የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ውሳኔ አስተላለፈ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለስድስት ወር ተደንግጎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ወሰነ። ምክር ቤቱ ዛሬ ረቡዕ ጥር 18 ባካሄደው ስብስባ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጻሚነት ጊዜ እንዲያጠር ያደረገው አዋጁን ማውጣት “የግድ አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎ የነበረው ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑ እና ስጋቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ስራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ” ውሳኔውን ማስተላለፉን አስታውቋል። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላው ኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚደረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገው ከሶስት ወር በፊት ጥቅምት 24፤ 2014  ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገገው “የሃገርን ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል” በሚል ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚቆይበት የስድስት ወር ጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዋጁ ተፈጻሚነት ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ ሊወስን እንደሚችልም በድንጋጌው ሰፍሯል። 

በዚህም መሰረት የአዋጁን ተፈጻሚነት ቀሪ የሚያደርግ የውሳኔ ሀሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ ባሰራጨው መረጃ አመልክቷል። በውሳኔ ሀሳቡ ላይ “በጥልቅ” መወያየቱ የተገለጸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ ይጸድቅ ዘንድ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ማስተላለፉንም ጽህፈቱ ቤት ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)