በኢትዮጵያ የከተማ አስተዳደር ደረጃ ያሟሉ ከተሞች 275 ብቻ መሆናቸው ተገለጸ  

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ካሏት 2,500 ከተሞች ውስጥ “የከተማ አስተዳደር ደረጃ ያላቸው” 275 ከተሞች ብቻ መሆናቸውን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ። ቀሪዎቹ ከተሞች “በጣም ዝቅተኛ የማዘጋጃ ቤት ደረጃ ያላቸው” እንደሆኑ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። 

ይህ ይፋ የተደረገው የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን በትላንትናው ዕለት ለፓርላማ ባቀረበበት ወቅት ነው። በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ “የክትመት ምጣኔ” አለ ያሉት በሚኒስቴሩ የከተማ አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፋንታ ደጀን፤ ከ10 ዓመት በፊት 1000 ገደማ የነበሩት ከተሞች አሁን ከእጥፍ በላይ መጨመራቸውን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ከተሞች ውስጥ አብዛኞቹ “በጣም ዝቅተኛ የማዘጋጃ ቤት ደረጃ ያላቸው” መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ “ይሄ የሚያሳየን ከገጠር ማዕከልነት ወደ ከተማነት እያደገ የመጣ የክትመት ምጣኔ ሰፊ እንደሆነ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያሉት የገጠር ቀበሌ ማዕከላት 12,300 እንደሆኑም አቶ ፋንታ አመልክተዋል። ከእነዚህ የገጠር ማዕከላት ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ብቻ “የከተማ ፕላን” ወይም “የቀበሌ ማዕከል ፕላን ያላቸው” መሆናቸውንም አክለዋል። 

የፌደራል መንግስት “ሁሉም ከተሞች ፕላን እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረት እያደረገ” እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በጸጥታ ችግር እና በሌሎች ምክንያቶች የሚኒስቴ መስሪያ ቤታቸው የእቅድ አፈጻጸም “ዝቅተኛ” መሆኑን አምነዋል። “አሁን ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሁሉም ክልሎች እና በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ደርሰን መስራት አለመቻላችን አንዱ ችግር ነው” ሲሉ አቶ ፋንታ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። 

“ሁለተኛው በዚህ ዓመት በነበረው የደቡብ ክልል እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ገና በመደራጀት ላይ በመሆናቸው፤ በዚህ ዓመት በሙል አቅም ወደ ስራ አለመግባት ነው። ክልሎች ለመፈጸም ያላቸው ትኩረት ከክልል ክልል የተለያየ መሆን [ሌላኛው] ነው። በእነዚህ ምክንያቶች አፈጻጸማችን ዝቅተኛ ነው” ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከክልሎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን እና በዚህ ዓመት “ሁሉንም ለመድረስ” ጥረቱ መቀጠሉን አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)