ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመሬት ናዳ 257 ዜጎች የሞቱበትን፤ የጎፋ ዞን ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌን በአካል በመገኘት ተመለከቱ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ቦታው የተጓዙት አደጋው በደረሰ በስድስተኛው ቀን ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሰኞ ሐምሌ 15፤ 2016 በደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል አስክሬናቸው የተገኙ ሰዎች ቁጥር 226 መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ትላንት ምሽት አስታውቋል። የአስክሬን ፍለጋው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ የሟቾቹ ቁጥር ወደ 257 ማሻቀቡን እና አጠቃላይ የአደጋው ሰለባዎች ቁጥር 500 ሊደርስ እንደሚችል ከትላንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል። ጽህፈት ቤቱ ለተጨማሪ የመሬት መንሸራተት አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጋለጡ የሚችሉ 15,515 ነዋሪዎች በአፋጣኝ ከአካባቢው እንዲለቅቁ ሊደረግ እንደሚገባም በሪፖርቱ አሳስቦ ነበር።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ትላንት ባወጣው መረጃ ግን ከተመሳሳይ የመሬት ናዳ ስጋት ለመታደግ በዘላቂነት መስፈር እና መቋቋም የሚገባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ቁጥር 6,000 ገደማ እንደሆነ ጠቅሷል። በአደጋው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ከ500 በላይ እንደሆኑም አመልክቷል።
በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦችን ያጽናኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ በጉዳቱ የተሰማቸውን “ጥልቅ ሀዘን” ገልጸዋል ተብሏል። ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ወደ ስፍራው ከተጓዙት ውስጥ ባለቤታቸው ዝናሽ ታያቸው፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ይገኙበታል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጎፋው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱ ዜጎችን ለማሰብ፤ ከዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 20፤ 2016 ጀምሮ ያሉት ተከታታይ ሶስት ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን እንዲሆኑ በትላንትናው ዕለት ማወጁ ይታወሳል። በእነዚህ የሀዘን ቀናት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ በሁሉም የሀገሪቱ ግዛቶች፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም በኢትዮጵያ መርከቦች ላይ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)