በሃሚድ አወል
የአሃዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ዜና አርታኢ ክብሮም ወርቁ ከ92 ቀናት እስር በኋላ ከእስር ተፈታ። ጋዜጠኛው ዛሬ ረቡዕ ጥር 18፤ 2014 ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ከእስር የተፈታው በመታወቂያ ዋስትና ነው።
ጋዜጠኛ ክብሮም ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ከእስር ሲለቀቅ ጠበቃው፣ አባቱ፣ ሁለት እህቶቹ፣ ሌሎች ዘመዶች እና የጋዜጠኛው ጓደኞች በቦታው ተገኝተው አቀባበል አደርገውለታል። ላለፉት ሁለት ወራት ክብሮም ያለበት ቦታ እንደማይታወቅ ቤተሰቦቹ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተው ነበር።

ከሶስት ወራት በፊት ጥቅምት 16 በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ክብሮም፤ ለመጀመሪያዎቹ 20 ቀናት ገደማ ታስሮ የቆየው በተለምዶ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በሚባለው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ነበር። ከህዳር 9 ጀምሮ ላለፉት 70 ቀናት ደግሞ የታሰረው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኘው አባ ሳሙኤል ማረሚያ ቤት እንደነበር ጋዜጠኛው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል።
ጋዜጠኛ ክብሮም ከአባ ሳሙኤል ማረሚያ ቤት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት የተዘዋወረው በዛሬው ዕለት ስድስት ሰዓት አካባቢ ነበር። ጋዜጠኛው ከእስር ስለተፈታበትም ሆነ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስለተዘዋወረበት ምክንያት ከፖሊስ ምንም አይነት ነገር እንዳልተነገረው ገልጿል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክብሮም በ15 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ የወሰነለት ከሁለት ወራት በፊት ነበር። የጋዜጠኛው ቤተሰቦች በፍርድ ቤት የተጠየቀውን የዋስትና ገንዘብ ቢከፍሉም፤ ክብሮም ከእስር ሳይፈታ መቅረቱን ለፍርድ ቤት ጭምር ሲያመለክቱ ቆይተዋል።

ይህን ተንተርሶም፤ የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ላይ “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ ለፍርድ ቤት አቅርበው ነበር። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለአቤቱታው በፍርድ ቤት በሰጠው ምላሽ፤ ጋዜጠኛ ክብሮም “በኮሚሽኑ በሚገኙ የተጠርጣሪ ማቆያም ሆነ በኮሚሽኑ እውቅና ስር የሌለ” መሆኑን ማስታወቁ አይዘነጋም።
ጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው፤ ከመታሰሩ ሶስት ቀናት በፊት በሚሰራበት አሃዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ተሰርቶ በተላለፈ ዜና ነው። “የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል የምትገኘውን የሐይቅ ከተማ መቆጣጠራቸውን” የሚገልጸው ይህ ዜና በስርጭት ላይ ከዋለ በኋላ፤ ዘገባውን የሰራችው ጋዜጠኛ ሉዋም አታክልቲ የዚያኑ ዕለት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንድትውል ተደርጓል።
እርሷን ተከትሎ በዕለቱ ተረኛ አርታኢ የነበረው ክብሮም በተመሳሳይ መልኩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፤ የጊዜ ቀጠሮ ጉዳዩንም በፍርድ ቤት ሲከታተል ቆይቷል። የሁለቱን ጋዜጠኞች ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
በዚህም መሰረት ጋዜጠኛ ሉዋም ህዳር 3፤ 2014 በ10 ሺህ ብር ዋስትና ተፈትታለች። ክብሮም በፍርድ ቤት የዋስትና መብቱ እንዲከበር ከተወሰነለት ከሁለት ወር በኋላ የተለቀቀው፤ በጠበቃው የቀረበው “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ በፍርድ ቤት ክርክር ላይ ባለበት ወቅት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)