በቤርሳቤህ ገብረ
መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎቶች አቅራቢ ኩባንያ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በአገልግሎቶቹ ላይ ያደረገው የዋጋ ጭማሪ፤ በህዝብ ዘንድ “ቁጣ ጭምር የቀሰቀሰ” እና “አስደንጋጭ ነው” ሲሉ አንድ የገዢው ፓርቲ የፓርላማ አባል ተቹ። የዋጋ ማሻሻያ የተደረገው፤ “ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን ባልነካ መልኩ ነው” ሲል ኢትዮ ቴሌኮም ምላሽ ሰጥቷል።
የኢትዮ ቴሌኮም የዋጋ ጭማሪ ጉዳይ መነጋገሪያ የሆነው፤ ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 23፤ 2017 በተካሄደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፊት ለፊት የውይይት መድረክ ላይ ነው። በምክር ቤቱ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተጠራው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ከህዝብ የተሰበሰቡ እና የፓርላማ አባላት በግላቸው ያነሷቸው ጥያቄዎች ቀርበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ወላይታ ዞን፣ ኦፋ ምርጫ ክልል የፓርላማ ተወካይ የሆኑት አቶ መለሰ መና ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል፤ ኢትዮ ቴሌኮም የዛሬ ሶስት ወር ገደማ ያደረገውን የዋጋ ጭማሪ የተመለከተው ይገኝበታል። ኩባንያው ከመስከረም 21፤ 2017 ጀምሮ ያደረገው “የዋጋ ማሻሻያ”፤ “በተወሰኑ ምርት እና አገልግሎቶቹ” ላይ እንደሆነ እና “22 የፓኬጅ አይነቶችን እንደማይነካ” አስታውቆ ነበር።
የዋጋ ጭማሪው የተደረገው በሁሉም አገልግሎቶች ላይ መሆኑን በዛሬው ጥያቄያቸው ላይ ያነሱት አቶ መለሰ፤ ማሻሻያው በህዝብ ዘንድ ፈጥሯል ያሉትን ስሜት አስተጋብተዋል። “በሁሉም product ላይ በአንድ ጊዜ ነው የዋጋ ጭማሪ የተደረገው። ይሄ ደግሞ ትንሽ ህዝብ ውስጥ ቁጣም ጭምር እየቀሰቀሰ ነው” ብለዋል የፓርላማ አባሉ።
“[ለኢትዮ ቴሌኮም] በእርግጥ በጀት ያስፈልጋል። በራሳቸው አቅም እንደሚሄዱ ይታወቃል። ልንደግፋቸው ይገባል ብዬ አስባለሁ። ግን በሁሉም ‘ፕሮዳክቶች ላይ፣ በአንድ ቤት ውስጥ ከአንድ ሪሶርስ ከሚያገኝ ሰው ላይ የመጣበት ሁኔታ ትንሽ አስደንጋጭ [ነው]” ሲሉ የኩባንያው አመራሮች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው፤ ኢትዮ ቴሌኮም በሚሰጠው የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ይታያል ያሉትን የዋጋ መናር በተመለከተ አስተያየት ሰጥተዋል። የአራተኛው ትውልድ የኢንተርኔት ኔትወርክ (4ጂ) እንደሚጠቀሙ የገለጹት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ራሳቸው በየጊዜው የሚገጥማቸውን በማሳያነት አንስተዋል።
እቤቴ wifi አለኝ። ከቤቴ ውጭ ግን 100 ብር ብሞላ አንድ ቀን አያቆየኝም። ወዲያው ነው የሚያልቀው። እና አንዳንዴ በዚህን ያህል ሰዎች የሚሞሉትን ካርድ ‘ቴሌ ይሰርቃል ወይ?’ ብዬ እንድጠረጥር ያደርገኛል”
ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል
“እቤቴ wifi አለኝ። ከቤቴ ውጭ ግን 100 ብር ብሞላ አንድ ቀን አያቆየኝም። ወዲያው ነው የሚያልቀው። እና አንዳንዴ በዚህን ያህል ሰዎች የሚሞሉትን ካርድ ‘ቴሌ ይሰርቃል ወይ?’ ብዬ እንድጠረጥር ያደርገኛል” ያሉት የተደመጡት ዶ/ር ደሳለኝ፤ የ100 ብር ካርድ ለሁለት እና ሶስት ቀን አገልግሎት ሊሰጥ ይገባ እንደነበር በአጽንኦት ተናግረዋል።
ለጥያቄዎቹ ላይ ምላሽ የሰጡት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የቴሌኮም አገልግሎቶች ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲደረግ የነበረው ዋጋውን የማውረድ (slash) አካሄድ እንደሆነ አስረድተዋል። በወቅቱ የተደረጉት የዋጋ ማሻሻያዎች ቅናሽ (discount) የሚባሉ እንዳልሆነም አክለዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በነሐሴ 2012 ዓ.ም. ባደረገው የታሪፍ ማሻሻያ፤ በሞባይል የኢንተርኔት ፓኬጅ ላይ 35 በመቶ እና በሞባይል ድምጽ አገልግሎቱ 29 በመቶ ቅናሽ ማድረጉ ይታወሳል። ኩባንያው ከዓመት በኋላ ባደረገው የዋጋ ማስተካከያ፤ በአጠቃላይ ጥቅል አገልግሎቱ ላይ የ20 በመቶ ቅናሽ ማድረጉም አይዘነጋም።
በነሐሴ 2013 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው በዚህ ማሻሻያ፤ የድምጽ አገልግሎት የሚጠቀሙ የኩባንያው ደንበኞች ከ20 እስከ 30 በመቶ የታሪፍ ቅናሽ እንደሚደረግላቸው ተገልጾ ነበር። ኢትዮ ቴሌኮም መሰል ማሻሻያዎችን ሲያደርግ የቆየው፤ የኩባንያውን አገልግሎቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ ለማድረስ ባለው ዓላማ መሰረት መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ለፓርላማ አባላት ገልጸዋል።
መንግስታዊው ተቋም ይህን በሚያደርግበት ወቅት፤ አገልግሎት በሚሰጥባቸው በርካታ ዘርፎች ያለው “ወጪ ሳይጨምር ቀርቶ አይደለም” ሲሉም ፍሬሕይወት ተናግረዋል። ኩባንያው የሚያስፈልጉት “በርካታ ማስፋፊያዎች” ከውጭ ሀገራት በውጭ ምንዛሬ እንደሚመጣ ያስታወሱት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ በዚህም ምክንያት የዋጋ ጭማሪ መደረጉን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓትን ተግባራዊ ማድረጓ ያመጣቸው “መልካም አጋጣሚዎች” ቢኖሩም፤ የተቋሙ ወጪ በዚያው ልክ መጨመሩን ገልጸዋል። “ከማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጡ በፊት በ58 ብር ስንገዛ የነበረውን፤ ዛሬ የምንገዛበትን የምታቁት ነው” ሲሉ አንድ የአሜሪካን ዶላር በወቅቱ በባንኮች ሲሸጥ የነበረበትን አሁን ካለበት ጋር አነጻጽረዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዛሬው ዕለት አንድ የአሜሪካን ዶላርን ሲሸጥ የዋለው በ126.4 ብር ነው።
“‘ምንም አይነት ዋጋ ሳይጨምር መቀጠል አልቻላችሁም ወይ?’ ያላችሁ እንደሆነ፤ አገልግሎቱን እንዲቋረጥ ነው የምናስገድደው። ትርፋማነትን እያረጋገጥን ካልሄድን ቢዝነስ የመቀጠል ሁኔታ compromise ነው የሚሆነው” ሲሉ ፍሬሕይወት ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። ኢትዮ ቴሌኮም የበጀት ተቋም አለመሆኑን የጠቆሙት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ ከሚገኘው ትርፍ መልሶ ኢንቨስት ለማድረግ የፋይናንስ አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በ2016 በጀት ዓመት ካስመዘገበው 93.7 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ውስጥ፤ ያገኘው ትርፍ 21.79 ቢሊዮን ብር ነው። ተቋሙ በዘንድሮው በጀት ዓመት ገቢውን በ75 በመቶ ገደማ በማሳደግ 163.7 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ማቀዱን ባለፈው መስከረም ወር አስታውቋል።
የደንበኞቹን ቁጥር በተያዘው በጀት ዓመት 83 ሚሊዮን ለማድረስ ግብ ያስቀመጠው ኢትዮ ቴሌኮም፤ ከሶስት ወራት በፊት ያደረገው የዋጋ ጭማሪ አሁን ያሉትን 75 በመቶ ተጠቃሚዎች የመክፈል አቅምን “ባገነዘበ መልኩ” የተደረገ ነው ባይ ነው። የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ለዚህ በማስረጃነት የጠቀሱት በአንድ፣ በሶስት እና በአምስት ብር ጥቅል ተጠቃሚዎች ላይ ምንም አይነት የታሪፍ ማሻሻያ አለመድረጉን ነው።
“ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው ሳንነካ ነው የዋጋ ማሻሻያ ያደረግነው። [ማሻሻያው የተደረገው] ለእናንተ የምንሰጠውን አገልግሎት ጥራቱን አስጠብቀን ለመሄድ ስለሚያስቸግረን ነው”
ፍሬሕይወት ታምሩ፤ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ
“ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው ሳንነካ ነው የዋጋ ማሻሻያ ያደረግነው። [ማሻሻያው የተደረገው] ለእናንተ የምንሰጠውን አገልግሎት ጥራቱን አስጠብቀን ለመሄድ ስለሚያስቸግረን ነው” ያሉት ፍሬሕይወት፤ “ዛሬ የጠየቃችሁትን የአገልግሎት ጥራት እና ሽፋንን፤ [ኢትዮ ቴሌኮም] ገቢው ሳያድግ በምን ያስተካክለዋል?” ሲሉም ጥያቄ ሰንዘረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)