በአማራ ክልል “ገቢ ለመሰብሰብ” በሚል የተቋቋሙ ኬላዎች “በፍጥነት እንዲነሱ” ትዕዛዝ ተላለፈ

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች “ገቢ ለመሰብሰብ” በሚል የተዘረጉ ኬላዎች “በፍጥነት እንዲነሱ” የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ትዕዛዝ ሰጠ። ይህን ትዕዛዝ ተላልፎ በተገኘ ማንኛውም የመንግስት አካል ላይ የጸጥታ ኃይሎች ለሚወስዱት “እርምጃ” ቢሮው ኃላፊነት የማይወስድ መሆኑንም አስታውቋል። 

ቢሮው ይህንን ያሳወቀው፤ በክልሉ የዞን እና የከተማ አስተዳደር ስር ላሉ የገቢዎች መምሪያዎች ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ህዳር 17፤ 2018 በጻፈው ደብዳቤ ነው። መስሪያ ቤቱ ትዕዛዙን ለመምሪያዎቹ ያስተላለፈው፤ የአማራ ክልልን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች “ገትተዋል” የተባሉ ኬላዎች እንዲነሱ ከክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ደብዳቤ ከተጻፈለት ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ነው። 

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተቋቋሙ ኬላዎች የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት እንቅስቃሴን “ሲያስተጓጉሉ” እና “ሲያዘገዩ” እንደነበር በደብዳቤው የጠቀሰው የክልሉ ገቢዎች ቢሮ፤ “ያልተገባ ክፍያ በማስከፈል” የምርት ዋጋ እንዲጨምር ማድረጋቸውን አትቷል። እነዚህ ድርጊቶች “የኑሮ ውድነትን በማባባስ”፤ በሸማቾች ላይ ጫና ማሳደራቸውንም ደብዳቤው አክሏል።

የምርቶች “የመጫን እና የማራገፍ አገልግሎት” ክፍያ መሰብሰብ ያለበት አገልግሎቱ በተሰጠበት “ከተማ” አሊያም “ቦታ” መሆን እንዳለበት ክልሉ ባወጣው ደንብ ቢደገነግም፤ ከስፍራው ርቆ ባሉ ኬላዎች “ተደራራቢ ክፍያዎች” እየተጠየቁ መሆኑን ቢሮው በደብዳቤው አስፍሯል። ኬላዎቹ የተቋቋሙት በተለያዩ ከተሞች መውጫ እና መግቢያ በር ላይ፣ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴዎች በሚበዛባቸው ቦታዎች እና በተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች እንደሆኑም ቢሮው አመልክቷል። 

በአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የከተማ አገልግሎት ገቢ ባለሙያ የሆኑት አቶ አሰፋ ወርቅዬ፤ ዞኖች እና ከተሞች ኬላዎችን ሲያቋቋሙ የነበረው “ገቢን ለመሰብሰብ በሚደረግ ጥረት” እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ሆኖም በተወሰኑ ኪሎሜትሮች ልዩነት የሚቋቋሙ ኬላዎች መበራከታቸው የአሽከርካሪዎች “መጉላላት” ማስከተሉን እንዲሁም በእነዚህ ቦታዎች የሚጠየቁ ክፍያዎች “የምርት ዋጋ ጭማሪ እንዲኖር ማድረጉን” አብራርተዋል።

አሽከርካሪዎች ለምርቶች መጫን እና ማራገፍ አገልግሎት የሚጠየቁት ክፍያ አንድ ቦታ ላይ ከከፈሉ፤ በሌሎች ኬላዎች ላይ ክፍያ የፈጸሙበትን ደረሰኝ አሳይተው ማለፍ ይገባቸው እንደነበር ባለሙያው ይገልጻሉ። “ችግሩ ድግግሞሽ ክፍያ መጠየቃቸው ነው” የሚሉት ባለሙያው፤ ይህ አሰራር እንዲቀር እና ኬላዎቹ እንዲነሱ ውሳኔው መተላለፉን ተናግረዋል። 

የአማራ ክልል ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ያጸደቀው የከተሞች የአገልግሎት ገቢ አሰባሰብ እና ታሪፍ ማሻሻያ ደንብ፤ ምርቶችን ለመጫን እና ለማራገፍ የሚሰበሰበውን ክፍያ “በቁርጥ” አስቀምጧል። ክፍያው ለግብርና ምርቶች በኩንታል እና በኪሎ፣ ለእንስሳት ደግሞ በአንድ ከብትና በአንድ ዶሮ ተሰልቶ እንደሆነ ደንቡ ይዘረዝራል። የደን ውጤቶች ክፍያ የሚሰላው በሜትር ኪዩብ ተለክቶ እንደሆነም በደንቡ ላይ ሰፍሯል። 

ይህንን ደንብ መሰረት በማድረግ ከተሞቹ በሚያወጡት “የታሪፍ ምጣኔ”፤ የምርቶች የመጫን እና የመራገፍ አገልግሎት ክፍያን መሰብሰብ የሚችሉት የከተማ አስተዳደሮች ወይም ማዘጋጃ ቤት ብቻ እንደሆኑም ተደንግጓል። ደንቡ ይህን ቢያስቀምጥም፤ በተለያዩ ቦታዎች በተዘረጉ ኬላዎች የሚጠየቁ “ተደራራቢ ክፍያዎች”፤ የክልሉን የምርት እንቅስቃሴ እያስተጓጎሉ እንደሆነ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ በደብዳቤው አጽንኦት ሰጥቷል።

ቢሮው በዚሁ ደብዳቤው “በህገወጥ መንገድ የተቋቋሙ” ሲል የገለጻቸው ኬላዎች፤ “ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት” ጋር በመቀናጀት “በፍጥነት እንዲነሱም ትዕዛዝ ሰጥቷል። “ይህን ክልከላ ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም የመንግስት አካል [ላይ] የጸጥታ ኃይሉ ለሚወስደው እርምጃ ኃላፊነት የማንወስድ መሆኑን እናሳውቃለን” ሲልም ቢሮው አስጠንቅቋል። 

በየአካባቢው የተቋቋሙ “ህገ ወጥ” የተባሉ ኬላዎች እንዲነሱ ውሳኔ በማሳለፍ፤ የአማራ ክልል የመጀመሪያው አይደለም። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሁለት ሳምንት በፊት ባሳለፈው ውሳኔ፤ “ለታክስ”፣ “ለቀረጥ” እና “ለአካባቢ ልማት” በሚል ሽፋን “በየሰፈሩ እና በመንገድ ዳር የተቋቋሙ” ኬላዎች “ሙሉ በሙሉ” እንዲነሱ በተመሳሳይ አዝዞ ነበር። 

ክልሉ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው፤ በየአካባቢው የተቋቋሙ ኬላዎች በክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ “ከፍተኛ ጫና” በማሳደራቸው እንደሆነ ገልጾ ነበር። የጉምሩክ ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ባስደረገው ጥናት፤ በተለያዩ ክልሎች የተቋቋሙ 297 ህገ ወጥ ኬላዎች እንዳሉ ማስታወቁ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)