ከውጭ ምንዛሬ ተመን ለውጥ በኋላ ገበያው እንዴት ዋለ?

በናሆም አየለ እና በሙሉጌታ በላይ

የውጭ ምንዛሬ ተመን ከዛሬ ጀምሮ በገበያ ስርዓት እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ፤ በአዲስ አበባ መርካቶ ገበያ እስከ 400 ብር የደረሰ የዋጋ ጭማሪ ተመዘገበ። የዋጋ ጭማሪው በዋናነት የታየው፤ ከውጭ ሀገር በሚገቡ የታሸጉ ምግብ እና መጠጦች እንዲሁም ሌሎች ሸቀጦች ላይ ነው።

ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22፤ 2016 ከሰዓት በኋላ በመርካቶ የተለያዩ የገበያ ስፍራዎች የተዘዋወረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ ከውጭ ሀገር በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የታየውን ያህል ጭማሪ በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ አለመደረጉን ለመታዘብ ችሏል። ዘጋቢው የመጀመሪያውን ቅኝት ያደረገው “ሲዳሞ ተራ” በሚባለው የምግብ ዘይት ምርቶች በስፋት በሚሸጥበት እና በሚከፋፈልበት አካባቢ ነው።

በዚሁ ተራ ከውጭ በሚገቡ የምግብ ዘይት ምርቶች ላይ በዛሬው ዕለት ብቻ ከ30 ብር እስከ 400 ብር የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን ነጋዴዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የዋጋ ጭማሪው “እንደ ዘይቱ ዓይነት እና ተፈላጊነት የተለያየ መሆኑን” ነጋዴዎቹ አስረድተዋል። 

የዋጋ ጭማሪ ካሳዩ “በብዙ ደንበኞች ተፈላጊ ናቸው” ከተባሉት የምግብ ዘይት ዓይነቶች መካከል፤ “ሰንፍላዎር”፣ “ኦማር”፣ “ሃያት” እና “ኦርካይድ” የተባሉት ይገኙበታል። “ሰንፍላዎር” የተሰኘው በ5 ሊትር የተዘጋጀው ዘይት እስከ ትላንት እሁድ ድረስ 920 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን ዛሬ በ70 ብር ጨምሮ 990 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

“ኦማር” የተሰኘው ዘይት ቅዳሜ እና እሁድ በነበረው ገበያ፤ ከ1,035 እስከ 1,045 ብር ይሸጥ ነበር። በዛሬው ገበያ ግን የእዚህ ዘይት ዋጋ 1,100 ብር ሆኗል። በዚህ ዘይት ላይ የታየው ጭማሪ ከ55 ብር እስከ 65 ብር መሆኑን ነጋዴዎች ገልጸዋል። 

በተለምዶ “የሚረጋው  ዘይት” ተብሎ የሚጠራው እና “ሃያት” የሚል መለያ ስም ያለው 3 ሊትር ዘይት ከዚህ ቀደም ይሸጥበት ከነበረበት የ150 ብር ጭማሪ አሳይቷል። የሶስት ሊትሩ “ሃያት” ዘይት ዛሬ 3,900 ብር ዋጋ ወጥቶለታል። 

ይህንኑ ስያሜ የያዘው 5 ሊትሩ ዘይት፤  3,900 ብር ይሸጥ ከነበረበት ዋጋ 400 ብር ጨምሮ ዛሬ በ4,300 ዋጋ ለገበያ ቀርቧል። “ኦርካይድ” የተሰኘው ዘይት በበኩሉ ይሸጥበት ከነበረበት 980 ብር፤ 30 ብር ጨምሮ ዛሬ 1,010 ብር ዋጋ ተቆርጦለታል።

ከውጭ ሀገራት በሚገባው ዘይት ላይ የዋጋ ጭማሪ ይኑር እንጂ፤ የዛሬው የገበያ ሁኔታ የተቀዛቀዘ እንደሆነ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ታዝቧል። ነጋዴዎቹ በቁጥር ሁለት እና ሶስት እየሆኑ፤ ስለ ዶላር ጭማሪ ሲወያዩ ታይተዋል። 

ለወትሮ ገዢዎችን በማስተናገድ ተጠምደው የሚውሉት የመርካቶ የምግብ ዘይት ነጋዴዎች፤ አልፎ አልፎ የሚመጣውን ገዢ የጠየቀውን ሸቀጥ “የለም” እያሉ ከበር ሲመልሱ ዘጋቢው አስተውሏል። የምግብ ዘይት ወደ ክፍለ ሀገር ለመጫን የመጡ ሸማቾች፤ “ዘይት የለም፤ አልገባልንም” የሚል ምላሽ ከነጋዴዎቹ ሲሰጣቸው እንደነበር ዘጋቢው ተመልክቷል።

ይህን ምላሽ ለምን ለደንበኞቻቸው እንደሚሰጡ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ጥያቄ የቀረበላቸው አንድ የዘይት ነጋዴ፤ የውጭ ምንዛሬው ዋጋ ቁርጡ እስከሚታወቅ ድረስ “ከመሸጥ ይልቅ ማስቀመጡ የተሻለ ነው” ብለው በማመናቸው እንደሆነ ነግረውታል።  እንደ ዘይት ነጋዴዎቹ ተመሳሳይ አስተያየታቸውን የገለጹት፤ ከውጭ ሀገራት የሚገቡ የዱቄት ወተት እና የዳይፐር ምርቶችን የሚሸጡ ነጋዴዎች ናቸው። 

በመርካቶ “ጌሾ ተራ” በሚባለው አካባቢ የሚገኙ አንድ ነጋዴ፤ “የዶላር ጭማሪው ከተሰማ በኋላ የዳይፐር እና የወተት ዋጋው ከፍ ብሏል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከቀናት በፊት 128 ፍሬ ዳይፐር፤ በ1,620 ብር ይሸጡ እንደነበር የሚናገሩት ነጋዴው፤ “ዜናው ከተሰማ በኋላ” ግን ዋጋው 80 ብር ጨምሮ 1,700 ብር መግባቱን አስታውቀዋል። 

ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገውን አዲሱን የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ማሻሻያ ተከትሎ፤ የዋጋ ጭማሪ የታየበት ሌላው ምርት ከውጭ ሀገር የሚገባ የታሸገ የዱቄት ወተት ነው። ባለፉት ቀናት በመርካቶ ገበያ 1,850 ብር ይሸጥ የነበረ 900 ግራም “ኒዶ” የዱቄት ወተት፤ 350 ብር ጨምሮ 2,200 ብር እየተሸጠ ይገኛል።  

በ400 ግራም የታሸገው “ቤቢ ላክ“ የዱቄት ወተት ደግሞ በፊት ከነበረበት 650 ብር በ100 ብር ጨምሮ ወደ 750 ብር ከፍ ብሏል። በተመሳሳይ 400 ግራም “ሊፕቶሚል” የተሰኘ የታሸገ የዱቄት ወተት 950 ብር ከሚሸጥበት ዋጋ 20 ብር ጨምሮ 970 ብር ገብቷል።

በመርካቶ ያሉ ነጋዴዎች፤ የውጭ ምንዛሬ ተመን ከዛሬ ጀምሮ “በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ስርአት መሻገሩ” ከተነገረ በኋላ ስጋት ገብቷቸዋል። አዲሱ ስርአት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ፤ በተለምዶ “ጥቁር ገበያ” በሚባለው “ትይዩ ገበያ” ያለው የዶላር ምንዛሬ ዋጋ “ሊቀንስ ይችላል” የሚል ግምት አላቸው። 

ይህ ከሆነ ደግሞ “በእጃችን ላይ ያለው ሸቀጥ ዋጋ በጣም ሊቀንስብን ይችላል” ሲሉ በአልባሳት እና ጫማዎች ንግድ የተሰማሩ አንድ ነጋዴ ስጋታቸውን ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አጋርተዋል። “አሁን ላይ [ዋጋ] አንጨምር እንጂ፤ በቅርቡ በእያንዳንዱ ላይ 200 ብር ጭማሪ ጠብቅ” ሲሉም ነጋዴው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ነግረውታል።  

“አሁን ላይ [ዋጋ] አንጨምር እንጂ፤ በቅርቡ በእያንዳንዱ ላይ 200 ብር ጭማሪ ጠብቅ”

– በመርካቶ ያሉ የአልባሳት እና የጫማዎች ነጋዴ

በዛሬው የገበያ ቅኝት፤ የተለየ የዋጋ ጭማሪ ያልተደረገባቸው የምግብ ምርቶች መኖራቸውን ዘጋቢው በመርካቶ በነበረው ቆይታ ተመልክቷል። እነዚህ የምግብ ምርቶች ፓስታ፣ መኮሮኒ እና የስንዴ ዱቄት ናቸው። 

የተጠቀሱት ምርቶች ባለፈው ሳምንት በነበረው የገበያ ዋጋ ዛሬም ሲሸጡ ውለዋል። መኮሮኒ በኪሎ 106 ብር፣ አንድ ፓስታ ደግሞ ከ72 ብር እስከ 74 ብር ዛሬ በመርካቶ ተሽጧል። አንድ ኪሎ የስንዴ ዱቄት ደግሞ ከ82 ብር እስከ 84 ብር ባለ ዋጋ፤ ዛሬ ለገበያ ቀርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)