በአማኑኤል ይልቃል
መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ኢትዮ ቴሌኮም፤ በ2015 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት 33.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ። ኢትዮ ቴሌኮም በዚሁ ጊዜ ውስጥ 8.18 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዘገቡም ተገልጿል።
ኢትዮ ቴሌኮም በስድስት ወር አፈጻጸሙ ያገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ19.9 በመቶ እድገት እንዳለው የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ዛሬ ሐሙስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። ተቋሙ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ በጀት ዓመት ያገኘው ገቢ 28 ቢሊዮን ብር ነበር።
በ2014 በጀት ዓመት 61.3 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በዘንድሮው ዓመት ገቢውን ወደ 75.05 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ እቅድ ይዟል። ተቋሙ ባለፈው ስድስት ወራት ያገኘው ገቢ የእቅዱን 96 በመቶ ያሳካ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት የደንበኞች ቁጥርን በማሳደግ የላቀ አፈጻጸም ማሳየቱ በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልጿል። ፍሬሕይወት ለጋዜጠኞች እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው መንፈቅ ዓመት የደንበኞቹን ቁጥር አምስት በመቶ በማሳደግ 70 ሚሊዮን አድርሷል።
ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹን ቁጥር በዚህ ያህን መጠን ያሳደገው፤ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎት መጀመርን ተከትሎ በነበረው “የውድድር ገበያ” ውስጥ መሆኑን ስራ አስፈጻሚዋ አጽንኦት ሰጥተዋል። በሀገሪቱ የቴሌኮም ገበያን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ የቆየው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በዘርፉ ተወዳዳሪ የሆነው ሳፋሪኮም ኩባንያ በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ የስራ አፈጻጸሙን ሲያሳውቅ የዛሬው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)