የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች የጅምላ መሸጫ ዋጋ ላይ ጣሪያ አስቀመጠ

በቤርሳቤህ ገብረ

በሶማሌ ክልል የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር፤ በስድስት መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ የጅምላ መሸጫ ዋጋ ጣሪያ ከትላንት እሁድ ሐምሌ 28፤ 2016 ጀምሮ ተግባራዊ አደረገ። በዚህ መሰረት በከተማዋ ባለፈው አንድ ሳምንት ወደ 4,000 ብር ገደማ አሻቅቦ የነበረው 20 ሊትር ዘይት፤ ከ2,800 ብር በላይ እንዳይሸጥ የዋጋ ተመን ወጥቶለታል።

የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ከሶማሌ ክልል የንግድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን በትላንትናው ዕለት ይፋ ያደረጉት የዋጋ ዝርዝር፤ ከዘይት በተጨማሪ የሩዝ፣ ፓስታ፣ ስኳር፣ መኮረኒ እና ዱቄት የምግብ ሸቀጦችን የሚመለከት ነው። ሁለቱ አካላት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት፤ የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት በገበያ እንዲመራ ከተወሰነበት ካለፈው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ በምግብ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ በመስተዋሉ ነው ተብሏል።  

በጅግጅጋ ከተማ ላሉ ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ማሻሻያው ከመደረጉ አስቀድሞ በነበረው ዋጋ ሸቀጦችን መሸጥ እንዲቀጥሉ የተነገራቸው ከአምስት ቀን ቀደም ብሎ እንደነበር የሶማሌ ክልል ንግድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱላሂ አደም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ሆኖም ቢሮው ከቀናት በኋላ በገበያው ላይ ባደረገው ጥናት፤ በምግብ ሸቀጦች ላይ ከ150 እስከ 500 ብር የደረሰ ጭማሪ መደረጉን እንደደረሰበት ምክትል ኃላፊው ጠቁመዋል። 

በዚህ ምክንያት ቢሮው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ በመሆን በእነዚህ ሸቀጦች ላይ የጅምላ መሸጫ ጣሪያ ተግባራዊ እንዲደረግ ከውሳኔ ላይ መድረሳቸውን አቶ አብዱላሂ አስረድተዋል። የዋጋው ጣሪያው የሚመለከታቸው ሸቀጦች፤ በውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ላይ ለውጥ ከመደረጉ በፊት ወደ ሀገር ውስጥ የገቡትን እንደሆነም አብራርተዋል። 

ከትላንት ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ በጀመረው የዋጋ ጣሪያ መሰረት፤ በጅግጅጋ ከተማ አምስት ሊትር የምግብ ዘይት መሸጥ የሚቻለው እስከ 800 ብር ባለው ዋጋ ነው። ባለ 20 ሊትር የምግብ ዘይት ዋጋም 2,800 ብር የመሸጫ ጣሪያ ተቀምጦለታል። የተለያየ አይነት ያለው ሩዝ፤ የ50 ኪሎ ግራም የመሸጫ ዋጋ ጣሪያ ከ4,050 እስከ 5,200 ብር እንዳይበልጥ በዋጋ ዝርዝሩ ተገድቧል። 

ይህን የዋጋ ጣሪያ ተላልፈው ዋጋ ጨምረው ሲሸጡ የተገኙ ነጋዴዎች ላይ “እስከ ንግድ ፈቃድ መሰረዝ የደረሰ እርምጃ” እንደሚወስድባቸው የሶማሌ ክልል ንግድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲሃኪም ሼክ ሀሰን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እርሳቸው ይህን ቢሉም፤ በጅግጅጋ፣ ደገሀቡር እና ቀብሪደሀር ከተሞች ባለፈው አንድ ሳምንት የዋጋ ጭማሪ አድርገው ሲሸጡ በመገኘታቸው ተዘግተው የነበሩ 57 የጀምላ ንግድ መሸጫዎች በትላንትናው ዕለት እንዲከፈቱ ተደርገዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)