የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ተመን ከዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22፤ 2016 ጀምሮ፤ “በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ስርአት እንደተሸጋገረ” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ58 ብር ከ50 ሳንቲም ገደማ ይሸጥ የነበረውን አንድ የአሜሪካን ዶላር፤ በዛሬው ዕለት ወደ 76.73 ብር አስገብቶታል።
የውጭ ምንዛሬ ተመን ለውጡ ተግባራዊ የተደረገው፤ የኢትዮጵያ መንግስት “በገበያ ላይ የተመሰረተ” የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓት ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን በትላንትናው ዕለት ማስታወቁን ተከትሎ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ማሻሻያን ተከትሎ ተግባራዊ የተደረጉ አዳዲስ የፖሊሲ ለውጦችን ዘርዝሯል።
በአዲሱ ማሻሻያ መሰረት፤ የውጭ ምዛሬን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታ እንዲቀር ተደርጓል። በዚህም መሰረት፤ ላኪዎች እና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጭ ምንዛሬ “ለራሳቸው ማስቀረት እንደሚችሉ” ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። ይህ እርምጃ ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት “በእጅጉ ያሻሽላል” ብሏል ባንኩ።
ዛሬ ይፋ በተደረገው የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ለውጥን ተከትሎ፤ በ38 የገቢ ንግድ ሸቀጦች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ መነሳቱንም ብሔራዊ ባንክ ገልጿል። የውጭ ምንዛሬ ገበያው ለገቢ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች “ነጻ” ቢሆንም፤ ወደ ውጭ የሚደረግ የካፒታል ሂሳብ ፍሰት ግን “እንደ በፊቱ የተገደበ” እንደሆነ ባንኩ አስገንዝቧል።
ከዚህ ቀደም ባንኮች ለተለያዩ ገቢ ሸቀጦች የሚጠቀሙበት የነበረው “የውጭ ምንዛሬ አሰራር እና አደላደል ደንቦች” ከዛሬ ጀምሮ እንዲቀሩ መደረጉን ባንኩ አክሏል። ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች፤ ካፈሩት የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለራሳቸው ያስቀሩት የነበረው መጠን “ከ40 በመቶ ወደ 50 በመቶ” ከፍ ማለቱንም ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።
የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ማሻሻያው፤ በባንክ ስር ያልሆኑ የግል የውጭ ምንዛሬ መገበያያዎች (Forex Bureaus) እንዲቋቋሙ ይፈቅዳል። እነዚህ መገበያያዎች፤ የውጭ ምንዛሬ ጥሬ ገንዘብ በገበያ ዋጋ እንዲገዙ እና እንዲሸጡ “የስራ ፈቃድ ይሰጣቸዋል” ተብሏል። አሁን በስራ ላይ ያሉ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች አቋቁመው ተመሳሳይ አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸው ይታወሳል።
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ባንኮችም ሆነ በስራቸው ያሉ የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች፤ የውጭ ምንዛሬ የሚገዙበት እና የሚሸጡበት ተመን የሚወጣላቸው በብሔራዊ ባንክ ነበር። አዲሱ ስርአት ተመኑ “በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል እንዲወሰን” ማድረጉን ተከትሎ፤ በውጭ ምንዛሬ ገበያው ላይ በዛሬው ዕለት ከፍ ያለ ለውጥ ተስተውሏል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው አርብ አንድ ዶላር ይሸጥበት የነበረው ተመን በዛሬው ዕለት በ18.23 ብር አሻቅቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)