ስድስት የግል ባንኮች በአዲሱ የውጭ ምንዛሬ ግብይት መጠቀም አልጀመሩም  

በቤርሳቤህ ገብረ

የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ተመን ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ “በገበያ ላይ የተመሰረተ” እንደሚሆን ቢያስታውቅም፤ ስድስት የግል ባንኮች የውጭ ገንዘቦችን የሚገዙበትን እና የሚሸጡበትን የተሻሻለ ተመን እስከ እኩለ ቀን ድረስ ይፋ አለማድረጋቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። የየባንኮቹ ኃላፊዎች በተመኑ ላይ ለመነጋገር ዛሬ ረፋዱን በየፊናቸው ስብሰባ ተቀምጠው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። 

እስከ ዛሬ ድረስ በነበረው አሰራር ባንኮች የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዙበት እና የሚሸጡበትን ተመን የሚያወጣላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነበር። ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ጠዋት ባወጣው መግለጫ፤ የውጭ ምንዛሬ ተመኑ “በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ስርአት መሸጋገሩን” አስታውቋል። ባንኩ ከዚህ በኋላ “ገበያውን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ” እንደሚሆንም ገልጿል። 

ይህን የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ለውጥ ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ተመኑን ከሁሉም አስቀድሞ ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው አርብ አንድ ዶላር ይገዛ የነበረው በ57 ብር ከ50 ሳንቲም የነበረ ሲሆን፤ በአዲሱ ተመኑ ግን የመግዣ ዋጋው ወደ 74 ብር ከ73 ሳንቲም አሻቅቧል። ባንኩ በ58 ብር ከ50 ሳንቲም ይሸጥ የነበረውን አንድ የአሜሪካን ዶላር፤ በዛሬው ዕለት ወደ 76.73 ብር አስገብቶታል።

የግል ባንኮች ያወጣሉ ተብሎ የሚጠበቀው የውጭ ምንዛሬ ተመን፤ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተመን ጋር ተቀራራቢ ይሆናል ብለው እንደሚጠብቁ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነገረቻቸው የአንድ የግል ባንክ ከፍተኛ ኃላፊ ተናግረዋል። ባንኮች ተመኑን የሚወስኑት ያላቸውን የውጭ መገበያያ ገንዘብ ክምችት መሰረት አድርገው መሆኑንም አክለዋል። 

የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ በአካል በመገኘት ከተመለከተቻቸው የግል ባንኮች ቅርንጫፎች ውስጥ በአንዱ ያሉ ስራ አስኪያጅ፤ ከዋናው መስሪያ ቤት አዲስ ተመን እስኪላክላቸው ድረስ ከቀናት በፊት የነበረው የውጭ ምንዛሬ ተመን መጠቀም እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። “እስካሁን ምንዛሬ ፈልጎ የመጣ ግለሰብ ባይኖርም፤ ቢመጡ የምናስተናግዳቸው ባልተሻሻለው የውጭ ምንዛሬ ነው” ሲሉ የባንክ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)