በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤን ያሰናከሉ የህግ አስፈጻሚ አካላት ላይ ፍትሕ ሚኒስቴር ክስ እንዲመሰርት ጠየቀ። በመንግስት መስሪያ ቤቶች ስር የሚተዳደሩ የስብሰባ ቦታዎች እና አዳራሾች ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ክፍት እንዲሆኑም ውሳኔ አሳልፏል።
ቦርዱ ይህን ያስታወቀው፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ያጋጠሙ መስተጓጎሎችን በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 6፤ 2015 በአዲስ አበባው ሃይሌ ግራንድ ሆቴል በሰጠው መግለጫ ነው። በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ መሰረት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ቢያንስ በሶስት ዓመት አንድ ጊዜ ማካሄድ አለባቸው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ግዴታቸውን ለመፈጸም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወቅት መስተጓጎል እየገጠማቸው እንደሚገኝ ምርጫ ቦርድ ገልጿል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ አሁን በስራ ላይ የሚገኘው ስራ አመራር ቦርድ ኃላፊነት ከወሰደበት ጊዜ ጀምሮ፤ ባልተለመደ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ከማድረጋቸው በፊት እና በኋላ እስር፣ እንግልት እና የማዋከብ ተግባራት ተፈጽሞባቸዋል” ሲል ቦርዱ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል።
ባለፈው እሁድ ጠቅላላ ጉባኤውን ሊያካሄድ የነበረው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ስብሰባውን ሊደርግበት የነበረበት ጋምቤላ ሆቴል ስብሰባውን ማስተናገድ እንደማይችል በመግለጹ ጉባኤውን ሳያካሄድ ቀርቷል። እናት ፓርቲም በተመሳሳይ መልኩ ከሳምንት በፊት የካቲት 26 ሊያካሄደው የነበረው ጠቅላላ ጉባኤ መስተጓጎሉ ይታወሳል። የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት በዕለቱ በሰጡት መግለጫ “ ‘ከበላይ አካል በመጣ ትዕዛዝ መሰብሰብ አትችሉም’ መባላቸውን አስታውቀው ነበር።
የሁለቱን ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤዎች ለመታዘብ በስፍራው የነበሩ የምርጫ ቦርድ ተወካዮች፤ ክስተቶቹን በቅርበት የተከታተሉ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላትንም አነጋግረው ነበር። የእናት ፓርቲ ጉባኤ፤ ቦርዱ ለጊዜው ስሙን ለይቶ ባላረጋገጠው “የህግ አስፈጻሚ ኃላፊ ትዕዛዝ እንዳይካሄድ መደናቀፉን” በዛሬው የምርጫ ቦርድ መግለጫ ላይ ተመላክቷል።
ቦርዱ በዚሁ መግለጫው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ካደረጉ በኋላም “በእስር እንግልት እና የማዋከብ ተግባራት” እንደተፈጸሙባቸው አስፍሯል። ባለፈው እሁድ የምስረታ ጠቅላላ ጉባኤው ያካሄደው የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ ሁለት አስተባባሪዎች፤ ከትላንት በስቲያ ሰኞ መጋቢት፤ 2015 በፌደራል ፖሊስ መታሰራቸውን በመግለጫው ለማሳያነት ቀርቧል።
የጎጎት ፓርቲ አስተባባሪዎች በፖሊስ የተያዙት፤ የፓርቲውን የጠቅላላ ጉባኤ ሰነዶች እንደያዙ መሆኑን ቦርዱ ገልጿል። የፓርቲው አስተባሪዎች ትላንት ማክሰኞ ለደቡብ ክልል ፖሊስ ተላልፈው መሰጠታቸውንም ቦርዱ አክሏል። የደቡብ ክልል ፖሊስ የጎጎት ፓርቲ አስተባባሪዎች “በአስቸኳይ” አንዲፈታ ቦርዱ በዛሬው መግለጫው አሳስቧል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የተፈጸሙት እነዚህ ተግባራት፤ “ቦርዱ የተቋቋመበትን መሰረታዊ ስራ እንዳይሰራ የሚያደርግ” መሆኑን አጽንኦት የሰጠው ምርጫ ቦርድ፤ ክልከላው “በመድብለ ፓርቲ ስርዓት የማሳደግ የሙከራ ሂደት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና የሚያስከትል ይሆናል” ሲል አስገንዝቧል። የዛሬውን መግለጫ ከምክትላቸው ጋር በመሆን የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ “ጥበቃ ሊያደርግ የሚገባው የጸጥታ ኃይል ጥበቃውን ትቶ ወደ ማሰናከል ስራ መግባት እንደ ተራ ነገር የሚወሰድ አይደለም። እንደ ወንጀል ተግባር የሚወሰድ ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የወንጀል ህግ፤ “ስብሰባን ወይም ጉባኤን ማወክ” ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል። የወንጀል ህጉ “ጉባኤው የፖለቲካ፣ የአስተዳደር፣ የህግ አስፈጻሚነት ወይም የዳኝነት ጠባይ ያለው ቢሆንም፤ ቅጣቱ ከሶስት ወር የማያንስ ቀላል እስራት እና ከአምስት መቶ ብር የማያንስ መቀጮ” እንደሚሆን አስቀምጧል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ጋር በተያያዘ የህግ አስፈጻሚ አካላቱ ወሰዱት የተባሉት እርምጃ፤ በምርጫ አዋጁ የተጣለባቸውን “የመተባበር ግዴታ” ያለመወጣታቸውን እንደሚያሳይ በዛሬው የምርጫ ቦርድ መግለጫ ላይ ተነስቷል። ከመተባበር ግዴታ በተጨማሪም ፓርቲዎች በምርጫ አዋጁ መሰረት ያለ አድሎ ሊያገኟቸው የሚገቡ አገልግሎቶች መጣሳቸውን የቦርድ ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።
“ፓርቲዎች በምርጫ ጊዜም ሆነ ከምርጫ ጊዜ ውጭ፤ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የመሰብሰቢያ ቦታዎች፣ አዳራሾች፣ እና ስቴዲዬሞችን እኩል የመጠቀም፤ በነጻ የማግኝት መብት አላቸው” ያሉት ብርቱካን፤ “እስካሁን በአደባባይ ወጥተን በተለያየ ሁኔታ ለመንግስት ኃላፊዎች ስላላሳወቅናቸው፤ ‘ይህን ግዴታቸው አላወቁ ይሆናል’ በሚል እኛ ውሳኔ አሳልፈናል” ሲሉ ቦርዱ ለችግሩ መፍትሔ ለማበጀት የወሰደውን እርምጃ አብራርተዋል።
በ2013 ዓ.ም. የወጣው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ፤ የመንግስት አካላት የስብሰባ አዳራሾችን ያለ አድልዎ እንዲገለገሉባቸው ለማድረግ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል። ይህን አዋጅ መሰረት በማድረግ ምርጫ ቦርድ፤ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ስር የሚተዳደሩ ስብሰባ ቦታዎች እና አዳራሾች ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ክፍት እንዲሆኑ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል። ቦርዱ የሰጠው ይህ ውሳኔ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እና በክልል ፕሬዝዳንቶች ጽህፈት ቤት በኩል ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ መስጠቱንም ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]