በአየር ንብረት ጉዳይ ላይ የሚመክር የመጀመሪያው አህጉር አቀፍ ጉባኤ በናይሮቢ መካሄድ ጀመረ 

በአማኑኤል ይልቃል

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከ20 ገደማ በላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እንደሚገኙበት የሚጠበቀው የመጀመሪያው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፤ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 29፤ 2015 በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ መካሄድ ጀመረ። በዚህ ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ለመቋቋም ስለሚወስዷቸው እርምጃዎች ቃል የሚገቡበት “የናይሮቢ ስምምነት” ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

ኬንያ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በጋራ ያዘጋጁት የአየር ንብረትን የተመለከተው ይህ ጉባኤ፤  በአህጉር አቀፍ ደረጃ ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ለሶስት ቀናት የሚቆየው ጉባኤ በኬንያታ አለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ዛሬ ሲከፈት የኬንያው ፕሬዝዳንን ዊሊያም ሩቶ ባደረጉት ንግግር፤ “አፍሪካ ለከባቢ አየር ለውጥ ያደጉ ሀገራትን ከመውቀስ ባለፈ ያላት አቅም ላይ ትኩረት በማድረግ እርምጃዎችን መውሰድ ላይ ማተኮር ይገባታል” ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለሚከላከሉ ቴክኖሎጂዎች የሚውሉ ጥሬ እቃዎች አፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ የጠቀሱት የኬንያው ፕሬዝዳንት፤ የአፍሪካ ሀገራት እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች እሴት በመጨመር ጥቅም ላይ ማዋል እና ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ዛሬ ጠዋት በተካሄደው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተገኝተዋል። አቶ ኃይለማርያም በጉባኤው የተገኙት በቦርድ ሰብሳቢነት የሚመሩትን የአፍሪካን የግብርና አሰራር ለማሻሻል የሚሰራውን “Alliance for a Green Revolution in Africa” የተሰኘውን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በመወከል ነው። 

በዚሁ ጉባኤ ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ተገኝተው ንግግር እንዲያደርጉ መጋበዛቸውን የጉባኤው መርሃ ግብር ያሳያል። በመርሃ ግብሩ መሰረት ፕሬዝዳቷ ንግግር የሚያደርጉት ነገ ማክሰኞ በሚካሄዱ ሁለት ውይይቶች ላይ ነው፡፡ በጉባኤው መርሃ ግብር ላይ ለውጥ ከመደረጉ በፊት፤ በነገው ዕለት አረንጓዴ እድገትን በተመለከተ ውይይት ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ፕሮግራም ተይዞላቸው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነበሩ።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ የሚገኙበት የነገው የመጀመሪያው ውይይት፤ የከባቢ ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የአፍሪካ ሀገራት እየወሰዷቸው ያሉ እርምጃዎችን የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ ውይይት ላይ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እንዲሁም የጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ ኦዶ ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል፡፡ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ንግግር ያደርጉበታል ተብሎ የሚጠበቀው ሁለተኛው ውይይት የአፍሪካን የምግብ ስርዓት መቀየርን የሚመለከት መሆኑ በጉባኤው ላይ የተሰራጨው መርሃ ግብር ያመለክታል፡፡

ለሶስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ላይ ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ በተጨማሪ የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹምአሰፋ እና የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ በተለያዩ ሁለት ውይይቶች ላይ ንግግር እንዲያደርጉ መርሃ ግብር ተይዞላቸዋል። በአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ከሚጠበቁ ጉዳዮች ውስጥ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው፤ በስብሰባው መጨረሻ ተሳታፊ ሀገራት ያጸድቁታል ተብሎ የሚጠበቀው “የአረንጓዴ እድገት እና የአየር ንብረት ፋይናንስ” የተመለከተው ስምምነት ነው።

በጉባኤው የሚሳተፉ መሪዎች የአፍሪካ ሀገራት የከባቢ አየር ለውጥን ለመከላከል እና ለመቋቋም የሚያስፈልጋቸው ገንዘብ የሚገኝበት መንገድን በተመለከተ አቋም የሚይዙበት እንደሚሆን ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካ ሀገራት እየተጠቀሙ የሚገኙባቸውን የኃይል አማራጮች በመቀየር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችላቸው ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)