የብልጽግና ፓርቲ አባላት ብዛት 13.5 ሚሊዮን መድረሱን ፕሬዝዳንቱ አስታወቁ   

የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባላት ብዛት 13.5 ሚሊዮን መድረሱን የፓርቲው ፕሬዝዳንት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ፓርቲው ባለፉት ወራት በመቶ ሺህ አባላቱ ላይ “የማጥራት” እርምጃ መውሰዱን የገለጹት አብይ፤ ወደፊትም ተመሳሳይ አካሄድ መከተል እንደሚያስፈልግ ጥቆማ ሰጥተዋል።

አብይ ይህን ያሉት ካለፈው ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ ለሚገኘው የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሰጡት ገለጻ ነው። የማዕከላዊ ኮሚቴው መደበኛ ስብሰባ እስከ ነገ ማክሰኞ ግንቦት 29፤ 2015 ድረስ እንደሚቆይ የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ከሳምንት በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር።

የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና ሚኒስትሮችን ያካተተው የብልጽግና ፓርቲ  ማዕከላዊ ኮሚቴ ያለው የአባላት ብዛት 225 ነው። ለእነዚሁ አባላት የፓርቲው ፕሬዝዳንት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሰጡት “ገለጻ” መቼ እንደተከናወነ ባይገለጸም፤ ትላንት እና ከትላንት በስቲያ በብሔራዊው፣ በክልል እና ለመንግስት ቅርበት ባላቸው ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሁለት ክፍል ተከፋፍሎ ለተመልካች ቀርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሁለት ሰዓታት ገደማ በወሰደው በዚሁ ገለጻቸው፤ የሚመሩት መንግስት እና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት የሰሯቸውን እና ሊያከናውኗቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል። ጦርነት፣ ድርቅ እና የኮሮና ወረርሽኝን ጨምሮ ሌሎች ፈተናዎችን ገዢው ፓርቲ እና መንግስት ባለፉት ዓመታት መጋፈጣቸውንም አብራርተዋል። 

አብይ ወቅታዊውን የፓርቲያቸውን አባላት ብዛት ጉዳይ የጠቀሱት፤ “የኢንተርፕሪዩነራል መንግስትን” የመፍጠር አስፈላጊነት ባስረዱበት የገለጻቸው ክፍል ላይ ነው። የብልጽግና ፓርቲ “የሚፈጥር እና ውጤታማ ስራ የሚሰራ መንግስት” ለመፍጠር ተግባራዊ ማድረግ ከሚገባው ነገር አንዱ “ስክነት” መሆኑን አብይ ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ ተናግረዋል።  “እኛ ብዙዎቻችን በመተባበር፣ በመደመር አምነን ሊሆን ይችላል። ስንጀምር ሀሳባችን ትንሽ ሊሆን ይችላል” ያሉት አብይ፤ ሀሳብ እያደገ፣ የፓርቲ አባላት ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ግን ነገሮችን “በሰከነ መንገድ” ማየት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

“ዝም ብሎ ብርጭቆ ተሰበረ – ጫጫታ፣ ውሃ ተደፋ – ጫጫታ። [ይህ] አያስፈልግም። ስክነት ያስፈልጋል። ብዙ ነገር ስለምንችል አሁን በጣም በሰከነ መንገድ ነገር ማየት ያስፈልጋል። ለሁሉ ነገር react ማድረግ አይቻልም። ለሁሉ ነገር ምላሽ መስጠት ተገቢ አይደለም። ስትበቁ መስከን ይጠይቃል። ‘ዝም ያለ ውሃ ጥልቀት አለው’ ይባላል። ስክን ማለታችን የማድረግ አቅማችንን የሚሳይ እንጂ መድከማችንን አያሳይም። አንዳንዱን ቸል ብሎ ማለት ያስፈልጋል። መስከን ያስፈልጋል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።

ብልጽግና ፓርቲን “በአፍሪካ ትልቁ” ሲሉ የጠሩት የፓርቲው ፕሬዝዳንት፤ በአሁኑ ወቅት ፓርቲው 13.5 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት በገለጻቸው አስታውቀዋል። ብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በመጋቢት 2014 ባካሄደበት ወቅት፤ ፓርቲው ያሉት አባላት ብዛት 11 ሚሊዮን እንደሆነ አብይ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ላይ ጠቅሰው ነበር። የአብይ የአሁኑ ገለጻ፤ 2.5 ሚሊዮን አዳዲስ አባላት ባለፈው አንድ ዓመት ገደማ ጊዜ ውስጥ ገዢውን ፓርቲ መቀላቀላቸውን ያመለከተ ሆኗል።

በይፋ ከተመሰረተ ሶስት ዓመት ከመንፈቅ የሞላው ብልጽግና ፓርቲ ያሉት አባላት ቁጥር በየጊዜው እያሻቀበ ቢመጣም፤ በአባላቱ ብዛት ልክ ያህል ፓርቲው የሚፈልገውን ያህል ስኬት አለማምጣቱን አብይ በገለጻቸው ላይ ጠቁመዋል። “13.5 ሚሊዮን አባል ትልቅ ነው። ከብዙ አፍሪካ ሀገሮች ይበልጣል። ይሄ የወል እውነት ገንብቶ ፈጥሮ፣ ፈጥኖ ቢሄድ ኢትዮጵያ ተአምር ትሰራለች። [ይህ] አልሆነም። ወደዚያ እንዲሄድ ስራ ያስፈልጋል” ሲሉ ለፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አስገንዝበዋል። 

በአሁኑ ወቅት ብልጽግና ፓርቲ እየፈተኑት ከሚገኙት ጉዳዮች አንዱ “የሰርጎ ገብ ፖለቲካ” መሆኑ የጠቀሱት አብይ፤ “ሰርጎ ገቦችን እና ፖለቲካል ነጋዴዎችን ነቅሶ በማውጣት” “ማጥራት” እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። “የሰርጎ ገብ ፖለቲካ አደገኛ ነው” ያሉት አብይ፤ ብልጽግና ፓርቲ ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፉት ስምንት፣ ዘጠኝ ወራት በመቶ ሺህ አባላቱ ላይ የማጥራት እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል። የተወሰደው እርምጃ “በቂ” አለመሆኑንም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)