የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተባቸው ካሉ ስፍራዎች ነዋሪዎችን ማዘዋወር ተጀመረ

በቤርሳቤህ ገብረ

በአፋር ክልል ገቢ ረሱ ዞን ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እየደረሰባቸው ባሉ ሁለት ቀበሌዎች የሚኖሩ አራት ሺህ ገደማ አባወራዎችን፤ “የአደጋ ስጋት ወዳልሆነ ስፍራ” የማዘዋወር ስራ መጀመሩን አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ተናገሩ። አደጋውን ሸሽተው ወደ አዋሽ አርባ ከተማ የገቡ ነዋሪዎችን በአንድ ማዕከል ለማሰባሰብ ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ በድግግሞሽም ሆነ በመጠን ባለፈው አንድ ሳምንት ይበልጥ በበረታው የመሬት መንቀጥቀጥ ይበልጡኑ የተጠቁ ስፍራዎች፤ በገቢ ረሱ ዞን፣ ዱለሳ ወረዳ ስር የሚገኙት የዱሩፍሊ እና ሳገንቶ የተባሉት ቀበሌዎች ናቸው። በቀበሌዎቹ እየደረሰ ያለውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ “የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ” እና በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ድንገት ውሃ መፍለቅ መከሰቱን የዱለሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሊ ደስታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በአካባቢው ወደፊት ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ታሳቢ በማድረግ፤ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ታህሳስ 23፤ 2017 ጀምሮ የሁለቱን ቀበሌ ነዋሪዎች በአቅራቢያው ወደሚገኘው አዋሽ አርባ ከተማ የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ አሊ ገልጸዋል። “የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የቱ ጋር ሊከሰት እንደሚችል ትክክለኛ ቦታዎችን እያወቅን አይደለም። የመሬት መንቀጥቀጥ አናሳ ወደ ሆነበት አካባቢ ነው [ነዋሪዎችን] እያዘዋወርን ያለነው” ሲሉ የወረዳው አስተዳዳሪ አስረድተዋል።

በአፋር ክልል ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ መጠናቸው በሬክተር ስኬል ከ4 እስከ 5.1 የሚለኩ 64 የመሬት መንቀጥቀጦች መከሰታቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ መሰል ክስተቶችን የሚመዘግቡ ተቋማት ያወጧቸው መረጃዎች ያሳያሉ። ትላንት ሐሙስ ለሊት በአካባቢው የተከሰተው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 5.3 የደረሰ እንደሆነ የጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል መዝግቧል። 

ይህ መጠን እስከ ዛሬ በአካባቢው ከተመዘገቡት ሁሉ ከፍተኛው ነው። በህንጻዎች እና በሌሎች ግንባታዎች ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ የመሬት መንቀጥቀጦች፤ በሬክተር ስኬል ከ5.5 እስከ 6.0 መጠን ያላቸው እንደሆኑ በክስተቶቹ ላይ ምርምር ከሚያደርጉ ተቋማት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የአደጋ ስጋት ወደሌለበት ስፍራ የሚዘዋወሩ በዱሩፍሊ እና በሳገንቶ ቀበሌዎች የሚገኙ አባወራዎች ብዛት 4,419 እንደሆነ አቶ አሊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ቀናት ወደ አዋሽ አርባ የተጓጓዙ የአካባቢው ነዋሪዎች፤ በከተማይቱ በሚገኝ የተፈናቃዮች ማዕከል እንዲገቡ መደረጋቸውን አብራርተዋል።

https://twitter.com/ethiopiainsider/status/1874055058339643655?t=fHmM4KL9ggsqUi8wKWxePA&s=19&mx=2

ባለፉት ቀናት በዱለሳ ወረዳ በመሬት መንቀጥቀጡ ሳቢያ ቤቶች መፈራረሳቸውን ተከትሎ፤ የተወሰኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት በአቅራቢያቸው ወዳሉ ከተሞች ሸሽተዋል። አቶ ሀሰን ካሚል የተባሉ የሳገንቶ ቀበሌ ነዋሪ፤ ባለቤታቸውን እና አምስት ልጆቻቸውን ይዘው ወደ አዋሽ አርባ ከተማ የመጡት ከሁለት ቀን በፊት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ወላጅ እናታቸው እና ንብረታቸውን እዚው ሳገንቶ ቀበሌ ትተው መምጣታቸውን የሚገልጹት አቶ ሀሰን፤ አሁን በጊዜያዊነት በአዋሽ አርባ ከተማ በሶስት ሺህ ብር ቤት ተከራይተው መቀመጣቸውን አስረድተዋል። እንደ እርሳቸው ሁሉ ወደ አዋሽ አርባ፣ አዋሽ ሰባት እና መተሐራ ከተማ ለተሰደዱ የአካባቢው ነዋሪዎች አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልግም አቶ ሀሰን አሳስበዋል።

እንደ አቶ ሀሰን ያሉ ተፈናቃዮችን “ወደ አንድ ቦታ ለመሰብሰብ” የቴክኒካል ቡድን መቋቋሙን የዱለሳ ወረዳ አስተዳዳሪ ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ በቴክኒካል ቡድኑ ከተመዘገቡ በኋላ ወደ አዋሽ አርባ ከተማ የተፈናቃይ ማዕከል እንዲገቡ እንደሚደረግ ተናግረዋል። ወደ ማዕከሉ ለሚገቡ ነዋሪዎች ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እንደሚቀርብላቸውም አስተዳዳሪው ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)