ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጣሊያን- አፍሪካ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ሮም ገቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 23 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በሚሳተፉበት የጣሊያን- አፍሪካ ጉባኤ ላይ ለመካፈል ዛሬ ቅዳሜ ሮም መግባታቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። በጉባኤው ላይ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይስ አፈወርቂ እና የሶማሊያ አቻቸው ሐሰን ሼክ መሐሙድ ይሳተፋሉ ተብሏል። 

በጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ አነሳሽነት የተዘጋጀው ጉባኤ፤ ሀገሪቱ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በአዲስ መልክ ለመቀየስ እና ወደ አውሮፓ የሚደረግ ስደትን ለመግታት ያለመ መሆኑ ተገልጿል። በዚሁ ጉባኤ ላይ ጣሊያን  ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በኃይል እና በመሰረተ ልማት ዘርፎች ልታደርገው ያቀደችው የኢንቨስትመንት ትብብር ዕቅድ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

አርባ በመቶ የሚሆነውን የተፈጥሮ ጋዝ ኃይል አቅርቦቷን ከአፍሪካ አምራቾች የምታገኘው ጣሊያን፤ ከአህጉሩ የምታገኘውን ድርሻ ወደ 60 በመቶ ከፍ የማድረግ እቅድ እንዳላት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ አስታውቀዋል። ሀገሪቱ ይህን እቅዷን ለማሳካት ከአልጄሪያ ጋር የመጀመሪያውን ስምምነት ባለፈው ሐምሌ ወር አድርጋለች። በቀጣይም ከሞዛምቢክ እና ሴኔጋል ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ለማድረግ እቅድ እንዳላት እኚሁ ምንጭ ተናግረዋል። 

ጣሊያን ለራሷ ጥቅም ላይ ከምታውለው በተጨማሪ የአውሮፓ ሀገራት ከአፍሪካ በቧንቧ መስመር ማጓጓዝ ለሚፈልጉት የተፈጥሮ ጋዝ እና ሃይድሮጅን የኃይል አቅርቦት “ዋነኛ መሸጋገሪያ” ሆና የማገልገል ትልም አላት። በአፍሪካ ያለውን ድርሻ እያሰፋ የሚገኘው “ኤኒ” የተሰኘው እና በሀገሪቱ መንግስት ቁጥጥር ስር ያለው ዓለም አቀፍ የነዳጅ አምራች እና አቅራቢ ኩባንያ፤ ለዚህ እቅድ መሳካት ትልቁን ሚና እንደሚጫወት “ሮይተርስ” የዜና ወኪል በትላንትናው ዕለት ባወጣው ዘገባ አመልክቷል።

ወደ ስልጣን ከመጡ አንድ ዓመት ያለፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ፤ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ቁልፍ አጀንዳ ካደረጓቸው ጉዳዮች መካከል ጣሊያን ከአፍሪካ ያላትን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ማጎልበት ነው። ሜሎኒ የመጀመሪያዋ እንስት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተመረጡ በመንፈቃቸው ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅትም ይህንኑ አንጸባርቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ በሚያዝያ 2015 ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት፤ ሀገራቸው በኃይል ዘርፍ ስለምታደርገው ትብብር እና ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ የሚደረግ ፍልሰትን መግታት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ መነጋገራቸው በወቅቱ ተዘግቦ ነበር። ሜሎኒ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መሪዎች ጋር የሶስትዮሽ ውይይት ማካሄዳቸውም ይታወሳል። 

በውይይቱ መግባባት ላይ ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ጣሊያን እና ኢትዮጵያ “በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የተጠናከረ ትብብር እንዲኖራቸው” ማድረግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በወቅቱ አስታውቀዋል። በዚሁ ውይይት ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን የሚያገናኙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማጠናከር ከመግባባት ላይ መደረሱንም አብይ ገልጸዋል። በጣሊያን በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች፤ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ “በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ” ስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል። 

የዚያን ጊዜውን ውይይት ፍሬያማ እና ውጤት ተኮር” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጠርተውት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሜሎኒ የኢትዮጵያ ጉብኝት ሁለት ወር አስቀድሞ ወደ ሮም በተጓዙበት ወቅትም፤ በተመሳሳይ መልኩ “ውጤታማ ውይይት” ማድረጋቸውን ገልጸዋል። 

አብይ በዚሁ ይፋዊ ጉብኝታቸው፤ የ180 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታ እና ብድርን የሚያካትት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ጋር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ ጋር መፈራረማቸው አይዘነጋም። ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም እና የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ማስፈጸሚያ የሚውል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በወቅቱ መግለጻቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)