የሚኒስትሮች ምክር ቤት የህዝብ በዓላትን፣ የዕረፍት ቀናትን እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን በቀረበለት የአዋጅ ረቂቅ ላይ ግብዓቶችን በማከል እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መራ። ምክር ቤቱ ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት የተደነገገውን የሜዳይ፣ የኒሻን እና የሽልማት አሰጣጥ ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ በሚያስችል የአዋጅ ረቂቅ ላይ ከተወያየ በኋላ በተመሳሳይ ለፓርላማ እንዲተላለፍ ወስኗል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔውን ያሳለፈውን ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 10፤ 2016 ባደረገው መደበኛ ስብሰባው ነው። ምክር ቤቱ በዛሬው ስብሰባው፤ ከሁለቱ አዋጆች በተጨማሪ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን፣ ካሣ የሚከፈልበትን እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን በቀረበለት ማሻሻያ የአዋጅ ረቂቅ ላይም ተወያይቷል።
የአምራች ኢንዱስትሪውን ለማበረታት ባለመ ረቂቅ ፖሊሲ ላይም ተወያይቶ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል። ምክር ቤቱ ከተወያየባቸው የአዋጅ ረቂቆች አንዱ የሆነውና የህዝብ በዓላትን አከባበር የሚመለከተው ድንጋጌ የተዘጋጀው፤ “ለዜጎች ስነ-ምግባርና ስነ-ልቦና ግንባታ እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦቸው ከፍተኛ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ለህዝብ በዓላት እና የእረፍት ቀናት “ሕጋዊ እውቅና መስጠት እና ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ሥርዓታቸውን ጠብቀው በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበሩ ማድረግ የሚገባ በመሆኑ” አዋጁ መዘጋጀቱን በመረጃው ተጠቅሷል። የአዋጅ ረቂቁ፤ የህዝብ በዓላት “የዜጎችን የእርስ በእርስ መልካም ግንኙነት እና መተሳሰብ የሚያጎለብቱ እንዲሆኑ የሚያስችል” ነው ተብሎለታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)