በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ኮንሰርት ሊካሄድ ነው

በሃሚድ አወል

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ፤ በቀጣዩ ወር ሚያዚያ 15፤ 2015 የሙዚቃ ኮንሰርት ሊካሄድ ነው። ከኮንሰርቱ የሚገኘው ገቢ በቦረና ዞን ውሃ ጉድጓድ ለማስቆፈር እንደሚውል በኮንሰርቱ ላይ የሚሳተፉት አርቲስቶች ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 5 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

የኦሮሞ አርቲስቶች ማህበር እና “ቪዥን ኢንተርቴይመንት” የተባለ የፕሮዳክሽን ድርጀት ያዘጋጁት ይህ የሙዚቃ ኮንሰርት፤ የሚካሄደው በአዲስ አበባው ሚሊኒየም አዳራሽ እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልጸዋል። ከኮንሰርቱ በተጨማሪም በአጭር የጽሁፍ መልዕክት፣ በቴሌቶን እና በባንክ ሂሳብ ገንዘብ ለማሰባሰብ ማቀዳቸውን አስተባባሪዎቹ በኢሊሌ ሆቴል በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።

“ምን ያህል ገንዘብ ለመሰብሰብ አቅዳችኋል?” በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ፤ በመግለጫው ላይ የተገኘው ድምጻዊ ታደለ ገመቹ “ምን ያህል የውሃ ጉድጓድ ነው የሚያስፈልገው? የሚለውን አላወቅንም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። ድምጻዊው አክሎም “ያለንን ገንዘብ ካወቅን በኋላ በቦረና እና አካባቢው የጉድጓድ ውሃ እናወጣለን” ብሏል።

ፎቶዎች፦ ቪዥን ኢንተርቴይመንት

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለቦረና ከሚደረገው ድጋፍ ጋር በተያያዘ፤ ባለፈው ቅዳሜ ያሳለፈው ክልከላን የተመለከተ ጥያቄ ለአስተባባሪዎቹ ቀርቦላቸዋል። ክልሉ ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ፤ “ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እውቅና ዉጭ በቡድንም ሆነ በተናጠል ድጋፍ ማድረግ የማይፈቀድ መሆኑን” ገልጾ ነበር።

ከክልሉ መግለጫ በፊት ከመንግስት እውቅና ማግኘታቸውን የገለጸው ድምጻዊ ቀመር ዩሱፍ፤ “ክልከላው እኛን የሚመለከት አይመስለኝም” ሲል መልሷል። “Lammi Koof” [ለወገኔ] በሚል ስያሜ በሚካሄደው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ፤ ታዋቂዎቹ የኦሮሚኛ ቋንቋ ሙዚቀኞች ቀመር የሱፍ፣ ታደለ ገመቹ እና ጃምቦ ጆቴን ጨምሮ ሌሎች ድምጻዊያንም እንደሚሳተፉ አዘጋጆቹ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)