በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመላው ሀገሪቱ የሚታዩ ግጭቶች “ያላንዳች ቅደመ ሁኔታ ቆመው” “በአስቸኳይ” በምክክር እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበ። ኮሚሽኑ ባለድርሻ አካላትን “በማቀራረብ፣ የልዩነት አጀንዳዎችን ሰብስቦ ለማወያየት እና ለማመካከር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን” አስታውቋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የሚመለከታቸው አካላት ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በምክክር እንዲፈቱ የጠየቀው፤ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 2፤ 2015 በጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። የምክክር ኮሚሽኑ የዛሬውን መግለጫ የሰጠው፤ በትላንትናው ዕለት የኮሚሽኑ ምክር ቤት ያደረገውን ልዩ ስብሰባ ተከትሎ ነው።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በንባብ ባሰሙት መግለጫ፤ ለሀገራዊ ምክክሩ የተሳታፊዎች የተሳታፊዎች ልየታ እየተከናወነ ባለበት ሁኔታ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አየታዩ ያሉ “ደም አፋሳሽ ግጭቶች” የኮሚሽኑን ስራ “አዳጋች እያደረጉበት ይገኛሉ” ብለዋል። በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች “ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ ቆመው”፤ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ “አሉን የሚሏቸውን ልዩነቶች ወይም ጥያቄዎች” “በአስቸኳይ” በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በምክክር እንዲፈቱ” ሲል ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።
በንባብ ከቀረበው ከዚህ መግለጫ በኋላ በጋዜጠኞች ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል፤ ኮሚሽኑ ያቀረበው ጥሪ “ከሰሞኑ በአማራ ክልል ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር የተያያዘ ነው ወይ?” የሚለው ይገኝበታል። “ኦሮሚያ ክልልም [ግጭት] በስፋት ሲካሄድ ነበር። እስከዛሬ ጥሪ አላደረጋችሁም። ዛሬ መንግስት እና በአማራ ክልል የታጠቀው ኃይል ግጭት ሲፈጥሩ መግለጫ ማውጣታችሁ ገለልተኛ ያስብላችኋል ወይ? እናንተ ላይ ጥያቄ አይፈጥርም ወይ?” የሚል ጥያቄ ጋዜጣዊ መግለጫውን ለሰጡ ኮሚሽነሮች ቀርቧል።
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ፕሮፌሰር መስፍን፤ “በተለያዩ የሀገራችን ቦታዎች በተለያየ ጊዜ ግጭቶች ሲከሰቱ ቆይተዋል። ይሄንንም ለመናገር አንድም ጊዜ ወደኋላ ያልነበት ጊዜ አልነበረም” ብለዋል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር አክለውም “ስራችንን ለመቀጠል ከተፈለገ ‘አንዱ እና ዋናው ቅደመ ሁኔታችን ወደ ሰላም መምጣት ነው’ በሚል እንጂ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ላይ በተለይ ትኩረት አድርገን አይደለም [መግለጫውን] ያወጣነው” ሲሉ የኮሚሽኑ መግለጫ ከሰሞኑ በአማራ ክልል ከተከሰተው ሁነት ጋር የተገናኘ አለመሆኑን አብራርተዋል።
ይህን የፕሮፌሰር መስፍንን ማብራሪያ ምክትል ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ጨምሮ ሌሎች የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አስተጋብተውታል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራውን የጀመረው “ተግባብቶ በሰላም በሚኖር ሀገር ላይ አይደለም” ሲሉ ኮሚሽኑ ሲቋቋም የነበረውን አውድ ያስታወሱት ሂሩት፤ “ሀገራዊ ምክክሩን ለማስጀመር ተሳታፊዎች መረጣ እያካሄድን ባለንበት ወቅት፤ ባሰብነው የተረጋጋ ሁኔታ ይሄንን ስራ መቀጠል አልቻልንም” ሲሉ ኮሚሽኑ ያጋጠመውን ችግር ተናግረዋል።
“ችግሮች ነበሩ። ነገር ግን ችግሮቹ እየበረከቱ መጥተው በሚገባው መልኩ ስራችንን ለመስራት የማንችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ነው በሚለው ግምገማ ላይ ተመስርተን ነው ይሄን ጥሪ ያቀረብነው” ሲሉም ምክትል ኮሚሽነሯ የዛሬው መግለጫ የተሰጠበትን ምክንያት አስረድተዋል። ሌላኛው ኮሚሽነር አቶ መላኩ ወልደማርያምም፤ “የትም ቦታ ልንገባ የማንችልበት ደረጃ ላይ ስንደርስ ይሄንን ለህዝባችን ማሳወቅ አለብን ብለን ወስንን” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ “ሁሉን አቀፍ እና አካታች ምክክር” እንዲያሄድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ የተቋቋመው ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በፊት በታህሳስ 2013 ዓ.ም ነው። በአዋጁ ከሰፈሩ የኮሚሽኑ ዓላማዎች መካከል፤ “ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ ተፈትተው አስተማማኝ ሰላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካ እና የማህበራዊ መደላድል ማመቻቸት” አንዱ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]