በሃሚድ አወል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ሊያጸድቅ ነው። የተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔውን የሚያጸድቀው ነገ ማክሰኞ የካቲት 8፤ 2014 በሚያካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው ነው።
ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባውን የጠራው፤ የፓርላማ አባላት ለአንድ ወር ያህል ለዕረፍት በመውጣታቸው ነው። የፓርላማ አባላቱ በየካቲት ወር እንዲሁም ከሐምሌ እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ባለው ጊዜ ከመረጣቸው ህዝብ ጋር እንዲገናኙ የዕረፍት ጊዜ ይሰጣቸዋል።
በነገው የምክር ቤቱ ስብሰባ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በሚመለከት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባጸደቀው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ማብራሪያ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ማብራሪያ የሚሰጡት የተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደሚሆኑ ከተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለስድስት ወር ተደንግጎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀሪ እንዲሆን የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ያጸደቀው ከ20 ቀናት በፊት ነበር። ከጥቅምት 23፤ 2014 ጀምሮ በስራ ላይ የዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ የተፈጻሚነት ጊዜው ስድስት ወራት እንደሆነ የተገለጸ ቢሆንም፤ አዋጁ ሶስት ወራት ሊሞላው አምስት ቀናት ሲቀሩት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የአዋጁ ተፈጻሚነት ጊዜ እንዲያጥር ተወስኗል።
በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው “የሃገርን ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል” በሚል ነበር። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የወሰነው፤ አዋጁን ማውጣት “የግድ አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎ የነበረው ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑ እና ስጋቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ስራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ” መሆኑን በወቅቱ አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)