ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያዎች የተደረጉት መቼ ነበር?

ኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘቧ ከዶላር አኳያ ያለውን የምንዛሬ ተመን፤ ባለፉት 33 ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ መጠን ያዳከመችው ለሶስት ጊዜያት ነው። የመጀመሪያው ከደርግ መንግስት መውደቅ በኋላ በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት በ1984 ዓ.ም. የተደረገ ነው። 

በወቅቱ 2.07 ብር የነበረው የዶላር ምንዛሬ 5 ብር ገብቷል። የእዚህ የምንዛሬ ምጣኔ በመቶኛ ሲሰላ የ142 ፐርሰንት ማሻቀብ የታየበት ነበር። ሀገሪቱ ሁለተኛውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ይፋ ያደረገችው በመስከረም 2003 ዓ.ም ነው። በዚህ ጊዜ ብር ከዶላር ጋር ያለው የምንዛሬ ተመን በ16.7 ፐርሰንት ጭማሪ አስመዝግቧል። 

በዚህም መሰረት አንድ የአሜሪካ ዶላር ሲመነዘርበት ከቆየው 13.6 ብር ወደ 16.3 ብር ከፍ ብሏል። የዛሬ 13 ዓመት ገደማ በውጭ ምንዛሬ ረገድ የተመዘገበው ሶስት ብር የሚጠጋ ጭማሪ ነበር። ከሰባት አመት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ይፋ ሲደረግ፤ በወቅቱ የነበረው የመመንዘሪያ ዋጋ ወደ አራት ብር በሚጠጋ መጠን ከፍ ብሏል።

በህዳር 2010 ዓ.ም የተደረገው ይህ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ የ15 በመቶ ጭማሪ የታየበት ነበር። በእዚህ ጊዜ በ23.3 ብር ይመነዘር የነበረው አንድ የአሜሪካ ዶላር፤ በአንድ ጊዜ ወደ 27 ብር ተመደንጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡት፤ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያው ከመንፈቅ በኋላ ነው። 

አብይ ስራቸውን ሲጀምሩ 27.5 ብር የነበረው የአንድ ዶላር ይፋ የባንክ ምንዛሬ ተመን፤ በስድስት ዓመት የስልጣን ዘመናቸው 58.6 ብር ደርሷል። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት በብር እና ዶላር መካከል ያለውን የምንዛሬ ተመን፤ በሽርፍራፊ ሳንቲም ደረጃ በየጊዜው የማዳከም አካሄድ ሲተገብር ቆይቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)