የጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ በስር ፍርድ ቤት በድጋሚ እንዲታይ ታዘዘ

በሃሚድ አወል

የአሐዱ ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያ አርታኢ የሆነው ክብሮም ወርቁ “አካልን ነጻ የማውጣት” (habeas corpus) አቤቱታ በስር ፍርድ ቤት በድጋሚ እንዲታይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 4 ትዕዛዙን ያስተላለፈው፤ የስር ፍርድ ቤት አቤቱታውን በተመለከተ የሰጠው ውሳኔ “ህግን መሰረት ያደረገ አይደለም” በማለት ነው። 

ጋዜጠኛ ክብሮም በዋስትና ከእስር እንዲፈታ ባለፈው ህዳር ወር በፍርድ ቤት ቢወሰነለትም፤ በውሳኔው መሰረት ከእስር ባለመለቀቁ በጠበቃው አማካኝነት “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ ለስር ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር። አቤቱታው የቀረበለት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ የፍትሐ ብሔር ችሎት፤ “የዋስትና መብቱ የተጠበቀለትን ግለሰብ፤ በአካል ነጻ ማውጣት አቤቱታ እንዲፈታ ሊጠየቅ አይችልም” በሚል አቤቱታውን ውድቅ አድርጎታል። 

በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር የተሰኙት የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ፤ ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ላይ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለዋል። ጠበቃው “የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ መስጠት ሲገባው፤ ስልጣን የለኝም በማለት የሰጠው ውሳኔ እንዲሻርላቸው” የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ጠይቀዋል።

የይግባኝ አቤቱታውን ሲመለከት የነበረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎቱ፤ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ያስተላለፈው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን በመጥቀስ ነው። ባለፈው ዓመት የጸደቀው ይህ አዋጅ፤ የፌደራል ፍርድ ቤቶች “ተገዶ የመያዝ ሕጋዊነትን ለማጣራት የሚቀርብ አቤቱታ” ላይ የዳኝነት ስልጣን እንዳላቸው ደንግጓል። 

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ያስተላለፈው “ወደ ስረ ነገሩ ሳይገባ ነው” ያለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ በይግባኝ ባይ እና ጋዜጠኛውን አስሮ ሲመረምር በቆየው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መካከል ያለውን ክርክር የስር ፍርድ ቤት “በመምራት ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል” ሲል አዝዟል። 

በስር ፍርድ ቤት በነበረው ክርክር፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን “የፍርድ ቤት ውሳኔን ባለማክበር” ጋዜጠኛ ክብሮምን “በኃይል አስገድዶ በመያዝ ከእስር ቤት እንዳይፈታ ከልክሏል” የሚል ውንጀላ ቀርቦበታል። የጋዜጠኛ ክብሮም ጠበቃ ይህን በመንተራስም “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ ለፍርድ ቤትና አስገብተዋል። 

ለዚህ አቤቱታ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የዛሬ ወር ታህሳስ 4፤ 2014 ለፍርድ ቤት በጽሁፍ በሰጠው መልስ ጋዜጠኛ ክብሮም “በኮሚሽኑ በሚገኙ የተጠርጣሪ ማቆያም ሆነ በኮሚሽኑ እውቅና ስር የሌለ” መሆኑን ገልጾ ነበር። ፖሊስ ይህን ምላሽ ቢሰጥም የጋዜጠኛው ቤተሰቦች ግን “ክብሮም ዋስትናው ተከብሮ ከእስር ተፈትቷል ቢባልም ያለበት ቦታ እንደማይታወቅ” ለፍርድ ቤት አቤት ብለዋል።  

ጋዜጠኛው ክብሮም በ15 ሺህ ብር በዋስትና እንዲፈታ፤ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የተወሰነለት ህዳር 3፤ 2014 ነው። በችሎቱ ውሳኔ ቅር የተሰኘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ውሳኔው በመቃወም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ቢልም፤ ችሎቱ የፖሊስን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔን ማጽናቱ ይታወሳል።

ጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ጥቅምት 16 ነበር። ጋዜጠኛው ለእስር የተዳረገው በሚሰራበት አሃዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ፤ ተሰርቶ በተላለፈ ዜና ነው። ጥቅምት 12፤ 2014 የተላለፈው ይህ ዜና “የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል የምትገኘውን የሐይቅ ከተማ መቆጣጠራቸውን” የሚገልጽ ነበር።

ዜናው በስርጭት ላይ ከዋለ በኋላ ዜናውን የሰራችው ጋዜጠኛ ሉዋም አታክልቲ እና በዕለቱ ተረኛ አርታኢ የነበረው ክብሮም ወርቁ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ዜናው በተላለፈበት ቀን በቁጥጥር ስር ውላ የነበረችው ጋዜጠኛ ሉዋም አታክልቲ ከሁለት ወር በፊት ህዳር 3፤ 2014 በ10 ሺህ ብር ዋስትና መፈታቷ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)