵያ ሶስት ተጨማሪ መጠለያዎችን በክልሉ ከፍታ ስደተኞችን ስትቀበል ቆይታለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)