በአዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ ላይ የትውልደ ኢትዮጵያውያን መብት በግልጽ አለመቀመጡ በፓርላማ ጥያቄ አስነሳ 

በቤርሳቤህ ገብረ

አዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ ጸድቆ ስራ ላይ ሲውል፤ በባንክ ስራ ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሀገር ውስጥ ወይም ከውጭ ሀገር ኢንቨስተርነት አንዱን መምረጥ እንደሚኖርባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ። አክሲዮን ገዝተው የነበሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ ሀገር ዜጎች፤ አግባብነት ባላቸው ህጎች መሰረት “እንደ ሀገር ውስጥ ኢንቨስተር የመቆጠር መብት እንዳላቸው” በአዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ ላይ ተደነግጓል።    

በ2000 እና በ2011 ዓ.ም. የወጡትን የባንክ ስራ አዋጆችን የሚሽረው አዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ፤ ለፓርላማ የቀረበው ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ነበር። በተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትላንት ሰኞ ህዳር 2፤ 2017 በጠራው የውይይት መድረክ ላይ፤ የትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ ጨምሮ በአዲሱ “የባንክ ስራ አዋጅ” የሰፈሩ ድንጋጌዎችን የተመለከቱ ጥያቄዎች ቀርበዋል። 

በፓርላማ ውይይት እየተደረገበት ያለው አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ፤ የባንክ ስራን በተመለከተ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ የወጡ አዋጆችን ቁጥር አራት ያደረሰ ነው። በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን በ1986 ዓ.ም. የወጣው የመጀመሪያው አዋጅ፤ የባንክ ስራን ከመንግስት በተጨማሪ ለሀገር ውስጥ የግል ባለሀብቶች ክፍት ሆኖ ቁጥጥር እንዲደረግበት የሚያስችል ሆኖ የተዘጋጀ ነበር።

“የባንክ ስራን ስለመቆጣጠር እና ስለመፍቀድ” የሚል መጠሪያ የነበረው ይህ አዋጅ፤ አዳዲስ ጉዳዮችን ባካተተው እና በ2000 ዓ.ም. በስራ ላይ እንዲውል በተደረገው የባንክ ስራ አዋጅ ተሽሯል። ይህ አዋጅ ከ11 ዓመታት በኋላ ሲሻሻል፤ “የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ” የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን እንዲያካትት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ መንግስት የባንክ አገልግሎትን ለውጭ ኢንቨስተሮች የሚከፍት ፖሊሲ በነሐሴ 2014 ዓ.ም. ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ የተዘጋጀው አዲሱ አዋጅ፤ “ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው” የሚል ጥያቄ ተነስቶበታል። ጥያቄውን በትላንትናው ዕለት በተካሄደው የፓርላማ የአስረጂ የውይይት መድረክ ላይ ያቀረበው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ጉዳዮች ጥናት ዳይሬክቶሬት ነው። 

አዲሱ አዋጅ በዋናነት ትኩረት ያደረገው “የውጭ ሀገር ዜጎች በባንክ የስራ መስክ” መሰማራት እንደሚችሉ መሆኑን ዳይሬክቶሬቱ በጥያቄው ላይ ጠቅሷል። የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎች፤ በህግ የተሰጣቸውን መብቶች ከማስፈጸም አንጻር የተሰጣቸው ትኩረት አነስተኛ ስለሆነ፤ ይህ ሃሳብ “በድጋሚ እንዲታይ” በትላንቱ የውይይት መድረክ ላይ አሳስቧል። 

ለፓርላማ የቀረበው የአዋጅ ረቂቅ “የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎችን” የጠቀሰው “በትርጓሜ” እና “በመሸጋገሪያ ድንጋጌ” ላይ ብቻ ነው። የአዋጁ የትርጓሜ ክፍል፤ “የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆነ የውጭ ዜጋ” ማለት “ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ ሀገር ዜጋ መሆኑን የሚያረጋግጥ ህጋዊ መታወቂያ ያለው ሰው” መሆኑን ያብራራል። 

የአዋጁ “የመሸጋገሪያ ድንጋጌ” በበኩሉ፤ በ2011 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ መሰረት “አክሲዮን ገዝተው የነበሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ ሀገር ዜጎች አግባብነት ባላቸው ህጎች መሰረት እንደ ሀገር ውስጥ ኢንቨስተር የመቆጠር መብት አላቸው” ይላል። በትላንትናው የአስረጂ የውይይት መድረክ ላይ ከተገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የስራ ኃላፊዎች አንዱ የሆኑት አቶ ፍሬዘር አያሌው፤ አዲሱ አዋጁ ከወጣ በኋላ በባንክ ስራ የሚሰማሩ ሰዎች የሚለዩት “የኢትዮጵያ ዜጋ” አሊያም “የውጭ ዜጋ” ተብለው እንደሆነ አስረድተዋል። 

በብሔራዊ ባንክ የባንኪንግ ሱፐርቪዥን ዳይሬክቶሬት ኃላፊ የሆኑት አቶ ፍሬዘር፤ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎች በትውልድ ሀገራቸው የተለያዩ መብቶች ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣ አዋጅ እንዳለ ለፓርላማ አባላት አስታውሰዋል። “የውጭ ዜጋ ሆኖ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከሆነ፤ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በተመለከተ የወጣ አዋጅ አለ። ምርጫ አላቸው። ወይ እንደ ሀገር ውስጥ ኢንቨስተር እንቆጠር ይላሉ። አይ አንፈልግም እንደ ውጭ ዜጋ [እንቆጠር] ካሉ፤ በዚያው መሰረት ይስተናገዳሉ ማለት ነው” ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።  

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

እንደ ውጭ ዜጋ መስተናገድ ፍላጎት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፤ በአዲሱ አዋጁ ላይ የውጭ ዜጎችን የሚመለከቱ አንቀጾች በጠቅላላ ተግባራዊ እንደሚሆኑባቸው አቶ ፍሬዘር ጨምረው ገልጸዋል። የውጭ ዜጎች በባንክ ስራ ስለሚሳተፉበት ሁኔታ የሚዘረዝረው የአዋጁ ክፍል፤  በአንድ ባንክ ውስጥ የውጭ ዜጎች የሚይዙት አጠቃላይ የአክስዮን መጠን “ከባንኩ የተፈረመ ካፒታል ከ49 በመቶ መብለጥ”  እንደማይችል ገደብ ያስቀምጣል። 

በአዲሱ አዋጅ መሰረት፤ የውጭ ዜጎች በአንድ ባንክ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉት “በቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት አማካኝነት በውጭ ሀገር ገንዘብ ብቻ” ነው። የውጭ ዜጎች  በእያንዳንዱ የሂሳብ ዓመት መጨረሻ ከአክሲዮን ባለቤትነት የሚያገኙትን የትርፍ ድርሻ “በኢትዮጵያ ብር መልሰው ኢንቨስት ሊያደርጉ እንደሚችሉም” በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

በትላንትናው የፓርላማ የአስረጂዎች የውይይት መድረክ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ውስጥ እና እንደ ውጭ ሀገር ኢንቨስተር ያላቸው መብት በአዲሱ የባንክ ስራ የአዋጅ ረቂቅ ላይ “ተብራርቶ” መቀመጥ እንዳለበት ለባልደረቦቻቸው ሃሳብ ሰጥተዋል። የእርሳቸው ሃሳብ ተከትሎ በብሔራዊ ባንክ የባንኪንግ ሱፐርቪዥን ዳይሬክቶሬት ኃላፊ፤ የትውልደ ኢትዮጵያውያን መብት በተብራራ መልኩ በአዋጁ ላይ እንዲካተት እንደሚደረግ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)