በሙሉጌታ በላይ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባል አቶ ዘመነ ኃይሉ እና በአማራ ክልል ምክር ቤት የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ መልካሙ ተሾመ በትላንትናው ዕለት በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቤተሰቦቻቸው እና ባልደረቦቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ሁለቱ የምክር ቤት አባላት በአሁኑ ወቅት በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙም ተናግረዋል።
አቶ ዘመኑ በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ፤ በጢስ አባይ ዘንዘልማ ምርጫ ክልል ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነውን አብንን በመወከል ለፓርላማ የተመረጡ ናቸው። በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው የአማራ መልሶ መቋቋም እና ልማት ድርጅት (አመልድ) የሚሰሩት አቶ ዘመኑ፤ ከመስሪያ ቤታቸው በጸጥታ ኃይሎች የተወሰዱት ትላንት ማክሰኞ መስከረም 21፤ 2017 እኩለ ቀን ገደማ መሆኑን አንድ የቤተሰባቸው አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
የፓርላማ አባሉ ከመታሰራቸው ግማሽ ሰዓት አስቀድሞ እርሳቸው በሌሉበት በመኖሪያ ቤታቸው ፍተሻ ተካሄዶ እንደነበር እኚሁ የቤተሰብ አባል አመልክተዋል። ፍተሻውን ያካሄዱት “የመከላከያ ኃይሎች፣ የአማራ ክልል አድማ በታኝ አባላት እና ሚሊሺያዎች” እንደነበሩ የገለጹት የቤተሰብ አባሉ፤ በወቅቱ የፍርድ ቤት የብርበራ ትዕዛዝ አለመያዛቸውንም አብራርተዋል።

በቤት ፍተሻው የተሳተፉት የጸጥታ ኃይሎች ወደ አቶ ዘመኑ መስሪያ ቤት በማምራት፤ ከስራ ገበታቸው ላይ እንዳሉ እንደያዟቸው ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ አንድ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ ዘመኑ የፓርላማ አባል ቢሆኑም፤ “ከህግ አግባብ ውጭ ያለ ምንም የፍርድ ማዘዣ በቁጥጥር ስር ውለዋል” ሲሉ እኚሁ ምንጭ ተናግረዋል።
“ማንኛውም የምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፈንጅ ካልተያዘ በስተቀር፤ ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ እንደማይያዝ እና በወንጀል እንደማይከሰስ” በኢፌዲሪ ህገ መንግስት ተደንግጓል። በ1987 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣውም ሆነ በ1994 ዓ.ም. የተሻሻለው የአማራ ክልል ህገ መንግስትም፤ በውስጡ ተመሳሳይ ድንጋጌ ይዟል።
የክልሉ ህገ መንግስት ይህን ቢልም፤ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ መልካሙ ተሾመ በተመሳሳይ መልኩ በትላትናው ዕለት ከረፋዱ አራት ሰዓት ገደማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ ባልደረባቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። አቶ መልካሙ በጸጥታ ኃይሎች የተያዙት፤ በህግ አማካሪነት ከሚሰሩበት የአማራ ክልል ህንጻ ኮንስትራክሽን ድርጅት በስራ ላይ እንዳሉ መሆኑን ባልደረባቸው አመልክተዋል።

ከሶስት ዓመት በፊት በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ገዢውን ፓርቲ በመወከል በምዕራብ ጎጃም ዞን በምትገኘው ሰከላ ወረዳ የተወዳደሩት አቶ መልካሙ፤ የአማራ ክልል ምክር ቤት ተመራጭ ናቸው። ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ዓመት የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ መልካሙ፤ በአማራ ክልል የጸጥታ ችግር ከተከሰተ በኋላ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።
አቶ መልካሙም ሆነ እንደ እርሳቸው ከስራ ቦታቸው ተወስደው የታሰሩት አቶ ዘመነ፤ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ መጀመሪያ የተወሰዱት በባህር ዳር ከተማ ወደሚገኘው ሙሉአለም የባህል ማእከል አዳራሽ እንደነበር ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሁለቱ የምክር ቤት አባላት ወደ ባህር ዳር ከተማ ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ የተዘዋወሩት ትላንት ምሽት እንደነበር እኚሁ ምንጭ አመልክተዋል።
የምክር ቤት አባላቱ ከተያዙበት ከትላንትና እኩለ ቀን ጀምሮ “ያነጋገራቸው አካል እንደሌለ” እና “በቁጥጥር ስር የዋሉበትን ምክንያት እንደማያውቁ” ከራሳቸው አንደበት መስማታቸውንም ጠቅሰዋል። የሁለቱን የምክር ቤት አባላት እስር በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት፤ የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ እንዲሁም የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
የአማራ ክልል እና የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት በትላንትናው ዕለት በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ “ለክልሉ መንግስት እና ህዝብ ሰላምን ለማስፈን” “የህግ ማስከበር እርምጃ” እየተወሰደ መሆኑን ማስታወቃቸው ይታወሳል። በዚሁ እርምጃ ውስጥ “በህግ ተጠያቂ” ከተደረጉት ውስጥ “በእገታ እና ዘረፋ የተሰማሩ” እንዲሁም በከተማ ሆነው “የማስተባበር” ስራ የሚያከናወኑ ኃይሎች እንደሚገኙበት በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
ከእነዚህ በተጨማሪም የክልሉ መንግስት “ጽንፈኛ” ሲል ለሚጠራቸው ኃይሎች “የሎጀስቲክ እና የመረጃ ምንጮች” በመሆን ሲያገለግሉ ነበሩ የተባሉ ግለሰቦችም በህግ ተጠያቂ እንደሚደረጉ በመግለጫው ተመልክቷል። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ በአማራ ክልል ባሉ ትልልቅ ከተሞች ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸውንም ገልጿል።
በክልሉ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እየተወሰደ ያለውን እርምጃ “የዘፈቀደ የጅምላ እስር” ሲል የጠራው አምነስቲ፤ በዚህም በፌደራል ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩ ምሁራን ጭምር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል። የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት “የዘፈቀደ የጅምላ እስሩን” በአፋጣኝ እንዲያቆሙም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























