“ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግስት አይሳካም” – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 

በኢትዮጵያ መንፈቅለ መንግስት ለማድረግ “ውይይት የሚያደርጉ” አካላት እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። “ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግስት አይሳካም” ሲሉ ለፓርላማ አባላት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “እኛ ወታደሮች ነን። መፈንቅለ መንግስት እንዳይሳካ አድርገን ነው ተቋማት የሰራነው” ሲሉ ተደምጠዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 27፤ 2016 ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። አብይ የመፈንቅለ መንግስት ጉዳይን ያነሱት፤ ስልጣን በኃይል ለመያዝ ስለፈልጉ አካላት ለፓርላማ አባላት ባስረዱበት የንግግራቸው ክፍል ነው። 

“በርካታ ሰዎች በንዋይ ፍቅር ሰክረዋል። ያ የንዋይ ፍቅራቸውን ለመመለስ የመጨረሻው ግብ ስልጣን መያዝ ነው ብለው ያስባሉ። እኔ ካልሆንኩ በቀር ይላሉ” ያሉት አብይ፤ “በቅርቡ መፈንቅለ መንግስት እናካሄዳለን” በሚል ውይይት የጀመሩ ግለሰቦች እንዳሉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ውይይት ያደርጋሉ ያሏቸውን አካላት በግልጽ አላሳወቁም። ሆኖም በንግግራቸው “አንዳንድ አባቶቻችን” እና “ታላላቅ ወንድሞቼ” የሚሉ ገለጻዎችን ተጠቅመዋል። “መፈንቅለ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ አይሳካም” ሲሉም ለእነዚሁ አካላት “ምክር” ለግሰዋል።

“ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግስት አንዴ ተሳካ፤ የዛሬ 50 ዓመት። ከ50 ዓመት በኋላ ብዙ የሚረቡና የማይረቡ ሙከራዎች ነበሩ አልተሳኩም። አሁን ጭራሽ አይሳካም” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። “ተቋማት የሰራነው፤ መፈንቅለ መንግስት እንዳይሳካ አድርገን ነው” ሲሉም አክለዋል።  

“እንበልና ይሄ የማይሳካው ነገር ተሳካ እንበል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነ ሰው ገድለን መፈንቅለ መንግስት ብናደርግ፤ ኢትዮጵያን ሌላ ሱዳን ሌላ ሱዳን እናደርጋት እንደሆን እንጂ ሀገር ሆና፣ እኛም መንግስት ሆነን አንቀጥልም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስጠንቅቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)