በናሆም አየለ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስረኛ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኩን፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በወላይታ ሶዶ ከተማ በዛሬው ዕለት ማካሄድ ጀመረ። በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ፤ በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ቁጥራቸው ሁለት ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
የዛሬውን መርሃ ግብር የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ያስጀመሩት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ካሉት 11 ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ናቸው። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ ብሔረሰቦች የሚገኙበት መሆኑ፤ በክልሉ የሚደረገውን የምክክር መድረክ ለየት የሚያደርገው መሆኑን ዶ/ር ዮናስ በንግግራቸው አንስተዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሚደረገው በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ ምክክር መድረክ ላይ፤ የ32 ብሔረሰብ ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሏል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ እስካሁን ባካሄዳቸው ተመሳሳይ መድረኮች ላይ ከ932 ወረዳዎች የተወከሉ 105,370 ዜጎች መሳተፋቸውን ኮሚሽነር ዮናስ አስረድተዋል።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተወከሉት ተሳታፊዎች የተውጣጡት ከ96 ወረዳዎች መሆኑን በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተገልጿል። የክልሉ የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ የሆነችው የወላይታ ሶዶ ከተማ፤ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኩን ለማስተናገድ እንግዶችን መቀበል የጀመረችው ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ጀምሮ ነበር።
በወላይታ ሶዶ ከተማ፤ የሀገራዊ ምክክሩን የተመለከቱ ግዙፍ “ቢልቦርዶች” በየቦታው ተሰቅለው ሁነቱን ለማስተዋወቅ ሞክረዋል። ሆኖም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተሳታፊዎች ምክክር በሚደርጉበት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ያለው ድባብ ግን ከከተማይቱ የተለየ ነው።
በግቢው ውስጥ ዛሬ ስለተጀመረው የምክክር መድረክ የሚያስረዳ አንዳችም ነገር የለም። የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም እንደ ወትሮ ሁሉ የዕለት ተዕለት ስራውን በመስራት ተጠምዷል። በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ “ምን እየተከናወነ እንደሆነ” ያውቁ እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አራት ተማሪዎች፤ የመርሃ ግብሩን ምንነት እንደማያውቁ ምላሽ ሰጥተዋል።



ዛሬ ረፋዱን በዩኒቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካባቢ የተሰባሰቡ ተሳታፊዎች፤ የየብሔረሰቦቻቸውን ባህላዊ አለባበስ ተውበው የመክፈቻውን ስነ ስርዓት በጉጉት ሲጠብቁ ተስተውለዋል። ስነ ስርዓቱ ከተጀመረ በኋላም፤ ከመድረክ ለሚተላለፉ መልዕክቶች ሞቅ ባለ ጭብጨባ ድጋፋቸውን ሲሰጡ ታይተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)