በአዲስ አበባ መርካቶ ገበያ ተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ያጋጠመው አካባቢ፤ “በመልሶ ማልማት እንዲለማ” ምክረ ሃሳብ ቀረበ

በናሆም አየለ

ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በትላንትናው ዕለት ለሁለተኛ ጊዜ የእሳት አደጋ ያጋጠመው በአዲስ አበባ ከተማ መርካቶ ገበያ የሚገኝ አካባቢ፤ “የአደጋ ደህንነት መስፈርትን ቧሟላ” መልኩ “በመልሶ ማልማት እንዲለማ” ምክረ ሃሳብ ቀረበ። ምክረ ሃሳቡን ያቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ነው።

ትላንት እሁድ ህዳር 8፤ 2017 እኩለ ቀን ገደማ የእሳት አደጋ የደረሰበት የመርካቶ ገበያ ስፍራ፤ በተለምዶ “ድንች ተራ” የሚል ስያሜ ያለው ነው። ስፍራው ከሁለት ሳምንት በፊት በተመሳሳይ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ከነበረው “ነባር የገበያ ማዕከል” በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።

የእሁዱ ቃጠሎ የደረሰበት ስፍራ፤ “በነባር የገበያ ማዕከል” ላይ የሚነግዱ ነጋዴዎች ንብረቶቻቸውን የሚያስቀምጡበት መጋዘን እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የእሳት አደጋው “ጌሾ ግቢ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ከሚገኘው መጋዘን በተጨማሪ በአቅራቢያው የሚገኙ መደብሮች እና መኖሪያ ቤቶች ላይ ውድመት አድርሷል። 

አደጋው በደረሰበት ዕለት በስፍራው የተገኘው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ነጋዴዎች የእሳት ቃጠሎው ወደ ሌሎች የገበያ ማዕከሎች እና መደብሮች እንዳይዛመት በስጋት ሲያስተውሉ ተመልክቷል። የተወሰኑ የአካባቢው ወጣቶች ከእሳት አደጋ ተከላካይ ሰራተኞች ጋር በመሆን ቃጠሎውን በቁጥጥር ስር ለማድረግ ርብርብ ሲያደርጉም አስተውሏል። 

በአንድ ሰዓት ተኩል ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋለውን የትላንትናውን የእሳት አደጋ ለመከላከል፤ ሰባት የውሃ ቦቴዎች እና 18 የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎች  ተሰማርተው እንደነበር የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከእነዚህ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ የኮሚሽኑ እና የቀይ መስቀል ማህበር አምቡላንሶች፤ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ወደ ህክምና ተቋማት ሲወስዱ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። 

በትላንቱ የእሳት አደጋ ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች እና ሁለት የኮሚሽኑ ሰራተኞች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን አቶ ንጋቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከሁለት ሳምንት በፊት በዚሁ አካባቢ በደረሰው ተመሳሳይ አደጋ፤ ዘጠኝ ሰዎች መጎዳታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማስታወቁ አይዘነጋም።

የትላንቱ አደጋ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ረፋድ ድረስ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረቦች አካባቢውን በገመድ በማጠር ጥበቃ ሲያደርጉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። ክልከላውን አልፈው ለመግባት ሲሞክሩ የነበሩ ነዋሪዎች እና ነጋዴዎችን፤ የፖሊስ አባላቱ ወደ ቦታው እንዳይጠጉ በኃይል ሲከላከሉም ታዝቧል።

ፖሊሶች እና የእሳት አደጋ ተከላካይ ሰራተኞች ከመድረሳቸው በፊት ግን የተወሰኑ ነጋዴዎች ንብረቶቻቸውን ከቃጠሎ ማትረፍ ችለዋል። በዚህም ምክንያት በአደጋው “የከፋ ጉዳት” አለመድረሱን የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አስረድተዋል። ቃጠሎው በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላም፤ ነጋዴዎች ንብረታቸውንን ከአካባቢው ለማራቅ ሲጥሩ ታይተዋል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ነጋዴዎች፤ አካባቢው በተደጋጋሚ የእሳት አደጋ እያጋጠመው በመሆኑ ምክንያት “መንግስት ከስፍራው ያነሳናል” የሚል ከፍተኛ ስጋት አላቸው። የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አካባቢውን “ለአደጋ ተጋላጭ” በሚል አስቀድሞ መለየቱን የገለጹት አቶ ንጋቱ፤ በቦታው ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን አስረድተዋል። 

“ያቀረብነው ምክረ ሃሳብ ቦታው እንደ አዲስ በመልሶ ማልማት ወይም የአደጋ ደህንነት መስፈርትን ቧሟላ፣ ደረጃውን በጠበቀ [መንገድ] መገንባት ይኖርበታል ነው። ምክረ ሃሳቡን ተቀብሎ በመልሶ ማልማት ለመስራት የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉ መረጃው አለን። በሂደት ላይ ነው ያለው። ታምኖበታል። ምን አልባትም በዚህ አመት ሊጀመር ይችላል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ አቶ ንጋቱ ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጎበታል]