በሙሉጌታ በላይ
በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ፈንታሌ ወረዳ በሚገኘው የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ተቀጥረው የሚሰሩ አራት ሰራተኞች፤ በ“ኦነግ ሸኔ” ታጣቂ ቡድን ታግተው መወሰዳቸውን የፋብሪካው ሰራተኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልቃድር የሱፍ፤ በሰራተኞች ላይ እገታ ሲፈጸም በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የስኳር ፋብሪካው ሰራተኞች የታገቱት ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 20፤ 2016 ጠዋት ሁለት ሰዓት ገደማ መሆኑን በዕለቱ በስራ ገበታቸው ላይ የነበሩ አንድ ሰራተኛ ተናግረዋል። ከታገቱት ሰራተኞች ሁለቱ የቀን ሰራተኞች ሲሆን ሌሎቹ በፋብሪካው የሱፐርቫይዝ እና የፎርማን የስራ ኃላፊነት ያላቸውን መሆኑንም አስረድተዋል።
“ሱፐርቫይዘሩ እና ፎርማኑ ‘ኤፍ አንድ’ ከሚባለው የሸንኮራ ማሳ አካባቢ ነው የተወሰዱት። ሁለቱ የቀን ሰራተኞች ‘ኤፍ ሃያ ስድስት’ ከሚባለው የሸንኮራ ማሳ አካባቢ ነው የወሰዷቸው። የሱፐር ቫይዘሩን መኪና አቃጥለዋል። መኪናው ሲቃጠል የፌደራል ፖሊሶች በአካባቢው ደርሰው ነበር። ግን ምንም ማድረግ ሳይችሉ፤ ሰዎቹን ታጣቂዎቹ ይዘዋቸው ሄዱ” ሲሉ በፋብሪካው ለ26 ዓመታት ያገለገሉት ሰራተኛ አብራርተዋል።
የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ሰፊ የሸንኮራ አገዳ ማሳ ስላለው፤ “የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች” በዚህ ማሳ ውስጥ “በቀላሉ” እንደሚገቡም ሰራተኛው ጠቁመዋል። በ1952 ዓ.ም. የተቋቋመው የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ፤ 14,733 ሔክታር ስፋት ባለው መሬት ላይ ያረፈ ነው። ከፋብሪካው ይዞታ ውስጥ 10,246 ሄክታር መሬት የተሸፈነው፤ ለስኳር ምርት ግብአት በሆነው የሸንኮራ አገዳ ሰብል ነው።
ፋብሪካው በዓመት 1.3 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ቢሆንም፤ ላለፉት ሶስት ዓመታት ባጋጠመው “የጸጥታ ችግር” ምክንያት “የአቅሙን ያህል እያመረተ” አለመሆኑን ሰራተኞቹ ይገልጻሉ። የስኳር ፋብሪካው ሰራተኞች የጸጥታ ስጋቱን የፈጠረው፤ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው “ኦነግ ሸኔ የተባለው ታጣቂ ቡድን ነው” ባይ ናቸው።
በዚህ ታጣቂ ቡድን ከሁለት ቀን በፊት መታገታቸው የተገለጸው ሰራተኞች፤ በአጠቃላይ 2.8 ሚሊዮን ብር እንደተጠየቀባቸው በፋብሪካው ለሰባት አመት ያገለገሉ ሰራተኛ “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “ሱፐርቫይዘሩ 1 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል ቤተሰቡ ተጠይቋል። ይዞት የነበረውን መኪናም አቃጥለውበታል። ፎርማኑ 800,000 [ብር] ተጠይቋል። የቀን ሰራተኞቹ የተጠየቁት አምስት አምስት መቶ ሺህ ብር ነው። ከየት ተገኝቶ ነው የሚከፈለው?” ሲሉ በታጣቂ ቡድኑ የተጠየቀውን ገንዘብ ማሟላት ለሰራተኞቹ ቤተሰቦች ከባድ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በፋብሪካው ሰራተኞች ላይ እገታ ሲፈጸም የአሁኑ የመጀመሪያ አለመሆኑን የሚገልጹት እኚሁ ሰራተኛ፤ እነርሱን ለማስለቀቅ የሚጠየቀው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ “ቤተሰብ ልመና እየወጣ” እንደሆነም አክለዋል። ከ15 ቀናት በፊት በ“ኦነግ ሸኔ” ታጣቂ ቡድን ለታገቱ 13 የፋብሪካው ሰራተኞች፤ ቤተሰቦቻቸው ለእያንዳንዳቸው 100,00 ሺህ ብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ለእዚህ አባባላቸው በማስረጃነት ይጠቅሳሉ።
ታጋቾቹ “በቀን ሰራተኛነት የተቀጠሩ” እንደነበሩ የገለጹት ሰራተኛው፤ የታጣቂ ቡድን አባላት ይህንን ሲረዱ “50 ሺህ ብር አስከፍለው” እንደለቀቋቸው አብራርተዋል። “ቤተሰብ ያለውን ከብት ሸጦ፤ ከፍሎ ነው የወጡት” ሲሉም አስራ ሶስቱ ሰራተኞች ስለተለቀቁበት ሂደት ተጨማሪ መረጃ ሰጥተዋል። “በኦነግ ሸኔ” የሚደርሰው ይህን መሰሉ “እገታ እና ጥቃት”፤ ስራቸውን በስጋት ውስጥ ሆነው እንዲያከናውኑ እንዳደረጋቸው የስኳር ፋብሪካው ሰራተኞች ይናገራሉ።
የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት የስኳር ፋብሪካውን ለመጠበቅ ቢሰማሩም፤ “ለውጥ እንዳላመጣላቸው” “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት ሰራተኞች ይስማማሉ። ከሰራተኞቹ አንዱ “ቤት ከመቀመጥ”፤ “በስጋት ውስጥ” ስራቸውን መስራት እንደመረጡ ያስረዳሉ።
“አሁን እኮ እከሌ ተወሰደ፤ እከሌ ሞተ ቀልድ ነው። ምን ታደርጋለህ? ረሃብ ከሚገድልህ፤ ጥይት ቢገድልህ ይሻላል። ረሃብ ጊዜ አይሰጥህም። ባለፈው 50 ሺህ ብር ያስከፈሉ ጊዜ እንደውም ጥሩ ነው። ‘ከዘመድ አዝማድ ለማምኖ መክፈል ይቻላል ነው’ ያለው ሰው። [ሰው] የዚህን ያህል በመንግስት ተስፋ ቆርጧል”
– የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ሰራተኛ
“አሁን እኮ እከሌ ተወሰደ፤ እከሌ ሞተ ቀልድ ነው። ምን ታደርጋለህ? ረሃብ ከሚገድልህ፤ ጥይት ቢገድልህ ይሻላል። ረሃብ ጊዜ አይሰጥህም። ባለፈው 50 ሺህ ብር ያስከፈሉ ጊዜ እንደውም ጥሩ ነው። ‘ከዘመድ አዝማድ ለማምኖ መክፈል ይቻላል ነው’ ያለው ሰው። [ሰው] የዚህን ያህል በመንግስት ተስፋ ቆርጧል” ሲሉ በፋብሪካው ሰራተኛ ዘንድ ይስተዋላል ያሉትን ስሜት አስተጋብተዋል።
እኚሁ ሰራተኛ፤ ፋብሪካው የሚገኝበት የፈንታሌ ወረዳ ኃላፊዎችም ሆነ የፋብሪካው አመራሮች “ችግሩ እንዳለ ያውቃሉ፤ ግን አላገዙንም ሲሉ” ወቅሰዋል። የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልቃድር፤ በፋብሪካው በርካታ የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ቢገኙም፤ “ታጣቂዎቹ በድንገት እየመጡ ሰራተኞችን ያግታሉ” ሲሉ ችግሩን መኖሩን ይቀበላሉ።
ከ15 ቀናት በፊት “9 ሰራተኞች ታግተው፤ ተለቅቀዋል” የሚሉት የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ፤ ባለፈው ቅዳሜ እለትም በተመሳሳይ “አራት የፋብሪካው ሰራተኞች ታግተው መወሰዳቸውን” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር አረጋግጠዋል። “በአጠቃላይ ሁሉም ቦታ ሰላም አይደለም። ሁሉም ቦታ ደግሞ ጦርነት አይደለም ያለው። ስለዚህ ስጋት ያሉባቸው ቦታዎች ላይ እኛ ፓትሮል እናደርጋለን” ሲሉም አቶ አብዱልቃድር ያስገነዝባሉ።
ባለፈው ቅዳሜ የታገቱቱን አራት ሰራተኞች ለማስመለስ “የጸጥታ ኃይሉ ኦፕሬሽን እንደጀመረ” የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ ተናግረዋል። ይህንኑ በተመለከተ በፋብሪካው አካባቢ ከሚገኘው ወረዳ እና ከዞን አመራሮች ጋር ውይይት እንደተካሄደም አክለዋል። ይሁንና የሰራተኞቹን እገታ አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጥያቄ የቀረበላቸው የፈንታሌ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀሰን ኤርሚያስ፤ “ስለጉዳዩ እንደማያውቁ” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምላሽ ሰጥተዋል። “እኔ አዳማ ነው ያለሁት። ሳምንት ሆኖኛል ለስብሰባ ከመጣሁ። ስለጉዳዩ አላወቅሁም” ሲሉ ዋና አስተዳደሪው ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)