🔴 ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ድጎማ እና ማሻሻያዎች “ለተወሰኑ ጊዜያት” ይደረጋል ተብሏል
የኢትዮጵያ መንግስት “በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓት” ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሆነ አስታወቀ። ውሳኔው በመንግስት ቁጥጥር ሲከናወን የቆየውን የውጭ ምንዛሬ ግብይት “በገበያው አማካኝነት እንዲበየን” የሚያደርግ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ እሁድ ማምሻውን ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ውሳኔው ተግባራዊ ሲሆን ብር፤ ዶላር እና ፓውንድን ከመሳሰሉ ዋና ዋና የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለው የምንዛሬ ተመን ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል። አሁን በስራ ላይ በሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርዓት፤ ባንኮች አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ57 ብር ከ50 ሳንቲም ገደማ ገዝተው በ58 ብር ከ64 ሳንቲም ገደማ ይሸጣሉ። በተለምዶ “ጥቁር” እየተባለ በሚጠራው ትይዩ ገበያ በአንጻሩ፤ ይህ የምንዛሪ ተመን ከእጥፍ በላይ ልዩነት አለው።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት፤ ውሳኔው “በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መዛባት ለማስተካከል ይረዳል” ብሏል። የውጭ የምንዛሪ ተመን ስርዓት በገበያው ፍላጎት መሰረት ሲከወን፤ “የገቢ እና የወጪ ሸቀጦችን እና አገልግሎቶችን ዋጋ ከገበያ እውነታዎች ጋር እንዲጣጣም ያስችላል” ያለው መንግስት፤ “በክፍያ ሚዛን ላይ ያለውን አለመመጣጠንም ለማስተካከል ይረዳል” የሚል ተስፋውን ገልጿል።
የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓትን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ በሚያደርጋቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎች እና እርምጃዎች “ተጋላጭ” የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በመግለጫቸው አመልክተዋል። “ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞች የማክሮ ኤኮኖሚ ማሻሻያዎቹ ሊያስከትሉ ከሚችሉት የአጭር ጊዜ አሉታዊ ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ አስፈላጊ የደመወዝ ድጎማ እና ማሻሻያዎች ለተወሰኑ ጊዜያት ይደረጋሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አስፍረዋል። በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚከተለውን ጭማሪም መንግስት በከፊል እንደመደጉም አብይ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)