ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ የተከሰሰችው ላምሮት ከማል ጥፋተኛ ተባለች

በሃሚድ አወል

ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ የተከሰሰችው ላምሮት ከማል “በአደጋ ላይ የሚገኝ ሰውን ባለመርዳት” ወንጀል ጥፋተኛ ተባለች። የጥፋተኝነት ውሳኔውን ዛሬ ሐሙስ ታህሳስ 14 ያስተላለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ነው።

ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔውን ያስተላለፈው ተከሳሿ የተከሰሰችበትን ወንጀል ሊከላከልላት የሚችል የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ ባለማቅረቧ መሆኑን በዛሬ የችሎት ውሎ ገልጿል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሿ የመከላከያ ማስረጃ እንድታቀርብ ባለፈው ህዳር ወር ወስኖ ነበር። 

ነገር ግን ተከሳሿ ላምሮት በችሎት ቀርባ መከላከያ ማስረጃ እንደሌላት ገልጻ፤ ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን ማስረጃ መርምሮ ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቃ ነበር። ዛሬ ታህሳስ 14 ቀን መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት የተሰየመው ችሎቱ ተከሳሽ ወንጀሉን “ያላስተባበለች” መሆኑን ጠቅሷል። 

ላምሮት ከማል በቅድሚያ ክስ የቀረበባት የወንጀል ድርጊት እንዲፈጸም በማመቻቸት “በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን” ነበር። ጉዳዩን ሲመለከት የነበረው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ባስተላለፈው የፍርድ ውሳኔ፤ የዐቃቤ ህግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች “ተከሳሿ የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸሟ አያስረዱም” በማለት ላምሮት ከማልን በነጻ አሰናብቷት ነበር።

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የተቃወመው ዐቃቤ ህግ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ወስዶት ነበር። የይግባኝ አቤቱታ የቀረበለት ፍርድ ቤቱ ከሁለት ወራት በፊት ጥቅምት 10፤ 2014 በነበረ የችሎት ውሎ፤ ተከሳሽ “አደጋ ላይ የሚገኝን ሰው ባለመርዳት” ወንጀል በስር ፍርድ ቤት በኩል እንድትከላከል ብይን ሰጥቷል። 

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ብይንን ተከትሎ፤ በሽብር ወንጀል ተከስሳ የነበረችው ላምሮት ከማል የተከሰሰችበት አንቀጽ ተሻሽሎ በስር ፍርድ ቤት ጉዳዩዋ መታየት ቀጥሏል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሿ በአምስት ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንድትለቀቅ በወሰነው መሰረትም፤ ላምሮት ጉዳዩዋን ስከታተል የቆየችው በውጭ ሆና ነው።

ሆኖም ዛሬ ተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላለፈው የከፍተኛው ፍርድ ቤት፤ ተከሳሿ የቅጣት ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማረፊያ ቤት እንድትቆይ ወስኗል። ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን ለመስጠት ቀጠሮ የሰጠው ለነገ አርብ ታህሳስ 15፤ 2014 ነው። 

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎው የከሳሽ እና ተከሳሽ ወገኖች የቅጣት አስተያየት እንዲያቀርቡ ጠይቋል። ከሳሽ ዐቃቤ ህግ የቅጣት አስተያየት ይዞ ባለመቅረቡ፤ ፍርድ ቤቱ ይህንኑ ዛሬ ከሰዓት በጽሁፍ እንዲያስገባ አዝዟል።  

የተከሳሽ ተከላካይ ጠበቃ በበኩላቸው ለፍርድ ቤቱ ባለ አንድ ገጽ የቅጣት አስተያየት አቅርበዋል። ጠበቃው በቅጣት አስተያየታቸው ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ሲሰጥ ተከሳሿ ለአንድ አመት ከአምስት ወር በማረሚያ ቤት መቆየቷን ከግምት ውስጥ እንዲያስገባ ጠይቀዋል። ላምሮት ጥፋተኛ የተባለችበት የወንጀል አንቀጽ፤ ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል እስር ወይም መቀጮ የሚያስፈርድ ነው። 

ላምሮት ለእስር የበቃቸው በሰኔ 2012 ከተፈጸመው የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ነው። ድምጻዊው በሚያሽከረክረው መኪና ውስጥ አብራው የነበረችው ተከሳሿ፤ በቁጥጥር ስር የዋለችው የወንጀል ድርጊቱ በተፈጸመበት ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ነበር። 

ድምጻዊውን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው አንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ መወሰኑ ይታወሳል። ፍርድ ቤቱ ሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹን በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣም ውሳኔ ማስተላለፉ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)