በአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ውሎ ምን ጉዳዮች ተነሱ?

በአማኑኤል ይልቃል

በኬንያ ናይሮቢ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ከተገኙ 19 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች መካከል አስራ ሶስቱ በዛሬው የጉባኤው ውሎ ላይ ንግግሮችን አድርገዋል። በጉባኤው ላይ ለመገኘት ትላንት ከሰዓት ናይሮቢ የደረሱት ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፤ የከባቢ አየር ለውጥን በተመለከተ ሀገራቸው ያላትን አቋም ለታዳሚዎች ያስደመጡት የአስር ሀገራት መሪዎች ንግግር ካደረጉ በኋላ ነበር።

እርሳቸውን ቀድመው የመናገር ዕድል ካገኙ መሪዎች መካከል የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ እና የጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ ኦዶ ይገኙበታል። ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ በዛሬው ንግግራቸው ኢትዮጵያ በከባቢ አየር ለውጥ ምክንያት እያጋጠማት ስላለው ድርቅ እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራት በጉዳዩ ላይ መያዝ ስላለባቸው ወጥ አቋም አንስተዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት የከባቢ አየር ለውጥን ለመከላከል እና ለመቋቋም በተለያዩ ዘርፎች ላይ ፕሮጀክቶችን መተግበሩን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቷ፤ ሀገሪቱ ተጨማሪ ፕሮግራሞችን እውን ለማድረግ “ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ” እንደሚያስፈልጋት አስረድተዋል። እነዚህን ፕሮግራሞች ለመደገፍ ቃል የገቡ አጋር አካላትም ቃላቸውን እንዲያከብሩ ጠይቀዋል። 

“የባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት፤ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች እና በዋነኛነት በአፍሪካ ትከሻ ላይ የተከማቸን ታሪካዊ ዕዳ ከማባባስ ይልቅ ዓላማቸውን የሚመጥን ከፍ ያለ ማሻሻያ እንዲያደርጉ አጥብቀን እናሳስባለን” ሲሉም ፕሬዝዳንቷ ተደምጠዋል። አህጉር አቀፉን ጉባኤ እየተሳተፉ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት መካከል አንዷ የሆኑት የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ትላንት በተካሄደ አንድ ውይይት ላይ፤ የከባቢ አየር ለውጥን ለመከላከል እና ለመቋቋም የሚያስፈልገውን ገንዘብ የኢትዮጵያ መንግስት ከሀገር ውስጥ ምንጮች ለመሸፈን እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀው ነበር።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የሚውል ገንዘብ የማሰባሰብ ጉዳይ በኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ተነስቶ ነበር። በዛሬው ዕለት በነበረ አንድ ውይይት ላይ ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ጋር መድረክ የተጋሩት ኢሳያስ፤ የአፍሪካ መሪዎች በሀገራቸው ያለን ሀብት ከመጠቀም ይልቅ ወደ ውጭ “ማማተራቸውን” አንስተው በጠንካራ ቃላት ወቀሳ አሰምተዋል። 

የአፍሪካ መሪዎች “ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካም ሆነ ከሌሎች ቦታዎች” በቢሊዮን የሚቆጠሩ ገንዘቦችን ሲቀበሉ፤ “በራሳቸውን ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ገብነትን እየጋበዙ” መሆኑን ሊያስታውሱ እንደሚገባ የኤርትራው ፕሬዝዳንት አመልክተዋል። “በቢሊዮኖች የሚመጣው ይህ ገንዘብ ተመልሶ ወደዚያው ይሄዳል። ከውጭ የሚመጣውን [ገንዘብ] ለመጠቀም፤ የራስን ሀብት እያንቀሳቀስህ ስለመሆኑ ማረጋገጥ አለብህ” ሲሉም የሀገር ውስጥ ሀብትን ጥቅም ላይ መዋል ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)