በአማራ ክልል “ሁሉንም ኃይሎች” ያካተተ “ጊዜያዊ አስተዳደር” እንዲቋቋም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጠየቁ

በሃሚድ አወል

የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በአማራ ክልል “ሁሉንም ኃይሎች” ያካተተ “ጊዜያዊ አስተዳደር” እንዲቋቋም ጠየቁ። አቶ ገዱ በአማራ ክልል ያለውን “ችግር በቅንነት ለመፍታት” ፖለቲካዊ ንግግር መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ወደ ስልጣን ያመጣውን “ለውጥ” ከመሩ ባለስልጣናት አንዱ መሆናቸው የሚነገርላቸው አቶ ገዱ ይህን ማሳሰቢያ የሰጡት፤ በዋነኛነት በአማራ ክልል ተፈጻሚ የሚሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት ከመጽደቁ በፊት ባስደመጡት አስተያየት ነው። የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የፓርላማ ተወካይ የሆኑት አቶ ገዱ፤ ዛሬ በተካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የተገኙት፤ በአማራ ክልል ለተፈጠረው ችግር “በቅንነት” ሃሳባቸውን በማቅረብ “አስተዋጽኦ ለማበርከት” በማሰብ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአማራ ክልልን ለአምስት ዓመታት የመሩት አቶ ገዱ፤ በክልሉ በአሁኑ ወቅት ያለውን ችግር ለመፍታት መፍትሔው “የፖለቲካ ውይይት፤፡ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። “ይህን ችግር በቅንነት ለመፍታት ከተፈለገ መፍትሔው፤ እስካሁን በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ሲሞከር ከርሞ ሀገርን ወደ ከፋ ጥፋት ያመራው ወታደራዊ ኃይል መጠቀም ሳይሆን፤ የፖለቲካ ውይይት ነው የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል አቶ ገዱ።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና በኋላም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የነበሩት አቶ ገዱ፤ በዛሬው የፓርላማ ንግግራቸው አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት “ፖለቲካዊ ችግርን ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በወታደራዊ ኃይል ለመፍታት ይነቀሳቀሳል” ሲሉ ተችተዋል። ፖለቲካዊ ችግሮችን “በኃይል ለመፍታት” ከዚህ ቀደም የታወጁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች እና የተቋቋቀሙ ወታደራዊ ኮማንድ ፖስቶች “ያቃለሉት ችግር የለም” ሲሉም ተደምጠዋል።

አቶ ገዱ ለሁለት ዓመታት የቆውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በማንሳትም፤ “የተወሰነ የሰላም ፍንጭ የታየው በፖለቲካዊ መንገድ ለመፍታት በተሞከረባቸው አካባቢዎች ብቻ ነው” ሲሉ አክለዋል። “የችግሩ መጀመሪያም መጨረሻ ፖለቲካዊ ነው” ያሉት አቶ ገዱ፤ “በአማራ ክልል ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ ከተፈለገ እኔ የሚታየኝ፤ አንደኛ መከላከያ ሰራዊት ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ወደ ካምፕ ይመለስ” ሲሉ መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።

ይህ ምክረ ሃሳብ ከሌሎች የፓርላማ አባላት ጉርምርምታ አስከትሏል። የዛሬውን የፓርላማ ስብሰባ የመሩት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ፤ አቶ ገዱ የሚሰጡት አስተያየት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። ከምክትል አፈ ጉባኤዋ ማሳሰቢያ በኋላ ንግግራቸውን የቀጠሉት አቶ ገዱ፤ ሌላኛውን “መፍትሔያቸውን” በጹሁፍ ካዘጋጁት ወረቀት ላይ በንባብ አስደምጠዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“የአማራ ህዝብ እና የብልጽግና ፓርቲ ግንኑነት በማይጠገንበት ደረጀ ስለተበጠሰ፤ በአስቸኳይ ሁሉንም የአማራ ኃይሎች ያቀፈ ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም ችግሩን ማቃለል ይችላል የሚል እምነት አለኝ” ሲሉ የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር መፍትሔ ነው ያሉትን ተናግረዋል። ከዚህኛው የአቶ ገዱ “የመፍትሔ ሃሳብ” በኋላም የፓርላማ አባላቱ ሌላ ጉርምርምታ አሰምተዋል።

የተወሰኑ የተወካዮች ምክር ቤት አባላትም “የአካሄድ” እና “ስነ ስርዓት” ጥያቄዎች እንዷላቸው ለምክትል አፈ ጉባኤዋ አሳውቀዋል። “የስነ ስርዓት” ጥያቄ እንዲያቀርቡ ዕድል የተሰጣቸው አቶ ኢሳ ቦሩ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ አቶ ገዱ የሚሰጡት አስተያየት “ከአዋጁ ውጭ ነው” ብለዋል። አቶ ኢሳ አክለውም “መንግስትን ከስልጣን ይውረድ እያሉ ነው። መንግስት ከስልጣን የሚወርደው በምርጫ እና ምርጫ ብቻ ነው። ይሄ ትክክል ስላልሆነ ቢታረሙ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከዚህ “የስነ ስርዓት” ጥያቄ በኋላ አስተያየታቸውን የቀጠሉት አቶ ገዱ፤ “ያልኩት ክልሉን ለማስተዳደር የቅቡልነት ችግር ስላለ ሁሉንም በማካተት የጋራ መፍትሔ መፈልግ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ ነው” ሲሉ ቀደም ሲል በመፍትሔነት ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። አቶ ገዱ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ “የምክር ቤት አባላት ይሄንን አዋጅ ማጽደቅ የለባቸውም” ሲሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፓርላማ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

አቶ ገዱ “ይህም ሆኖ የሚጸድቅ ከሆነ…” ብለው ተጨማሪ ማብራሪያ ሊሰጡ ሲሉ፤ ከሌሎች የፓርላማ አባላት “የአካሄድ” ጥያቄ በድጋሚ ተነስቷል። ይህንን ተከተሎም ምክትል አፈ ጉባኤዋ፤ አቶ ገዱ የተሰጣቸውን “ማሳሰቢያ ባለማክበራቸው” አስተያየታቸውን ሳይጨርሱ እንዲያቋርጡ አድርገዋቸዋል። ከአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ ደላንታ ዳውንት ምርጫ ክልል ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ለፓርላማ የተመረጡት አቶ ገዱ ንግግራቸውን እንዲያቋርጡ ሲደረጉ “ብታስጨርሱኝ ጥሩ ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል።

አቶ ገዱ የፓርላማ አባላቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዳያጸድቁት ያቀረቡት ተማጽኖም አልተሳካላቸውም። እርሳቸውን ጨምሮ 16 የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ቢቃወሙትም፤ አዋጁ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማጽደቅ በተጠራው በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ፤ 12 የፓርላማ አባላት ድምጽ ከመሰጠት ተቆጥበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]